Arts

​”እኔን የሚያክል ዘፋኝ በኢትዮጵያ አልተፈጠረም፣ ወደፊትም አይፈጠርም- አርቲስት ሙሉቀን መለሰ

የውልደት ስሙ ሙሉቀን ታምር ጥሩነህ ነው። ወላጆቹ ቄሰ ገበዝ ታምር ጥሩነህና ወ/ሮ እናትነሽ ጌታሁን በሞት ሲለዩት ያሳደጉት አጎቱ አቶ መለሰ ገሠሠ በስማቸው እንዲጠራ አድርገውት ሙሉቀን መለሰ በሚል ስም አወቅነው። አራት እህትና ሦስት ወንድሞች ሲኖሩት ባለትዳርና በሕይወት ዘመኑ ያፈራቸው ሦስት ልጆች አሉት።
ግጥሞቹ ለሐዘን ከልብ የሚያስለቅሱ ‘ለመፅናናት ዕንባ የሚያብሱ ‘ ፍቅር ገላጭ፣ ናፍቆት ነጋሪ፣ ለመረዳት ለሕፃናት አንኳን ቀላል ስለነበሩ መወደድ ችለዋል። ድምፁ በመስረፅ አቅሙ አዛውንቶች ሳይቀር እንኳን “ እስኪ የሙሉቀንን ክፈቱ” ይሉ ነበር።

በ1970ዎቹ አጋማሽ ላይ በመንገድ ላይ ገመድ የሚዘሉ ሕፃናት፣ መንገድ ላይ የተቀደደ ልብስ የሚጠቅሙ ልብስ ሰፊ፣ ጫማ የሚጠርግ ሊስትሮ፣ ታክሲ የሚያሽከረክረው ሾፌርና በራሱ ኃሳብ የነጎደውም ተሳፋሪ ቢሆን በመንገድ ሲዘፍኑ የሚሰማው

‹‹ናኑ ናኑ ነይ ናኑ ናኑ ነይ

ካንቺ አለኝ ጉዳይ›› እንደነበረ በወቅቱ የነበሩ ምስክር ናቸው።

በፍቅር የተጠመደች ጉብል፣ በኃዘን የተጎዳው ኮበሌ፣ በናፍቆት የምትብሰከሰክ እመቤት ‘

‹‹በሐሳብ መዋለሌ እሷን መናፈቄ

ተወደድኩ ብዬ ነው ዘወትር መጨነቄ

እንዲያው ለስም ብቻ ከሆነ መውደዴ

ከጨከነ ልቧ ቁረጥልኝ ሆዴ።›› እያሉ የሙሉቀንን ዜማ ያንጎራጉሩ ነበር።

የከተማ ሻይ ቤቶች፣ የአንዋር መስኪድ አካባቢ ሙዚቃ ሱቆች፣ የቀበሌ የስብሰባ አዳራሾች፣ የገጠር አውቶብሶች፣የኢትዮጵያ ራዲዩ እንኳን በአብዮት መዝሙር ለተሰላቹ አድማጮች ‹‹እምቧ በለው በለው››ን አስታኮ ለሕዝብ ያቀርብ ነበር። የሙሉቀን ዘፈኖች የሕዝብ መዝሙር እስኪመስል ድረስ የታወቁና የተወደዱ ነበሩ።

ሙሉቀን መለሰ ከሙዚቃው ዓለም ራሱን ካገለለ ሩብ ምዕተ ዓመት ሆኖት እንኳን ዛሬም ድረስ ተወዳጅነታቸው አልቀነሰም። ከሙዚቃው ራሱን ቢያገልም መዝሙሮችን በመዘመር በፕሮቴስታንት እምነት ተከታይነቱ አሁንም አገልግሎት ይሰጣል። ዛሬ መኖሪያውን በአሌክሳንደሪያ ቨርጂኒያ ዩ ኤስ ኤ ያደረገው ሙሉቀን ማን ነው፣ አሁን ሙሉቀን የትና በምን ሁኔታ ላይ ነው፣ ምንስ እየሠራ ነው ፣ለአፍቃሪዎቹስ

ጥያቄ፡- ሙሉቀን! ለቃለመጠይቃችን ፍቃደኛ ስለሆንክልን በቅድሚያ በምሥጋና ልጀምር።

ሙሉቀን፡-እኔም ስለግብዣችሁ አመሰግናለሁ።

ጥያቄ፡-እስቲ ከውልደትህ እና እድገትህ በመነሳት ጥያቄዬን ልጀምር፣ የልጅነት ጊዜህ ምን ይመስል ነበር፣ መቼ እና የት ተወለድክ፣ ከዚህ ብንነሳስ፣

ሙሉቀን፡- የተወለድኩት ጎጃም ጠቅላይ ግዛት ተብሎ በሚጠራው አገር ነው።

ጥያቄ፡-ዘመኑ ትዝ ይልሃል?

ሙሉቀን፡- እኔ ስወለድ አላውቅም፣ ወላጆቼ የነገሩኝን ነው የማውቀው ፤ በእኔ መታወቂያ ላይ ያለውና እኔም የማውቀው በ1946 ነው፣ ነገር ግን እህቴ ደግሞ ከአባታችን መጽሐፍ ላይ በማስታወሻነት ተፅፎ ተገኘ የምትለኝ 1948 ዓ.ም ነው። የሁለት ዓመት ስህተት አለ። ይኼኛው ትክክል ነው ለማለት እቸገራለሁ። የማውቀው ግን 1946 ዓ.ም መሆኑንን ነው።

ጥያቄ፡-፡- እስቲ እያንዳንዱን ጥያቄ ከማንሳት ይልቅ፣ አጠር እያደረክ ከትውልድ እስከ እድገት ያለኸን ሕይወት አውጋን፣ ከወላጆችህ ሥም ጀምርልን።

ሙሉቀን፡- ወላጅ አባቴ ቀሰ ገበዝ ተዓምር ጥሩነህ ይባላል። እናቴ ወ/ሮ እናትነሽ ጌታሁን ናት።

ጥያቄ፡-፡- ለወላጆችህ ብቸኛ ልጅ ነህ ወይስ እህቶች እና ወንድሞች አሉህ?

ሙሉቀን፡- አዎ! ሦስት ወንድሞችና እና አራት እህቶች አሉኝ።

ጥያቄ፡-አባትህ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ቄስ ገበዝ እንደነበሩ አንስተሃል፣ ለመሆን በልጅነትህ ከቤተክርስቲያን ጋር የነበረህ ቅርበት እንዴት ነበር?

ሙሉቀን፡- አባቴ ምንጊዜም ቤተክርስቲያን ይዞኝ በመሄድ እኔም የሱን አርዓያነት እንድከተል ይፈልግ ነበር። ከበሮ አመታት፣ አቋቋም ፣የቤተክህነት ሥርዓትም ያስተምረኝ ነበር።

ጥያቄ፡-በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ  የሚያውቅህ እና የሚያደንቅህ በዜማዎችህ ነው።  እስቲ ወደ ሙዚቃ ዓለም እንዴት እንደገባህ እንጀምርና፣ ከሙዚቃው ዓለም ተለይተህ የቆየኽባቸውን ደግሞ አንመልከት። ለመሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሙዚቃ ዓለም እንዴት ገባህ?

ሙሉቀን፡- ከምንም ነገር በላይ የምወዳት እናቴ የአምስት ዓመት ልጅ እንዳለሁ ሞተችብኝ። በሕፃንነት ዕድሜ ኃዘኔ በጣም የበረታ ነበር። ቀንም ማታም አለቅሳለሁ። ኑሯችን በጣም  ተዛባ። በዚህ ላይ ሽፍታ መጥቶ ንብረታችንን ዘርፎ ቤታችንን አቃጠለብን፤ እኛም ሜዳ ላይ ቀረን። ይኽ በሆነ በዓመቱ አጎቴ ከአዲስ አበባ መጣና እኔን መርጦ አስተምረዋለሁ ብሎ ይዞኝ አዲስ አበባ ገባ።

ጥያቄ፡-እስቲ ዝንባሌህ ወደ ሙዚቃ ያመራው መቼ እንደሆነ በቅድሚያ ንገረን፣

ሙሉቀን፡- ከመነሻው ልጀምር ብዬ ነው እሱን እነግርሃለሁ፣ምን አስቸኮለህ?

ጥያቄ፡- መቸኮሌ ሳይሆን ጥያቄውና መልሱ እንዲጣጣም ብዬ ነው።

ሙሉቀን፡-  እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ የሙዚቃ ፍቅር ያደረብኝ ሠርግ ቤት ሲዘፍኑ ሰውነቴን ሁሉ ይወርረኝ ነበር።እኔም ከዘፈን ጋር የተያያዘ ተፈጠሮ እንዳለኝ ይሰማኝ የነበረው የዛን ጊዜ ነው።

ጥያቄ፡-በል አሁን ወደኋላ ተመልሰህ ቅድም የጀመርከውን ጨርስልኝ፣

ሙሉቀን፡- የቱን?

ጥያቄ፡-ቅድም አቋርጠኸኝ “ልነግርህ ነው አትቸኩል” ያልከኝን ነዋ!

ሙሉቀን፡- ቅድሙኑ ብታስጨርስኝ ምን ነበረበት?

ጥያቄ፡-ይቅርታ አሁን መቀጠል ትችላለህ።

ሙሉቀን፡- እሺ ይባርክህ! እናቴ ስትሞትብኝ የእኔ ኃዘን መሪር ነበር። አንድ ቀን በሠፈራችን ውስጥ በጣም አዝኜና ልቤ ተሰብሮ ወዲያ ወዲህ ስል ከሠማይ እጅ ሲመጣ አየሁ፡ ይኼ እጅ በግራ ጡቴ በኩል አንድ ነገር ከውስጤ ወስዶ ሌላ ነገር በመተካት ወደ ሠማይ መልሶ ሲያርግ ተሰማኝ። እኔ አላወቅሁትም እንጂ ገና በሕፃንነቴ ነበር ጌታ መንፈሣዊ ያረገኝ ለካስ፤ አሮጌው ልቤን ወስዶ አዲስ ልብ ነው የተካልኝ።

ጥያቄ፡- አንተ ገና ብዙ ያልተጠቀምክበት ትኩስ የህፃን ልጅ አዲስ ልብ ነው ያለህ ‘እንዴት አሮጌ ልብ አልከው?

ሙሉቀን፡- አልተግባባንም! መንፈሣዊ እና አለማዊ ልብ ይለያያል። ያንን መንፈሣዊ አዲስ ልብ ነበር ጌታ የተካልኝ። በወቅቱ ግን ሕፃን በመሆኔ አልገባኝም ነበር።

ጥያቄ፡-ከአጎትህ ጋር ወደ አዲስ አበባ ከመጣህ በኋላ ያለውን ሕይወትህን እስቲ አጫውተን?

ሙሉቀን፡- አጎቴ የመጀመሪያውን የት/ቤት ደብተሬን ገዝቶ በላዩ ላይ ‹‹ሙሉቀን መለሰ›› ብሎ የፃፈበት እሱ ነበር። እንግዲህ ከዚያን ቀን ጀምሮ ሙሉቀን ታምር ጥሩነህ መባሌ ቀርቶ ሙሉቀን መለሰ ገሠሠ ሆንኩ። የምንኖርበት ሠፈር ኮልፌ ልዩ ስሙ ፍሪዶሮ የሚባል የልጆች ት/ቤት ነበር። አጎቴ እዛ እንዳስገባኝ ትምህርት በጣም ያስጠላኝ ነበር። በተለይ ሂሳብ የሚባል ትምህርት ጠላቴ ነው። እኔ የምወደው የመዝሙር ክፍለ ጊዜ ሲሆን። ስነ-ፅሁፍም እወድ ነበር።

ታዲያ በመዝሙር ክፍለጊዜ ስዘምር የተመለከቱኝ አስተማሪ በንዲራ ሲወጣ እና ሲወርድ የትምህርት ቤቱ ዘማሪ አደረጉኝ።

ጥያቄ፡-ለመሆኑ እስከ ስንተኛ ክፍል ተምረሃል?

ሙሉቀን፡- ረሳሁት እስከ ሦስተኛ ክፍል የተማርኩ ይመስለኛል።

ጥያቄ፡-ድምፃዊው ጥላሁን ገሠሠ በሁለት ክፍል ይበልጥሃላ!

ሙሉቀን፡- እሱ እዚያ ደርሷል እንዴ?

ጥያቄ፡-›­ እኛ የምናውቀው እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ መማሩን ነው። እሱም እንዳንተ ትምሀርት በተለይ ሂሳብ እንደማይወድ ይናገር ነበር።

ሙሉቀን፡- እንዲያውም አሁን ትዝ አለኝ። እኔም አምስተኛ ክፍል ድረስ ነው እዚያ የተማርኩት።

ጥያቄ፡-ጥሩ ድምፅ ያላችሁ ታዋቂ ድምፃዊያን ከአምስተኛ ክፍል በላይ አትሄዱም ማለት ይሆን?

ሙሉቀን፡- እንደሱ እንኳን አይመስለኝም ፣ አጋጣሚ ሆኖ እንጂ። ብዙ ድምፃዊያን ከዛ በላይ የተማሩና ከዚያም በታች ተምረው ታዋቂ የሆኑ አሉ።

ጥያቄ፡-ከዚያ በኋላ እንዴት ወደምትታወቅበት የሙዚቃ ዓለም ገባህ?

ሙሉቀን፡- አሁንም አትቸኩልብኛ፣ አብራርቼ ልንገርህ።

ጥያቄ፡-ይቅርታ እንደሚመችህ ቀጥል።

ሙሉቀን፡- አጎቴ ወ/ሮ ፈሰሱ የምትባል ሚስት ነበረችው። በጣም ጠንቋይ ትወዳለች። ውሎዋ እዛው ነው። ልጅ መውለድ ስላልቻለች አጎቴ ልጅ ፈልጎ ከሌላ የወለዳቸውን ስድስት ልጆች በጥንቆላ አስገድላለች።የሠይጣን ቁራጭ የሆነች ጋኔን የሰፈረባት ሴት ነበረች። እኔን በጣም ትበድለኝ እና ታስርበኝ ነበር። ንብረቴን እንዲወርስ ሆን ብሎ ነው ያመጣው የሚል ቁጭት ስላለባት እኔንም ማጥፋት ትፈልጋለች። ታዲያ እዛው አጎቴ ቤት ሠራተኛ የነበረች ደሜ የምትባል መልካም ሴት ነበረች። ለእኔ መቼም ምንጊዜም የማልረሳት ባለውለታዬ ነበረች፡ የአጎቴ ሚስት ከቤት አስወጥታ በር ስትዘጋብኝ ይኽቺ ደሜ የምትባለው ሠራተኛ የሚበላ ነገር ደብቃ በአጥር በኩል ቀስ ብላ ታቀብለኛለች። ሊዮን የሚባለው ግዙፍ የአጎቴ የጀርመን ውሻ በጣም ስለሚወደኝ ከኔ ጋር ውጪ ተኝቶ ሲጠብቀኝ ያድራል።

ጥያቄ፡-ለምን ይኽን በደልህን ለአጎትህ አትናገርም ነበር?

ሙሉቀን፡- እሱ የት ተገኝቶ? የት ውሎ የት እንደሚያድር አላውቅም። የሥራ ጠባዩ ስለሆነ ብዙ ጊዜ እቤት አይመጣም ድንገት ከመጣም እኔ በግል እንዳላነጋግረው አጋጣሚውን ሁሉ ትደፍንብኛለች። እኔ ሕፃን ነኝ። በደል በጣም ሲበዛብኝ ራሴን ማጥፋት ወሰንኩ። ሶስት ጊዜ ራሴን ልሰቅል ከዛፍ ላይ ወጥቼ ሰው ደርሶ አድኖኛል። በልጅነቴ የደረሰብኝ በደል በተለይ የጎሹ አባት የሚባሉ አዛውንት ብዙ ጊዜ ተከታትለለው ከሞት አትርፈውኛል። ኑሮ በጣም መሮኝ ነበር። በዚህ ላይ ቤተሰቦቼ ይናፍቁኛል። ለሁሉም ነገር መፍትሔ ስላጣሁለት ነበር ራሴን ማጥፋት የመረጥኩት።

ጥያቄ፡-ይኼ በጣም የሚያሳዝን ታሪክ ነው። ለመሆኑ ከዛ ሁሉ ስቃይ እንዴት ተገላግለህ እኛ የምናውቀውን ሙሉቀንን ለመሆን በቃህ?

ሙሉቀን፡- አሁንም አትቸኩልብኛ ! ልነግርህ እኮ ነው።

ጥያቄ፡-መጨረሻው ናፈቀኝ። ይቅርታ!

ሙሉቀን፡- አንድ ቀን የሠፈራችን ሕፃናት ጳውሎስ የሚባል ትምህርት ቤት ኃይለስላሴ ገንዘብ ይሰጣሉ እያሉ ሲያወሩ ሰምቼ እኔም ከጃንሆይ ገንዘብ ልቀበል ወደዚያው ስሮጥ ሄድኩና ከሌሎቹ ጋር ተቀላቅዬ ተሰለፍኩ።ለነገሩ ሁሉም አንዴ ብቻ ተቀብሎ ይሄዳል እኔ ግን ሕጉን ስለማላውቅ ከተቀበልኩ በኋላ ብሩን ኪሴ ከትቼ እንደገና ከኋላ ሄጄ እሰለፍና እቀበላለሁ። የጃንሆይ አጃቢዎች እና ፖሊሶች ሊያስጥሉኝና ሊከለክሉኝ ሲሞክሩ ጃንሆይ ተውት ይላሉ። በመጀመሪያ ቀን ብዙ ብር ወደ ሰላሳ ብር የሚሆን ተቀብዬ ገባሁ። በጣም ደስ አለኝ። የበለጠ ገንዘብ ለማግኘት ሎተሪ ሁሉ እገዛ ነበር።

(የአንድ መልአክ ስም ጠቅሶ)የሌባ ሽርክ ነው ሲባል እሰማ ስለነበር (የሚጠቅሰው መልአክ ስም) እየሄድኩ ሎተሪ እንዲደርሰኝ እፀልያለሁ፣ እሳላለሁ። የምፀልየው ደግሞ በአባቴ ስም ነው። ግን አንድ ጊዜም ደርሶኝ አያውቅም። እኔም (የሚጠቅሰው መልአክ ስም) ተሳድቤ፣ (የሚጠቅሰው መልአክ ስም))  ተሳድቤ፣ እግዚአብሔር የለም እያልኩ እሄዳለሁ።

ጥያቄ፡-ይኽን በምታደርግበት ጊዜ የስንት ዓመት ልጅ ትሆናለህ?

ሙሉ ቀን፡- እድሜዬ የዛን ጊዜ ሰባት ወይም ስምንት ቢሆን ነው።

ጥያቄ፡-ታዲያ እኮ ሎቶሪ ቢደርስህም አይሰጡህም ነበር። ሎቶሪ ተጫውቶ ለማሸነፍ የእድሜ ገደብ አለው?

ሙሉቀን፡- እሱን እንኳን አላውቅም እኔ ሎቶሪ ገዝቼ ከደረሰኝ ሃብታም እንደምሆን ነው የማስበው።

ጥያቄ፡-ወደ ሙዚቃ ዓለም የወሰደህ መስመር እንዴት ተከፈተ?

ሙሉቀን፡- ብዙም ሳንቆይ አንድ ቀን ኮልፌ አጠና ተራ የአባት ጡረተኞች እና ወላጅ ያጡ ሕፃናትን የሚቀበሉ አሉ ሲባል ወሬ ሰማሁና ሄድኩ። ነገሩ እውነት ነበር ብዙ ችግር ሳይገጥመኝ ወዲያውኑ ተቀበሉኝ። ትምሕርት ቤቱ አዳሪ ነው።የተደራረበ አልጋ ላይ እንተኛለን። የሚቀርብልን ምግብ የሽሮ ዓይነት ነው። የሽሮ ቀይ ወጥ& የሽሮ አልጫ፣ ሁሉም ነገር ሽሮ በሽሮ ነው። የግድ ሆነና እዛው ኑሮን ተያያዝኩት ። ዞሬ መግቢያ አገኘሁ። ከጊዜ በኋላ ታዋቂ የሆኑ አርቲስቶች ሁሉ እዛው ነበሩ።

ጥያቄ፡-እነማን እንደሆኑ ትዝ ይልሃል?

ሙሉቀን፡- እነ ፋንቱ ማንዶዬ፣ ግርማ ወልደሚካኤል፣ ቁምላቸው (በኋላ ትራምፔት ተጫዋች የሆነ)…ብቻ የሌሎቹ ሥም ተረስቶኛል እንጂ ሌሎችም ነበሩ።

ጥያቄ፡-የአዳሪ ትምህርት ቤት ሕይወትህ እንዴት አበቃ?

ሙሉቀን፡- የዚያን ትምሕርት ቤት የበላይ ጠባቂ የነበሩት የከንቲባ ዘውዴ ገብረሕይወት ባለቤት ወ/ሮ ደብረወርቅ ይባላሉ። ባለቤታቸው ከንቲባ ዘውዴ ቢትወደድ ተብለው  የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ነበሩ።

በትምሕርት ቤቱ ውስጥ የምታወቀው በመዝሙር ችሎታዬ ነው። ትምሕርት በተለይ ሂሳብ የሚሉት ነገር አይሆንልኝም። ታዲያ አንድ ቀን የትምሕርት ቤቱ የበላይ ጠባቂ ወ/ሮ ደብረወርቅ ይመጣሉ ተባለና ተማሪዎች በሙሉ ተሰልፈን መጠበቅ ጀመርን። እኚሁ ሴት እኛ በሰልፍ ላይ እያለን ትምሕርት ቤቱን ጎበኙና ወደ እኛ ሲመጡ ዓይናቸው እኔ ላይ አረፈና አስጠሩኝ።‹‹ይኼ  የማነው ቆንጆ? ምን ሆኖ እዚህ ገባ?›› ብለው ጠየቁ። ‹‹እናት እና አባት የለኝም ብሎ ስለነገረን ተቀበልነው›› ብለው ነገሯቸው። በጣም አዘኑልኝ። አንዳንድ ነገር አዘጋጅቼለት እኔ ወስጄ አሳድገዋለሁ አሉ።

‹‹ለመሆኑ በትምሕርቱ ጎበዝ ነው? ምን ይወዳል?›› የሚል ጥያቄ ለት/ቤቱ ዳይሬክተር ሲያቀርቡላቸው፣ ዳይሬክተሩም ‹‹እሱ የሚወደው መዝሙር እና ሙዚቃ ብቻ ነው›› አሏቸው። በዚኽ ጊዜ ወ/ሮ ደብረወርቅ ‹‹ወደ ውጪ ልኬ እንዲማር አደርጋለሁ›› አሉና የእለቱን ጉብኝታቸውን ጨርሰው ሄዱ። በሳምንቱ ተመልሰው ሲመጡ ለእኔ ሹራብ፣ሸሚዝ ፣ ሱሬ እና ጫማ ይዘውልኝ መጡ። ሙዚቃ የሚወድ ከሆነ ከሌሎች እንደዚህ ያለ ፍላጎት ያላቸው ልጆች እንዲመለመሉ ትዕዛዝ ሰጥተው በአጭር ጊዜ ውስጥ  ከጀርመን አገር የሙዚቃ መሣሪያ መጥቶልኝ አቶ ተፈራ አቡነወልድ የሚባል የሙዚቃ መምሕር ተመድቦልን ሙዚቃ መማር ጀመርን።

ጥያቄ፡-ለመሆኑ ከሌሎች አብረውህ ከነበሩ ተማሪዎች ጋር የነበረህ ግንኙነት እንዴት ነበር?

ሙሉቀን፡- ጥሩ አልነበረም።

ጥያቄ፡-ለምን?

ሙሉቀን፡- ይቀኑብኛል።

ጥያቄ፡-በምንድን ነው የሚቀኑብህ? በመልክህ ? በዘፈን ችሎታህ? ቅናቱ ከምን የመነጨ ነው?

ሙሉቀን፡- አላናግር እኮ አልከኝ!

ጥያቄ፡-ሙሉቀን! ቃለመጠይቅ ህግ አለው። እኔ እጠይቃለሁ አንተ ትመልሳለህ። ጥያቄና መልሱ የተያያዘ እንዲሆን  ማድረጉ የእኔ ፋንታ ነው። ስለዚህ በመሃል ገብቼ ጥያቄ ሳቀርብ ቅር አይበልህ።

ሙሉቀን፡- ይኼማ ዲክታተርሺፕ ነው። እኔ የፈለኩትን መናገር የምችል መሰለኝ። መጀመሪያ አድምጠኝና ወደኃላ እየሄድን እናስተካክለዋለን።

ጥያቄ፡-እንደዚያማ አይሆንም። ግድየለህም ቃለመጠይቁ አይበላሽም። አንተም ማስተላለፍ የምትፈልገው ምንም አይጓደልም። እኔ ስጠይቅ አንተ ከጥያቄው መሠረታዊ ሃሳብ ሳትወጣ መልስ ስጠኝ።

መሉቀን፡- ምን ነበር ጥያቄህ?

ጥያቄ፡-ይቀኑብኝ ነበር ያልከው ቅናቱ ከምን የመነጨ ነበር?

ሙሉቀን፡- የሚቀኑብኝ በሁሉ ነገር ነበር። በችሎታዬ፣ ወ/ሮ ደብረወርቅ በሚያመጡልኝ ከእነሱ ለየት ያለ ስጦታ፣ በቁመናዬ ጭምር ይቀኑብኝ ነበር።

ጥያቄ፡-ይኼ በቅናት የተጀመረ ነገር መጨረሻው ምን ሆነ?

ሙሉቀን፡- በመጨረሻ እነዚህ ልጆች በእኔ ላይ አድመው ልብሴን መስረቅ፣ መደብደብ ጀመሩ። እኔም በጣም ተበሳጨሁ። ንብረቴን ሲሰርቁ እጅ ከፍንጅ ስይዛቸው እነሱ ትላልቅ እና ጉልበተኛ ስለሆኑ ይደበድቡኛል። በመጨረሻ እኔም አፀፋውን መመለስ ፈለኩና የእነሱን ልብስ መውሰድ ጀመርኩ። “ሌባ ነው ንብረታችንን ሰረቀብን” ብለው ለዳይሬክተሩ ከሰሱኝ። እኔም ትክክለኛውን ነገር ለመናገር ብሞክርም የእነሱ ድምፅ ብዙ ስለሆነ የሚያምነኝ አጣሁና ከትምሕርት ቤቱ ተባረርኩ።

ጥያቄ፡- ወ/ሮ ደብረወርቅ ሰምተው ከመባረር ሊያድኑህ አልቻሉም?

ሙሉቀን፡- በኋላ ሰምተው ይሆናል። እኔ ግን ርቄ ስለሄድኩ የተፈጠረውን  ነገር አላውቅም።

ጥያቄ፡- ይህ በሚሆንበት ወቅት እድሜህ ስንት ይሆናል? ከዚያስ ምን ሆነ?… ወደ ሙዚቃው ዓለም ወደ ወሰደህ ጎዳና ይዘከን እንደምትሄድ እገምታለሁ።

ጥያቄ፡- ወ/ሮ ደብረወርቅ ሰምተው ከመባረር ሊያድኑህ አልቻሉም?

ሙሉቀን፡- በኋላ ሰምተው ይሆናል፡፡ እኔ ግን ርቄ ስለሄድኩ የተፈጠረውን  ነገር አላውቅም፡፡

ጥያቄ፡- ይህ በሚሆንበት ወቅት እድሜህ ስንት ይሆናል? ከዚያስ ምን ሆነ? ወደ ሙዚቃው ዓለም ወደ ወሰደህ ጎዳና ይዘከን እንደምትሄድ እገምታለሁ፡፡

ሙሉቀን፡- አዎ ትክክል ነህ&  ከዚህ በኋላ የምነግርህ ወደሙዚቃ ዓለም ከሄድኩበት እና በሩን ከከፈተልኝ የመጀመሪያው ገጽ ነው፡፡ ከትምህርት ቤቱ እንደወጣሁ አንድ ዘመድ ገዳም ሠፈር እንዳለኝ በወሬ ሰምቼ ነበርና ወደዚያው ሄድኩ፡፡ በዛው ሰሞን አንድ ቀን አቡነ ጴጥሮስ ኃውልት አካባቢ አትክልት ተራ ተብሎ በሚጠራው ሠፈር ሻይ ቤት ገብቼ  ስጠጣ አንድ ከእኔ በጣም የሚበልጥ ልጅ አርሞኒካ ይጫወታል፡፡ በጣም ጥሩ ችሎታ አለው፡፡ ጠጋ አልኩና ‹‹እኔ በድምጼ መዝፈን እችላለሁ& አንተ ለምን  በአርሞኒካ እያጀብከኝ አብረን አንጫወትም›› አልኩት፡፡ በዚህ ተስማማንና እኔ ስዘፍን እሱ በአርሞኒካ ሲያጅበኝ ሻይሊጠጣ የመጣው ሰው ሁሉ ማጨብጨብና ማድነቅ ጀመረ፡፡ የሻይ ቤቱም ባለቤት ገበያ ሲበዛ በጣም ደስ አለውና እዛው እንድንጫወትለት ለመነን፡፡ እኛም የምንበላው ፓስቴ እና ጮርናቄ እንደልብ ይሰጠናል& ሻይ ያለገደብ እንጠጣለን፡፡ በጣም ተደሰትን፡፡

ጥያቄ፡-ገንዘብ አይሰጣችሁም?

ሙሉ ቀን፡- አይመስለኝም ትዝ አይለኝም&ፓስቴና ሻይ ግን እንደልብ ነበር፡፡

ጥያቄ፡-ከዚህ ልጅ ጋር አብራችሁ ቀጠላችሁ ወይስ ይሔ ሁኔታ ሌላ በር ከፈተልህ?

ሙሉቀን፡-እንግዲህ ልጅነት ላይ ስለነበርኩ ዋናው የእኔ ትግል የቀን ምግቤን መሸፈን  ስለነበር በሱ በኩል ተሳክቶልኛል፡፡ በዛው ዓመት ጥምቀት በዓል ላይ ከዚሁ ልጅ ጋር በየታቦቱ እየዞርን እንጫወት ጀመር፡፡ ሰው ሁሉ በእጅጉ ተደነቀ፡፡‹‹ ይህ ልጅ ወደፊት ጥላሁንን የሚበልጥ ነው›› ተባለ፡፡ ተመልካቹ በሙሉ ገንዘብ ይሰበስብና ይሰጠናል በቃ ምን ልበልህ ተደሰትን፡፡ አንድ ቀን ጨዋታችንን ጨርሰን ሌላ አንድ አብሮን የዋለ ጓደኛዬን ልንሸንኝ በደጃች ውቤ ሠፈር  በኩል ስንሄድ የማየው መብራት ሁሉ ገነት የገባሁ መሰለኝ፡፡ ምሽት ስለነበር ሁሉም ቡና ቤቶች የተለያየ ቀለም ያላቸው መብራት አብርዋል፡፡ እኔ ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ነገር በሕይወቴ አይቼ አላውቅም፡፡ በቃ የገነት በር መሰለኝ፡፡ ለካ ገሃነም እሳት ነበር፡፡ እነዚህን ቡና ቤቶች አንድ ሱቅ ተጠግተን ስናይ ታኮ ጫማ ያደረጉ ሴቶች ወዲያ ወዲህ ይላሉ፡፡ ትዕይንቱ ሁሉ አስደሰተኝ፡፡ ቀስ ብለን ባለሱቁን፡- “ይኼ ምንድን ነው?” ብለን ጠየቅነው፡፡

“ይኽማ ፓትሪስ ሉሙምባ የሚባለው የታወቀ ናይት ክለብ ነው” አለን፡፡

የሚዘፍኑትስ ሙዚቀኖች እነማን ናቸው? አልነው፡፡

“ፈጣን ባንድ ይባላሉ” አለን፡፡ እዚህ የሙዚቃ ባንድ ውስጥ እነ አያሌው መስፍን እና ሌሎች የታወቁ ዘፋኞች አሉበት፡፡ አያሌው ዘፈን ይችላል፡፡ በቴሌቭዥን አይቼዋለሁ፡፡

ጓደኛዬ ቀበል አደረገና “እሱ ዘፈን በጣም ይችላል& አይቀጥሩትም?” የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡

“ባለቤቷ ወ/ሮ አሰገደች አላምረው ይባላሉ፡፡ በጣም ደግ ሴት ናቸው፡፡” አለን፡፡

እባክህ ወረቀት እንዳለህ ስጠኝና ደብዳቤ ልፃፍላቸው አልኩና በሰጠኝ ወረቀት ላይ “አሳዳጊ ወላጅ እና መኖሪያ የሌለኝ የደሃ ልጅ ነኝ መዝፈን ግን በደንብ እችላለሁ፤ እባክዎ ይቅጠሩኝ፡፡” ብዬ ፃፍኩና ለእሳቸው እንዲያደርስልኝ ለዘበኛው ብሰጠው ሰድቦ አባረረኝ እኔም ማልቀስ ጀመርኩ& እሱም በዱላ ከአከባቢው ሊያርቀኝ ሲል መጯጯሁን የሰሙት ወ/ሮ አሰገደች አላምረው ድንገት ሁኔታውን ተመልክተው

ምን  ሆኖ ነው የሚያለቅሰው ብለው ወደእኔ ሲጠጉ የሆነውን ነገር ነገርኳቸው፡፡ የዚህ ጊዜ ሁኔታዬን አይተው “ይሄማ ኤልቪስን አይደል እንዴ የሚመስለው?”አሉና በኃዘኔታ አባበሉኝ፡፡ እኔም እባክዎ ጥሩ ድምፅ አለኝ ይቅጠሩኝ አልኳቸው፡፡

ዘመድ የለህም ብለው ሲጠይቁኝ ሲሉኝ ከጎጃም አምጥተው ሜዳ ላይ ጣሉኝ ማንንም አላውቅም አልኩ፡፡ ከልባቸው አዘኑልኝና ስዩም የሚባለውን የኦርኬስትራውን ሃላፊ ኃላፊ  አስጠርተው እንዲፈትነኝ ነገሩት፡፡ እሱም የድምጽ ችሎታዬን ተመልክቶ በጣም በመደነቁ በኦርኬስትራው ታጅቤ እንድጫወት አደረገ፡፡

“ምግብማ ሞልቷል” የሚለውን የጥላሁንን ዘፈን ከእነአክሽኑ  በደንብ ሰለምችል& ዘፈኑን ስጨርስ ቤቱ በሙሉ ጭብጨባ በጭብጨባ ሆነ፡፡

የኦርኬስትራው ሙዚቀኞችም በጣም ከመደሰታቸው የተነሳ አለባበሴን አይተው ወዲያው ገንዘብ አዋጡልኝ፡፡

ጥያቄ፡-ምን ነበር በወቅቱ የለበስከው?

ሙሉቀን፡- አንድ ቤዥ ቀለም ቁምጣ ሱሪ ነበረችኝ በሷ ላይ ስቀደድ ቀይ ስለጥፍባት & እንደገና ስትቦጨቅ አረንጓዴ ስጥፍባት ማንነቷን ቀይራ ቀለሟም አያስታውቅም፡፡ ጫማ የለኝም ባዶ እግሬን ነኝ፡፡ ባለቤቷ ባዩት እና በሰሙት ነገር ተደንቀው አምጡት አሉና ራት እንድበላ ከሁሉም ዓይነት ቀረበልኝ፡ ልዩ ክፍል ተዘጋጀልኝና የግል ባኞ ቤት ተሰጠኝ፡፡ በዛው ምሽት እዛ ክለብ ውስት ከሚሰሩት ሴቶች 260 ብር ተዋጣና ልብስ ይገዛለት ተባለ፡፡ እኔ ይኼን የገንዘብ ልክ በቁጥር እንጂ በዓይኔ አይቼ አላውቅም፡፡

ጥያቄ፡-ያቺ ምሽት ናት ማለት ነው ህይወትህን የቀየረችው?

ሙሉቀን፡- ቆይ እንጂ ታሪኩ ብዙ ነው አታጣድፈኝ፡፡

ጥያቄ፡-ሌላውን ቀስ እያልን እደርስበታለን፡፡ የሕይወትህ መቀየር የታየበት ቀን ማለቴ ነው?

ሙሉቀን፡- ሕይወቴን የቀየረውማ ጌታ እየሱስ ነው፡፡

ጥያቄ፡-አሁን ወደ መንፈሳዊ ሕይወትህ ስላልገባን እሱ ይቆየንና ወደ ሙዚቃ ዓለም ለመግባት በር ከፋች የሆነውን ነው የጠየኩህ?

ሙሉቀን፡- ዋናው ነገር ወ/ሮ አሰገደች አላምረው ለእኔ አዝነው አስጠግተውና መኖሪያ ሰጥተው የመጀመሪያ ሕይወቴ እንዲቀይር የደረጉት እሳቸው ናቸው፡፡ ውለታቸውን ሳልመልስ መሞታቸው ይቆጨኛል፡፡

ጥያቄ፡-አርሞኒካ አብሮህ ይጫወት የነበረውስ ልጅ የት ደረሰ?

ሙሉቀን፡- በቃ ተለያየን& እሱም እንጀራ ፍለጋ ወደመራው ሄደ& እኔም በገጠመኝ ነገር ቀጠልኩበት፡፡

ጥያቄ፡-እስኪ ባጭሩ የፓትሪስ ሉሙምባ ናይት ክለብ፤ የፈጣን ኦርኬስትራ እና ያንተ ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር አጫውተን?

ሙሉቀን፡- ለጥቂት ቀናት በዱሮ ልብሴ መድረክ ላይ መጫወቴ ትዝ ይለኛል& ከዛ በኋላ ግን ሌላ ክለብ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ እኔ ወዳለሁበት መጉረፍ ጀመሩ፡፡ ዝናዬ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ተሰማ፡፡ ተወዳጅነቴ በአጭር ጊዜ ታወቀ፡፡

ጥያቄ፡-ወ/ሮ አሰገደች እንደልጅ ይመክሩህ ነበር?

ሙሉቀን፡- በጣም እንጂ ለምሳሌ ሰዎች መጠጥ ሰጋብዙኝ ገንዘብ ይሁንልኝ ለስላሳ መጠጥ አልፈልግም በል ይሉኛል፡፡ እኔም እንደዛ  እያልኩ ገንዘብ በገንዘብ ሆንኩ፡፡ ኑሮዬ በአፋጣኝ ተለወጠ፡፡ ሰው ሁሉ ወደደኝ፡፡ የሌላው ክለብ እየቀዘቀዘ የእኛ ክለብ እየሞቀ መጣ፡፡

ጥያቄ፡-ገንዘብ ስታገኝ አገር ቤት ያሉ እህቶችህን መርዳት ጀመርክ ወይስ እድሉን አላገኘህም?

ሙሉቀን፡- ብር አጠራቅሜ ከጎጃም እህቶቼን መጥተው ነበር፡፡ ስዘፍን አይተውኛል፡፡ ሴትዮዋም አህቶቼን ጠርተው “ይሄ ልጅ ከዚህ በኋላ እኔ ጋ ይኖራል በወር ዘጠና ብር እሰጠዋለሁ” አሏቸው፡፡ ዘጠና ብር በዚያን ጊዜ በጣም ብዙ ገንዘብ ነበር፡፡

ጥያቄ፡- የዛን ጊዜ እድሜህ ስንት ይሆናል?

ሙሉቀን፡- 11 ወይም 12 ቢሆነኝ ነው፡፡

አዲስ ሀሳብ፡- ከወ/ሮ አሰገደች አላምረው እና ከፈጣን ባንድ ጋር እንዴት ተለያያችሁ?

ሙሉቀን፡- የተለያዩ ኦርኬስትራዎች እኔን ለመውሰድ ጨረታ ገቡ፡፡ ሁሉም ያባብሉኝ ጀመር፡፡ የዛን ጊዜ በከተማው ታዋቂ ከሆኑት ባንዶች አንዱ የዙላ ባንድ ነበር፡፡ እነተሾመ ምትኩ የሚጫወቱት እዛ ነው፡፡ በፊት ተሾመ ሲጫወት በቴሌቭዥን አይቼዋለሁ፡፡ ጎበዝ ዘፋኝ ነው፡፡ የዙላ ክለብ ሲያግባባኝ “ይህቺ …….. በ90 ብር ባሪያዋ አደረገችህ አይደል እኛ 300 ብር እንከፍልሃለን ጥለሃት ወደ እኛ ና” ብለው አግባቡኝ፡፡ከዛምጠፍቼ ወደ ዙላ ባንድ ሄድኩ፡፡

ጥያቄ፡-ወ/ሮ አሰገደች ሲሰሙ ምን ተሰማቸው?

ሙሉቀን፡- እንደሰሙ እብድ ሆኑ& ኮንትራትና ውሉን አፍርሷል ብለው ፍርድ ቤት ከሰሱኝ፡፡

ጥያቄ፡-ተመለስክ ወይስ በዛው ቀረህ?

ሙሉቀን፡- አልተመለስኩም ከዙላ ጋር መስራት ጀመርኩ፡፡ ዙላ ክለብ ምግብና መኖሪያ ይሰጥሃል& ገንዘብ ግን አይሰጥህም፡፡ የገቡትን ቃል ሁሉ አላከበሩም፡፡ ውሸታቸውን ነው፡፡ ባለቤቱ በጣም መጥፎ ሰው ነው፡፡ እዛ የጫወቱት ሙዚቀኞች ደግሞ ሥራቸውን መጠጣት እና መስከር ብቻ ነው፡፡ ሥነ ሥርዓት የሚባል ነገር የለም፡፡ ኑሮው ሁሉ የዱርዬ ዓይነት ሆነብኝ፡፡ እኔም ደስተኛ አልነበርኩም፡፡ በዚህ መሐል ከፖሊስ ኦርኬስትራ አለማየሁ እሸቴ በሆነ ምክንያት ጥሎ ይወጣል፡፡ ኮሎኔል ታዬ ባለኬር እና ሻለቃ ወርቅነህ ዘለቀ ወደ እኔ መጥተው እኛ በወር 300 ብር እንከፍልሃለን ብለው ወሰዱኝና በሲቪል ደንብ ተቀጥሬ ፖሊስ ኦርኬስትራ ገባሁ፡፡

ጥያቄ፡-ለመሆኑ በገባህበት የሙዚቃ ባንድ ሁሉ የምትጫወተው ዘፈን የሌላ ሰው ነው ወይስ የራስህን መጫወት ጀመርክ?

ሙሉቀን፡- ከፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ በፊት ጋዜጠኛው ሰለሞን ተሰማ ለእኔና ለተሾመ ምትኩ የሰጠንን፡-

“የዘላለም እንቅልፍ እስከሚወስደኝ

ፍቅሬ የእኔ እጮኛ መቼም ያንቺው ነኝ”

የሚለውን ተጫውቻለሁ፡፡

ፖሊስ ሠራዊት ደግሞ “እምቧይ ሎሚ መስሎ” የሚለውን ተስፋዬ አበበ የሰጠኝ ዘፈኖች ለዝናዬ በር ከፋቾች ናቸው፡፡

ጥያቄ፡-መቼም ጊዜው ረዥም በመሆኑ ሁሉንም ማስታወስ ሊከብድ ይችል፡፡ ግን ከሌሎች ግጥምና ዜማ ፈጣሪዎች የተሰጡህ ትዝ ይሉሃል?

ሙሉቀን፡- አዎ! “ያላየነው የለም ሁሉንም አይተናል” የሚለውን ዘፈን ግጥሙን ሠይፉ ኃ/ማርያም ዜማውን ደግሞ አቡበከር እሸቴ ሰጥተውኝ በደንብ አድርጌ ተጫውቼዋለሁ፡፡ በወቅቱ በነበረው የዘፈን ምርጫ ፕርግራምም ከፍተኛ ተመራጭነት የያዙ ነበሩ፡፡

“እናቴ ስትወልደኝ መች አማከረችኝ&

የፊት ጉዴን ትታ እደግ ማሞ አለችኝ”

እና “ያ ልጅነት በጊዜያቱ ደስ ማለቱ” የሚለውም የተስፋዬ አበበ ድርሰት ነው፡፡

ጥያቄ፡-ለመሆኑ ከፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ ጋር እንዴት ከረማችሁ?

ሙሉቀን፡-ቆይ ልንገርህ የነሱንማ ጉድ፡፡ ፖሊሶች በጣም ዋሽተውኛል፡፡ የገንዘቡን  መጠን ከፍ አድርገው ሦስት መቶ ብር በወር ያሉኝ እኔን በእጃቸው ለማስገባት እንጂ ጭራሽ ውሸታቸውን ነበር፡፡

የክህደታቸው ክህደት ሁለት መቶውን ብር ቆርጠው አንድ መቶ ብር በወር ይከፍሉኝ ጀመር፡፡ ምነው እንዲህ ታደርጋላችሁ ነውር አይደል ወይ ብዬ ብጠይቅ የሁሉም ደመወዝ ከዚህ ያነሰ ነው& ለአንተ ነው ከፍተኛውን ደመወዝ የምንከፍለው ለወደፊቱ ደግሞ ይጨመርልሃል ብለው አግባቡኝ፡፡ እኔ ግን ከፍተኛ ቅሬታ ተሰማኝ፡፡ የፖሊስ ኦርኬስትራንም በጣም ጠላሁት፡፡ ሌላው የኦርኬስትራው ችግር ደግሞ ሠርግም ይሁን ሌላ ትልቅ ዝግጅት ከኛ ጋር ሲሰሩ የነበሩትን የኦርኬስትራው አባላት ቀን ሙሉ ሲሰሩ ውለው ማታ ዘብ ያቆሟቸዋል፡፡ ይኼ ሁሉ ተጨምሮ ነው የበለጠ እንድጠላቸው ያደረገኝ፡፡

ጥያቄ፡-በውስጥህ ሙዚቃ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊነትና ለሌላው ተቆርቋሪነት አለብህ ማለት ነው?

ሙሉቀን፡- አንተ ታሾፋለህ መሰለኝ?

ጥያቄ፡-ይኼ ማሾፍ ሳይሆን አንተነትህን መግለጽ መሰለኝ፡፡

ሙሉቀን፡- እውነትን ለመናገር እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ለሌላው መቆርቆርና ሰብዓዊነት በውስጤ ምንጊዜም አለ፡፡ እኔ ላይ ካልደረሰ ብዩ ሌላው ሲጠቃ ዝም ብዬ ማየት እልችልም፡፡ ይኼ ተፈጥዬ ነው፡፡ እስካሁንም አብሮኝ ይኖራል፡፡

ጥያቄ፡-ይኽንን እናሳጥረውና ወደሌላው ብንሸጋገር ምን ይመስልሃል?

ሙሉቀን፡-ለምንድነው ወደሌላ የምንሸጋገረው? ይኼንን እንጨርስ እንጂ፡፡

ጥያቄ፡- ሙሉቀን! ባንተ ህይወት ውስጥ ያለፍክበትን እያንዳንዱ ነገር የምንነጋገርበት ከሆነ እንኳን መፅሄት አንድ መፅሐፍም ላይበቃ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ነገር አጠር አድርገን መነጋገር ሊኖርብን ግድ ይላል፡፡ ግድ የለህም በእኔ ይሁንብህ ታሪኩ አይበላሽም ቁምነገሩንም አልስተውም፡፡

ሙሉቀን፡- እስቲ እናያለን ቀጥል ጥያቄህን?

ጥያቄ፡-ከፖሊስ ሠራዊት አርኬስትራ ጋር እንዴት ተፋታችሁ? ምን ያህል ጊዜስ አብረህ ሰራህ?

ሙሉቀን፡- ሁለት ዓመት ተኩል አካባቢ እንደሰራሁ አንድ ቀን የፖሊስ ዩኒፎርም እንደለበስኩ ወጥቼ በዛው ቀረሁ፡፡

ጥያቄ፡- ለመሆኑ መለዮ ለባሽፖሊስ ሆነህ ነበር እንዴ እኔ እኮ የመሰለኝ በሲቪል ደረጃ የሚያሰሩህ መስሎኝ

ሙሉቀን፡-  የፖሊሶች ትልቁ ችግራቸው መዋሸት ነው፡፡ውሸታቸው ከዛ ይጀምራል፡፡ ተቀጥሬ ትንሽ እንደቆየሁ ዩኒፎረም መልበስ አለብህ ተባልኩ፡፡

ጥያቄ፡- ማዕረግህ የሚወሰነው በምን ነበር በደመወዝ ወይስ በምትሰራው ሥራ?

ሙሉቀን፡- እነሱ እባክህ እደፈለጋቸው ነው፡፡ ይህንን እንተወው፡ የያኔዎቹ አሁን ስለሌሉ ወቀሳው ምንም ነገር አያሻሽልም እንተወው ፡፡

ጥያቄ፡-እሺ እውነትህን ነው እዚህ ላይ ይኸን እናቁምና ወደሌላው እንለፍ፡፡ ከዚያ በኋላ ያለውን በሙዚቃ  የነበረህን ቆይታ ባጭሩ አጫውተን ?

ሙሉቀን፡- ይኽ እኮ ባጭሩ የምትለው ነገር ነው እኔ የማልስማማበት፡፡የእኔ ሕይወት እና በሙዚቃ ዓለም የሰራሁት ታሪክ በአጭሩ የሚገለጽ አይደለም፡፡

ጥያቄ፡-እሺ በአጭሩ ሳይሆን በረዥሙ አጫውተን?

ሙሉቀን፡- እንደዚያ እየተስማማን ብንነጋገር ይሻላል፡፡ ከዚያ በኋላ ፒያሳ ገብረተንሳይ ኬክ ፊት ለፊት ያለው “ቬኑስ ክለብ’’ ገባሁ፡፡ በወቅቱ በጣም ታዋቂና ተወዳጅ ክለብ ነበር፡፡ ከቬኑስ ጋር ለጥቂት ጊዜ ሰርቼ ወደ ዋቢሸበሌ ገበሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ጥቂቶች ተሰባስብንና “ኢክዌተርስ” በሚል ባንድ ጊዮን ሆቴል እንሰራ ጀመር፡፡ እንግዲህ የእኔ ሕይወት ሙሉ በሙሉ የተለወጠው የዛን ጊዜ ነው፡፡ እነ “ሠውነቷ ናኑ ናኑ ናዬ! አገሯዋሳ መገና” ሁሉ የወጡት የዛን ጊዜ ነው፡፡የሠይጣን ዘመን ነበር ጊዜው፡፡

ጥያቄ፡-እዚህ ላይ አንዴ ላቋርጥህና ለምን እንዲህ ልትል ቻልክ?

ሙሉቀን፡- እንደዚህ ምን?

ጥያቄ፡-ዘመኑ የሠይጣን ነበር ማለትህ ነዋ፡፡ እንደኔ ከሆነ ወርቃማ ዘመንና ዘመናዊ ሙዚቃ በሃገራችን ያበበበት እና እንደ አንተ ዓይነቱ ድምፃዊ የፈራበት ወቅት ነበር፡፡

ሙሉቀን፡- እሱ ላንተና ለመሰሎችህ ነው፡፡ ለእኔ ሠይጣን ለጉሞኝ እንደፈለገው ሲጋልበኝ የነበረበት ወቅት ነበር፡፡ አንተ የፈለከውን በል እኔ‹‹የሠይጣን ዘመን›› እለዋለሁ፡፡

ጥያቄ፡-አንተ ዘፋኝ በመሆንህ ነው የሠይጣን ዘመን ያልከው?

ሙሉቀን፡- አዎ! ዘፈን የሠይጣን ነው፡፡ዘፋኝ ገነት አይገባም ይላል መፅኃፉ፡፡

ጥያቄ፡-እሱን ወደኋላ እንመጣበታለን፡፡ እስቲ በዚያን ወቅት ታዋቂ ስለነበሩት አርቲስቶች ትንሽ አጫውተን?

ሙሉቀን፡- በወቅቱ ታዋቂ የነበርነው እኔ ምኒሊክ ወስናቸው እና ጥላሁን ገሠሠ ነበርን፡፡

ጥያቄ፡- ለመሆኑ የምታደንቀውና ላንተ ጥሩ ምሳሌ የሆነህ ድምፃዊ ማነው?

ሙሉቀን፡- እኔ በሀገራችን ከተፈጠሩ ድምፃውያን ውስጥ በጣም የማደንቀው በአንደኛ ደረጃ ምኒሊክ ወስናቸውን ሲሆን ከዚያ ቀጥሎ ተሾመ ምትኩን እና መሀሙድን ነው፡፡

ጥያቄ፡- ጥላሁንን የረሳኸው መሰለኝ፡፡

ሙሉቀን፡- አልረሳሁትም፡፡ ጥላሁን  ለእኔ ዘፋኝ አይደለም፡፡ ድምፅ እንጂ ታለንት የለውም፡፡ የመድረክ ብቃትም የሌለው ሰው ነው፡፡ እኔ ጥላሁን ገሠሠን እንደታላቅ አርቲስት ቆጥሬውም አላውቅም አይደለምም፡፡

ጥያቄ፡- ሙሉቀን ምን ማለትህ ነው? ጥላሁን በሠላም ጊዜ ሕይወትን፤ፍቅርን፤ደስታና ኃዘንን በዜማው እና በዘፈኑ የገለፀ ድምፁ በሁሉም ዘንድ የተወደደ ዝነኛ እና ብቸኛ አርቲስት ነው ፡፡ ለዚህም የረጅም ጊዜ መልካም አገልግሎቱ ከተለያዩ ሽልማቶች አንስቶ የክብር ዶክትሬት እእስከማግኘት በቅቷል፡፡ ታዲያ አንተ አርቲስት አይደለም ብለህ ስትል ይኽን ታላቅ ሰው ማቃለል አይሆንም?

ሙሉቀን፡- አየህ ስህተቱ የሚጀምረው እዚህ ጋ ነው፡፡ ሙዚቃ መስማት እና ማወቅ በጣም የተለያዩ ነገሮች ናችው፡፡ እናንተ ሙዚቃ በጆሯችሁ መስማት ነው የምታውቁት እኔ ደግሞ ሙዚቃን በደንብ መለየት እችላለሁ፡፡ ከዚህ ጋር አብሮ መታየት ያለበት ደግሞ የመድረክ አጠቃቀም እና ብቃት ነው፡፡

ጥያቄ፡-ምን ማለት ነው እስቲ ግልፅ አድርግልን?

ሙሉቀን፡- አታቻኩለኛ!…..ልነግርህ እኮ ነው! የመድረክ ብቃት ማለት አንድ አርቲስት በመድረክ ሲጫወት ከሚያጅቡት ሙዚቀኞች ጋር መናበብና መደማመጥ ከእነሱም ጋር ድምፁን አስማምቶ መጫወት ማለት ነው፡፡

ጥያቄ፡-ታዲያ ጥላሁን በዚህ በኩል ችሎታ የለውም ነው የምትለኝ ? ቅሬታስ ያሰማ የሙዚቃ  አጃቢስ አለ?

ሙሉቀን፡- አሁን አላስጨረስከኝም!!!!! ጥላሁን የጉልበት ዘፋኝ ነው፡፡ ያቺ በተፈጥሮ የተሰጠችውን ድምፅ በጣም ስለሚኩራራባት አጃቢዎቹን በጣም ይንቃል:: በአብዛኛው ከሙዚቃ ውጭ ወደፊት ወይም ወደኋላ በመሄድ አጃቢዎቹን በጣም ያስጨንቃል ግራ ያጋባል፡፡ እሱ የሚያየው አፉን መክፈቱን ነው እንጂ የአጃቢ ሙዚቀኞቹን ምቾት አይጠብቅላቸውም፡፡ ይኼ ደግሞ ብዙ ጊዜ ስሞታ አስከትሎበታል፡፡ ግን የሚያዳምጥ የለም፡፡ ጥላሁን.. ጥላሁን ስለተባለ ብቻ ሁሉም ለእሱ ያደላል የአጃቢ ሙዚቀኞቹን ስሞታ የሚሰማ የለም፡፡ እነሱም ሥራችንን በዚህ ምክንያት እናጣለን በማለት እንደምንም እሱን ለመከተል ይገደዳሉ፡፡

ጥያቄ፡-ለመሆኑ ከጥላሁን ጋር በሙያችሁ የነበራችሁ ግንኙነት እንዴት ነበር?

ሙሉቀን፡- እደማንኛውም ዘፋኝ አብሬው ሰርቻለሁ፡፡ ግን የመድረክ ብቃቱን አልወድለትም ነበር፡፡ መቼም ይኽንን በምልበት ጊዜ ብዙዎች ቅር እንደሚሰኙ ይገባኛል፡፡ ሁሉም እሱ ላይ የአምልኮ ወይም ካለሱ በስተቀር ግሩም ዘፋኝ የለም የሚል እምነት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እኔ ግን በሙያው ውስጥ  ስለነበርኩ ያለምንም ይሉኝታ ነው ስለሁሉም የምናገረው፡፡ ስለዚህ አሁንም ደግሜ ጥላሁን ድምፅ እንጂ አርቲስት የሚለውን ሥም የሚያሟላ ታለንት የለውም የምለው፡፡ ደግሞም ትክክል ነኝ፡፡

ጥያቄ፡- -ለመሆኑ ከድምፃዊነት ባሻገር ሌላ  ምን ችሎታ አለህ ?

ሙሉቀን-የእኔ ችሎታ ጥቂት አይደለም፡፡ ጥምር የሆነ የብዙ የሙዚቃ አይነቶች ባለቤት እና ችሎታውም ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ የእኔን ያህል በሙዚቃው አለም ብዙ እውቀት ያለውም በሃገሪቱ አልተፈጠረም አሁንም የለም ይሄንን በማስረጃ ለማረጋገጥ ሙዚቃ እፅፋለው፤ ግጥም እደርሳለሁ ፤ሙዚቃና ዜማውን ኮምቦዝ አደርጋለሁ ፤ድራም በደንብ እጫወታለሁ በዚህ ላይ ደግሞ ድምፃዊ ነኝ፡፡ እስቲ እነዚህን ሁሉ ችሎታዎች የያዘ አንድ አርቲስት ጥራልኝ? ዛሬ እኮ የጠጅ ቤት አዝማሪ ሁሉ አርቲስት እየተባለ የሚጠራበት ዘመን ላይ ደርሳችኋል፡፡

ሙሉቀን-የእኔ ችሎታ ጥቂት አይደለም ጥምር የሆነ የብዙ የሙዚቃ አይነቶች ባለቤት እና ችሎታውም ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ የእኔን ያህል በሙዚቃው አለም ብዙ እውቀት ያለውም በሃገሪቱም አልተፈጠረም አሁንም የለም ይኼንን በማስረጃ ለማረጋገጥ ሙዚቃ እፅፋለው ፣ግጥም እደርሳለሁ፣ሙዚቃና ዜማውን ኮምቦዝ አደርጋለሁ፣ ድራማ በደንብ እጫወታለሁ በዚህ ላይ ደግሞ ድምፃዊ ነኝ፡፡ እስቲ እነዚህን ሁሉ ችሎታዎች የያዘ አንድ አርቲስት ጥራልኝ? ዛሬ እኮ የጠጅ ቤት አዝማሪ ሁሉ አርቲስት እየተባለ የሚጠራበት ዘመን ላይ ደርሳችኋል፡፡

ጥያቄ፡- ደርሰናል በል እንጂ ሙሉቀን… አንተን ለምን አትጨምርም? በዚህ ዘመን ላይ ያለህ ሰው እኮ ነህ፡፡

ሙሉቀን- እኔማ በደህናው ጊዜ አመለጥኩ ከአምላኬ ጋር ተገናኘሁ ያንን የሠይጣን ኑሮ አሽቀንጥሬ ጣልኩት ጌታ የተባረከ ይሁን! ስለዚህ ይኽንን ያልኩት የለሁበትም ለማለት ነው፡፡

ጥያቄ፡- የጌታን ጉዳይ ወደኋላ እንመለስበታለን፡፡እስቲ በሙዚቃ ዓለም ውስጥ የሰራኽውን እና ታላቅ ተግባር ነበር የምትለውን ከምታስታውሰው አንኳሮቹን በአጭሩ አተጫውተን?

ሙሉቀን -የኔ ታሪክ እና ሥራ በአጭሩ የሚገለፅ አይደለም፡፡ በሙዚቃ አለም የሠይጣን አገልጋይ ሆኜ ብዙ ሥራዎችን ሰርቻለው፡፡ ለምሳሌ ያህል ታላቁ የሬጌ ሙዚቃ አባት ቦብ ማርሊ አብሬው እንድጫወት ጠይቆኛል፣ አሜሪካዊው  ስመጥር  አርቲስት ስቲቪ ወንደር አብሬው እንድጫወት ስምንት የዘፈን ግጥሞችን ልኮልኝ ወደዚህ ወደአሜሪካ ስመጣ አንዱም እውን ሳይሆን ጌታ ቀድሞ የሱ አገልጋይ እንድሆን መረጠኝ ፡፡ በእነዚህ ዓለም አቀፍ ታዋቂ ምርጥ አርቲስቶች የተጋበዝኩ ብቸኛ ኢትዮጵያዊ አርቲስት እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ቦብ ማርሊም በአጋጣሚ ሞተ፡፡ ከስቲቭ ወንደርም ጋር ላደርገው የነበረውን ጨዋታ ተውኩት፡፡ አሁን ሳስበው ጌታን ለመቀበል ይኽን ያኽል መዘግየቴ እንዴት ያሳዝነኛል መሰለህ? ከሁሉም በላይ በጌታ ጥላ ስር መጠለል ምነኛ መታደል እንደሆነ ያወቅኩት በኋላ ነው፡፡  ጌታ የተመሰገነ ይሁንና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁሉንም ሠይጣናዊ ሥራ ከእኔ ከልጁ ላይ አስወግዶ የሱ አገልጋይ ስላደረገኝ አመሰግነዋለሁ ፡፡

ጥያቄ፡- ለመሆኑ ጌታን ከመቀበልህ በፊት የሰራኸው ምን ኃጢያት አለና ነው ይኽን ያኽል ዘፋኝ በመሆን ራስህን  የምተኮንነው ?

ሙሉቀን – ዓለማዊ በነበርኩበት ጊዜ መጠጡ፣ ሲጋራው ፣ሐሺሹ፣ ሴቱ ምን የሚቀር ነገር አለ ብለህ ነው? ሁሉም ነገር  ከእግዚአብሄር መንገድ የራቀ ፍፁም የሰይጣን ሥራ ነበር:: ለምሳሌ እኔ ሦስቱንም ልጆቼን ያፈራሁት ከሦስት የተለያዩ ሴቶች ነው ይኼ እንግዲህ ከአንድ ያለመርጋትና ሁሉንም ወይም ያዩትን ከመፈለግ የሚመነጭ ነው ዘመናዊነት ነው ከዚህ የበለጠ ምን ኃጢአት አለ?

ጥያቄ፡- በጋብቻ ወይም በፍቅር ጊዜ ያለመስማማት ሲኖር ሁለቱም ወገኖች ይለያያሉ፤ታዲያ ከሌላዋ ወይም ከሌላው ጋር ፍቅር መጀመር ባንተ የተጀመረ አይደለም ምኑን ነው እንደ ኃጢአት የቆጠረከው?

ሙሉቀን – አንተ  የምታየው እነደዚያ አድርገህ ነው፡፡ እኔ ግን  የማየው በጌታ ፍቃድ ሥር ተጠልዬ ነው፡፡ ህጉንም ከማክበር አኳያ ነው በአለማዊ ህይወቴ የሠራኋቸው ነገሮች በሙሉ ይቆጩኛል፡፡ ወደ ኋላ ሄጄ አላስተካክለውም እንጂ ሁሉም ኃጢአት ነበሩ፡፡

ጥያቄ፡-በዘፈንህና በመረዋ ድምፅህ አድማጮችን ማስደሰትህ ሁሉ ይቆጭሃል?

ሙሉቀን፡- በጣም እንጂ ቢቻለኝ በዓለማዊ ህይወቴ የሠራኋቸው ዘፈኖች እና ሙዚቃዎች ሁሉ ተሰብስበው ቢቃጠሉና እኔን በዓለማዊነቴ የሚያስታውሱኝ ነገሮች ሁሉ ቢወድሙ ደስ ይለኛል… ግን ከቁጥጥር ውጪ ነው ምንም ማድረግ አልችልም፡፡

ጥያቄ፡- አንተ ብቻ ሳትሆን ቀድሞ አርቲስት ሆነው ከግዜ በኋላ ደግሞ ወደመንፈሳዊው ዓለም የገቡ ብዙ ድምፃዊያን አሉ፡፡ እንዳንተ ስላለፈው ህይወታቸው በመቆጨት ይኽን አጥፉልኝ፣ ይኽን ደምስሱልኝ፤ ሰብስባቸሁ አቃጥሉልኝ ሲሉ አይሰሙም፡፡ ድምፃቸውን አጥፍተው በመንፈሳዊነታቸው ይተጋሉ ፡፡ያንተ ግን የተለየ ሆነብኝ ለምን ባለፈው መቆጨትህን ትተህ አሁን በያዝከው ደስተኛ አትሆንም ? የድሮውን እያሰብክ የምትናደድና የምትቆጭ ከሆነ ተፈጥሮህ ሌላውን ፍጡር የሚጠላና ተናዳጅ ያደርግሃል፡፡ ለጤናህም ደግ አይመስለኝም፣ ለምን ድሮ በሰራኸው ሥራ ትፀፀታለህ ያለፈው አልፏል ስለወደፊቱ ህይወትህ አታስብም ?

ሙሉቀን – እኔ የምለው የገባህ አይመስለኝም፡፡በተለያየ መስመር ነው እየተጓዝን ያለነው፡፡ በደንብ ከተረዳኽኝ እኔ የምለው ጌታን ቀድሜ ያለማግኘቴ ይቆጨኛል፤ ያለፈው ሥራዬን አልወደውም፤ ስሜም በሱ እንዲነሳ አልፈልግም ባይ ነኝ ስለሌሎቹ ግን አያገባኝም፡፡

ጥያቄ፡- ሙሉቀን በአንድ በኩል የቀድሞው ስራዬን በሙሉ ሰብስቤ ባቃጥለው እመርጣለሁ ትላለህ ሌላ በኩል ደግሞ አንተ የጠላኸውንና የጣልከውን ስራህን ሌሎች አንስተው ነፍስ ሲዘሩበት በጣም ቅር ይልሃል፡፡ ሙግት የገጠምክበትም ወቅት አለ ይህንን ለመግፅ እንደ ምሳሌ የማነሳው በአንድ ወቅት ብዙአየሁ የተባለ ድምፃዊ የአንተን ዘፈኖች በመጫወቱ አሜሪካ ድምፅ ሬድዮ ላይ ለቃለ መጠይቅ ቀርበህ ዘፋኙን እንዳይሆን እንዳይሆን ኮንነኸዋል፡፡ አንተ የጣልከውን ሌላው አንስቶ ነፍስ ቢዘራበት ምናለበት? ይሄ ዘፈኔ ተሰብስቦ ይቃጠልልኝ ከሚለው አባባልህ ጋር ፍፁም የሚጋጭ አይደለም?

ሙሉ ቀን፡- በፍፁም ተሳስተሃል፡፡ እኔ ስርቆት እና ውሸት  አልወድም፡፡ የቀድሞ ሙያዬን ልጥላው እንጂ ሥራዎቼን በሙሉ የእኔ ናቸው፡፡ አስፈላጊ ከሆነ በጨዋነት እኔን መጠየቅ ሲቻል ሌብነትን ምን አመጣው ነው ያልኩት፡፡ ለምንስ ሰርቆ እና የራሱ አስመስሎ ለሕዝብ ያቀርባል፡፡ በእኔ ሥራዎች ላይ እኔ ብቻ ሳይሆን በግጥም በዜማ እና በቅንብር የተሳተፉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ግን ይኼ ልጅ የእኔን ስራዎች በሲዲ ሲያሳትም አንዳችንም አናውቅም፡፡ ገበያ ላይ ውሎ የግል ተጠቃሚ ከሆነ በኋላ  ነው የሰማሁት፡፡ ይኼ መቼም ማንም ይፍረደኝ ደረቅ ዓይን ያወጣ ሌብነት ነው፡፡ ለዚህ መጥፎ ተግባሩ እንጂ ጥቅም ፈልጌ አይደለም አደባባይ የወጣሁት፡፡

ጥያቄ፡- አንድ ዘፈን እኮ ሃያ ዓመት ካለፈው የሕዝብ ይሆናል፡፡ይኸንንም በማስረጃ  ለማቅረብ የብዙ ዘፋኞች የቀድሞ ሥራ በአዲሱ ትውልድ  ድምፃውያን  እየተሻሻለ ወይም እንዳለ በዘመናዊ እና በተራራቀ መሣሪያ ተቀናብሮ ተሰርቷል፡፡ የአሰፋ አባተ፤የጥላሁን ገሠሠ፤ የተፈራ ካሳ፤ የሌሎችም ጭምር የቆየና ተወዳጅ ስለነበረ አዲሱ ትውልድ እንደገና አሳምሮና አሻሽሎ አቅርቦታል፡፡ ያንተ ሥራ ብቻ ለምን ልዩ ሆነ? ሕይወትህ ለማይኖርበት ሥራ ምን አስጨነቀህ?

ሙሉቀን፡- አየህ አንተ አሁን የሌባ ሽርክ ነህ ማለት ነው፡፡ ሌቦችን እንደማጋለጥ አንተ ለእነሱ ትከራከራለህ፡፡ ሃያ ዓመት ያለፈው ንብረት እንዲዘርፍ የሚፈቅድ ሕግ አላውቅም፡፡ ከተቋቋመ ሃያ ዓመት ያለፈው ባንክ ይዘረፍ የሚል ሕግ የለም፡፡

ጥያቄ፡-እነዚህ ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ባንክ እና ዘፈንን ምን አገናኘው? ለነገሩ ያንተ ትክክል ሊሆን ስለሚችል ይኽንን እንለፈውና ወደ ሌላው እንሸጋገር፡፡ ባንተ እምነት ዘፋኝ አይፀድቅም የምትል ይመስላል ይኼ እውነት ነው?

ሙሉቀን፡- እኔ ብቻ አይደለሁም ይህን የምለው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ይህን ያረጋግጣል፡፡ ዘፋኝ በፍጹም ገነት አይገባም፡፡ ቤቱ ሲዖል ነው፡፡ የሰይጣን ማሳደጊያ ጡጦው ዘፈን ነው፡፡

ጥያቄ፡-ይኼ ሁሉ ወፈ ሠማይ ድምፃዊ የገነትን በር አያይም ነው የምትለው?

ሙሉቀን፡- አጠያየቅህ እንኳን የማሾፍ ይመስላል፡፡ እኔ ግን የምነገርህ እውነቱን ነው፡፡

ጥያቄ፡- ከዚህ በፊት በሞት የተለዩን አርቲስቶች በሙሉ (……) ሲዖል ወርደዋል ነው የምትለው?

ሙሉቀን፡- እነሱ በአሁኑ ጊዜ በፈፀሙት ኃጢአት ቅጣታቸውን በሲዖል እየተቀበሉ መሆኑን አረጋግጥልሃለሁ፡፡

ጥያቄ፡-ይሕ አባባል ፀሐፊዎች ማለቴ ደራሲያንን፤ አዲስ ነገር ለመፍጠር የሚጥሩ ሳይንቲስት ፈላስፋዎችን ያጠቃልላል?

ሙሉቀን፡- ከፈጣሪ ጋር ያልተገናኘ እና መንፈሳዊነትን መሠረት ያላደረገ ነገር ሁሉ ዋጋ የሌለው ነው፡፡ እንደ እናንተ ያለው መጽሔት ፤ጋዜጣ፣ ሬዲዮ እያለ ኃጢአት የሚያራባው ሁሉ መግቢያው ሲዖል ነው፡፡ የሁሉ ነገር መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስና የጌታ ቃል ብቻ ነው፡፡ እሱን ማንበብና መፀለይ በየዕለቱ ከጌታ ጋር መገናኘት ብቻ ነው የሚያድንህ፡፡ አንተም ካሁኑ ብትነቃና ብታስብበት መልካም መሰለኝ፡፡

ጥያቄ፡-ተው እንጂ ሙሉቀን እንደዚህ እያልክማ ልታስፈራራኝ አትችልም፡፡

ሙሉቀን፡- ምንድን ነው የማስፈራራህ?

ጥያቄ፡-ሲዖል ትገባለህ እያልክ ነዋ!

ሙሉቀን፡- እኔ አኮ አይደለሁም ይኽን የምለው ‹‹ቃሉ ነው›› የሚናገረው፡፡ በግዜ ነቅተህ ጌታን ተቀብለህ ዳግም ካልተወለድክ እዚያው የሰይጣን ቤት ገቢ ነህ፡፡ ይኼንን ካሁኑ ስነገርህ እያስጠነቀቅሁም እየመከርኩህም መሆኑን እወቅ፡፡

ጥያቄ፡-እኔ እኮ ከልጅነቴ ጀምሮ ቤተክርስቲያን ቤት ያደግኩ ጥሩ ክርስቲያን ነኝ ክርስትናም ተነስቻለሁ፡፡

ሙሉቀን፡- እሱ ጌታን መቀበል አይደለም የክርስትና ስም መቀበል እንጂ፡፡

ጥያቄ፡-ክርስቲያን መሆንና ጌታን መቀበል ማለት ታዲያ ምን ማለት ነው?

ሙሉቀን፡- ክርስቲያን መሆን እና ጌታን መቀበል ማለት ‹‹እንደ እኔ መሆን›› ማለት ነው፡፡

ጥያቄ፡- ይኼንን የውይይታችንን መስመር እንኳን አልወደድኩትም፡፡ አንተንም እኔንም ከሌሎች የተለያየ  የኃይማኖት መስመር ካላቸው ጋር ሊያጋጨን ወይም አንዳንዶችን ቅር ያሰኝ ይሆናልና ይኼንን በዚሁ አቁመን ወደሌላ ብንሄድ ምን ይመስልሀል?

ሙሉቀን፡- አንተ ጥያቄህን በትዕዛዝ ማድረግ ትወዳለህ፡፡እኔ መናገር የምፈልገውን ‹‹ይኽን እንለፈው›› ትለኛለህ፡፡ ይኼንን አልወደድኩልህም፡፡

ጥያቄ፡-መልካም እስኪ በዚህ ጉዳይ ላይ የምትናገረው ካለ  ባጭሩ ንገረኝ?

ሙሉቀን፡- በምኑ ላይ? አንተ ሁሉንም ነው ይኼን እንለፈው የምትለው፡፡

(…………….)
ጥያቄ፡- በኃይማኖት እና በዘር ጉዳይ መወያየት ችግር እንዳለዉ አዉቃለዉ፡፡ እኔ የኃይማኖት አክራሪ እና እንዳንተ በፀሎት በየዕለቱ የምተጋ አይደለሁም፡፡ ገነት እና ሲኦል የሚባል ነገር ካለም ገነትን እመርጣለሁ፡፡

ሙሉቀን – አይመስለኝም፡፡ እንደስራህ ከሆነ የገነትን በር የምታይ አይመስለኝም ለአንተ እና ለመሰሎችህ የተዘጋጀ ቦታ ኣላችሁ፡፡

ጥያቄ፡- አባት ሆይ ለሰሩት ኃጥያት ይቅር በላቸዉ የሚያደርጉትን አያዉቁምና ያለዉን የጌታን ቃል እንዴት ታየዋለህ? እኔንና መሰሎቼንም ለይቅርታ ማቅረብ እንጂ እንዳንተ ካለ ከኃይማኖት ሊቅ ሊነገር የሚገባዉ ቃል ይመስልሃል?

ሙሉቀን ፡- እኔ ተናግሬያለሁ፤ ቀኑ ቀርቧል እላለሁ፡፡ መፍትሄዉ ጌታን መቀበል ብቻ ነዉ፡፡

ጥያቄ ፡- እንግዲህ እኔ ወደ ሌላዉ የዉይይታችን አርዕስት ልገባ ነዉ፡፡ ይኼኛዉ ያማረብን አይመስለኝም፡፡

ሙሉቀን – አንተ ነህ እንጂ የማታዉቀዉን ነገር እየተናገርክ ያስቸገርከኝ፡፡ ዉይይታችንማ ስለጌታ እየሱስ ስለሆነ ምን ጥፋት አለዉ፡፡ እኔም መቀጠል የምፈልገዉ ቢኖር እሱን ነዉ፡፡ ሌላ አለማዊ ነገር እየደነቀርክ የረሳሁትን እና የጠላሁትን ነገር አታስታዉሰኝ፡፡

ጥያቄ ፡- አየህ ሙሉቀን የቃለ መጠይቁ ዋና አላማ በአጠቃላይ በአንተ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን ሆኖ ካለፈዉ ሕይወትህ ጋር በተገናኘ በከያኒነትህ ያሳለፍከዉን ለአድናቂዎችህ ለመንገርና እንዴት ወደ መንፈሳዊ ሕይወት እንዳመራህ የሚናገር ነዉ፡፡

ስለዚህ አንዳንድ ቀደም ብዬ ያልነካኋቸዉን ነገሮችና ካንተም መልስ ያላገኘሁበትን ጉዳይ መንካት እፈልጋለሁና ብትፈቅድልኝ ምን ይመስልሀል?

ሙሉ ቀን – እስቲ ልስማቸዉና ከተመቹኝ እመልስልሀለሁ፡፡

ጥያቄ ፡- በአንድ ወቅት የቀድሞ የሙያ አቻዎችህ ያለህበትን ሁኔታ ሰምተዉ በስምህ ኮንሰርት በማዘጋጀት ለኑሮህም ድጎማ ለማድረግ ጠይቀዉህ ነበር ይባላል፡፡ አንተ ግን አልተቀበልከዉም ለምን ይሄን አደረክ? እነሱ ከልባቸዉ አንተን ለመርዳት ፈልገዉ በመልካምነት መንፈስ ያቀረቡትን ጥያቄ ለምን አጣጣልከዉ?

ሙሉቀን – ይኼ አንተ እንደምትለዉ ለማጣጣል ፈልጌ አይደለም እንቢተኛ የሆንኩት፡፡ በእርግጥ ጥያቄ ማቅረባቸዉ እዉነት ነዉ፡፡ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ስለእኔ የህይወት ታሪክ መፅሀፍ ለመፃፍ ፤ ፎቶዬን ሙዝየም ዉስጥ ለማስቀመጥ ፤የቀድሞ አለማዊ ስራዎቼን አሰባስቦ እንደገና አሳትሞ ለሕዝብ ለማቅረብ  የጠየቁኝ ብዙ ሰዎችና ድርጅቶች አሉ፡፡ እኔ ግን ያለ ጌታ ፈቃድ የምሰራዉ ነገር ስለሌለ “ልፀልይበት ወይም ጌታን ላማክር” በሚል አቆየዉና ዉሳኔዬን አሳርፋለዉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች የጌታን ፈቃድ ስላላገኙ ልቀበለዉ አልፈለኩም፡፡

(…………….)

ጥያቄ፡-  ሙሉቀን ብዙ ጊዜ የቀድሞዉ ዓለማዊ የምትለዉን የሙዚቃ ስራህን “ተሰብስቦ ይቃጠልልኝ” ትላለህ፤ እንደገና ደግሞ ሌላዉ ስራህ እንዳይሞት ባለዉ ፍቅር ተነሳስቶ ኣሻሽሎ ይጫወተዋል የዚህ ጊዜ ደግሞ “ተዘረፍኩ ፤ተቀማሁ” ትላለህ፡፡ እነዚህ ሁለት ኣባባሎች እርስ በእርስ አይቃረኑም? ለጠላኸዉ ነገር ለምንስ ቦታ ትሰጠዋለህ?

ሙሉ ቀን:- አንተ በጭራሽ ከመስመር ዉጪ ነህ:: አየህ በመስረቅ እና በማስፈቀድ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ ያ ሰው የእኔን ስራ ሰርቆ ነዉ ለግል መጠቀሚያ ያደረገዉ፡፡ (…..)ን ደግሞ (“…….”) ማለት ተገቢና ዳግም እንዳይሰርቅ ያደርገዋል፡፡ ለዚህ እንጂ እኔ ከእሱ ምንም ፈልጌ አይደለም፡፡ አጭበርባሪ ነዉ፡፡ በዚሁ ላይ ደግሞ አበላሽቶ ነዉ የተጫወተዉ፡፡

ጥያቄ፡-ብዙ አድማጮች እንደነገሩኝና እኔም እንዳዳመጥኩት በብዙአየሁ ያቀረበዉ ያንተዎቹ የድሮ ዜማዎች በዘመናዊ መሳሪያ ጥበብ እጅግ አምሮባቸዉ ሰምተናል፡፡ እንዴት አበላሸዉ ትላለህ?

ሙሉ ቀን – አንተ እና አንተ ያናገርካቸዉ አድማጮች የሙዚቃ ምንነትን በደምብ የምታዉቁ አትመስሉም፡፡ አንተ ካነጋገርካቸው  ወጣ ብለህ ሙዚቃ እና የድምፅ ጥራትን በደንብ የሚያውቁ አነጋግር፡፡ እነሱ እውነቱን ይነግሩሃል፡፡ ይኼ ልጅ ከ(…..ነቱ)ባለፈ የድምፅ ችሎታም የለዉም፡፡ ሙልጭ ያለ (….) ነዉ፡፡

ጥያቄ፡- ለመሆኑ በዚህ ዘመን የኢትዮጲያ ሙዚቃ ደረጃ የደረሰበትን ደረጃ እንዴት ታየዋለህ?

ሙሉ ቀን – እኔ የምነግርህ ያየሁትን ሳልደብቅ እዉነቱን ነዉ፡፡ ሙዚቃ ድሮ በኛ ግዜ ቀረ፡፡ የአሁኑ ሙዚቃም ሆነ ዘፈን የሽሚያ ይመስላል፡፡ በእርግጥ በኣንዳንድ በቁጥር ትንሽ የሆኑ ወጣት አርቲስቶች ተፈጥረዉ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ምንም ቢሆን የድሮዉን የሚያክል የለም፡፡ ለምሳሌ እኔ ዘፈን ማቆሜን የሰማ አንድ ታዋቂ አርቲስት “የኢትዮጲያ ሙዚቃ ሞተ” ብሎ ተናግሯል፡፡

ጥያቄ፡- ምን ማለቱ ነዉ? ያለአንተ ተሳትፎ ሌላ ሰዉ የለም ማለቱ ነዉ ወይስ ታላቁን አርቲስት አጣን ማለቱ ይሆን?

ሙሉ ቀን –  አንተ በፈለከዉ መንገድ ተርጉመዉ እንጂ እኔ በዘፈን አለም በነበርኩበት ወቅት የኢትዮጲያን ሙዚቃ በዉጭው አለምም ሆነ በሀገር ዉስጥ ከፍተኛ ቦታ ማድረሴንና በዓለም ስሙ የተጠራ ድምፃዊ እንደነበርኩ የሚክድ ያለ አይመስለኝም፡፡

ጥያቄ፡- በአለም ደረጃ ስትል ምን ማለትህ ነዉ?
ሙሉ ቀን – ከሀገር ውጪም በአለም ዓቀፍ ደረጃም ስመጥር የነበሩት እንደ ቦብ ማርሊ እና ስቲቭ ወንደር አብሬያቸዉ እንድጫወት ጥያቄ አቅርበውልኝና የምጫወተውን ዘፈን ግጥም እንዳጠና ልከውልኝ የነበረው ለእኔ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ብዙ ሙዚየሞች ፎቶግራፌንና ታሪኬን ለማስቀመጥ ጥያቄ አቅርበዉለት የነበረ ኢትዮጲያዊ ዘፋኝ እኔ ብቻ እንደነበርኩ ቀደም ብዬ ነግሬህ ነበር፡፡

ጥያቄ፡- ታዲያ ምን ተፈጠረና ይህ እቅድ ተቋረጠ?

ሙሉ ቀን – በመሀል ጌታ ጠልፎ ወሰደኝና በእቅፍ ዉስጥ አደረገኝ፡፡ እኔም አለማዊ ሕይወቴን ትቼ ሕይወቴን ለጌታ ሰጠሁ፡፡

ጥያቄ፡- አሁን ካለህበት ሁኔታ እና ከቀድሞዉ አንተ ዓለማዊ ከምትለዉ ሕይወትህ የትኛዉ ተመችቶሃል?

ሙሉ ቀን – ይኼን ጥያቄ ብለህ ማቅረብህ ራሱ ይገርማል፡፡ ጥያቄህ ከሞት እና ከህይወት የቱን ትመርጣለህ እንደማለት ነዉ፡፡

ጥያቄ፡- በህይወትህ ፍቅር ይዞህ ያዉቃል እስቲ ትዝታህን ትንሽ አጫዉተኝ?

ሙሉ ቀን – እኔ በህይወቴ ፍቅር ይዞኝ አያዉቅም፡፡ ፍቅር የጀመረኝም የያዘኝም አንዴ ብቻ ነዉ፡፡ ያም ጌታን የተቀበልኩ ጊዜ ለመጀመሪያ ግዜ ከሱ ጋር በፍቅር ወደቅሁ፡፡

ጥያቄ፡-  በአንድ ተወዳጅ ዘፈንህ ላይ

“እመነኩሳለሁ ስፋልኝ ቆቧን፤

እሷም አልተገኘች አለሷም አይሆን”

ብለህ የዘፈንከዉ  የምታፈቅረዉ ስላጣህ ነበር ማለት ነው?

ሙሉ ቀን – እኔ ይሄን አስቤዉ  አይደለም፡፡ ግን እውነትም አንተ እንዳልከው ይመስላል፡፡

ጥያቄ፡- ሙሉቀን ያንተ ዘፈኖች እኮ በሙሉ ፍቅርን የሚሰብኩ ፤ የተጣላን ፍቅረኛ የሚያስታርቁ ፤ የከፋዉን የሚያስደስቱ ፤ልቡ የተሰበረን የሚጠግኑ ናቸዉ፡፡ አንተ ምኑን ነዉ ሀጥያት የምትለው?

ሙሉ ቀን – ከሙዚቃዉና ከዘፈኑ ጋር በተጓዳኝነት የሚመጡ ብዙ ኃጥያቶች አሉ፡፡ ዘርዝሬ ለመንገር እቸገራለዉ፡፡

ጥያቄ፡- – ዘፋኝ ገነት አይገባም የሚለዉ አስፈርቶህ ነዉ ሃይማኖት የቀየርከው ወይስ በቅድሚያ ስለኃይማኖቱ በቂ ትምህርት ወስደሃል?

ሙሉ ቀን – ጌታን ለመቀበል በቅድሚያ ትምህርት መውሰድ አያስፈልግም፡፡ አምነህ መቀበል ብቻ ነዉ የሚያስፈልገው፡፡ በእርግጥም በመፅሀፍ ቅዱስ ላይ “ዘፋኝ ገነትን አይወርስም” ተብሎ ተፅፏል፡፡

ጥያቄ፡-  ታዲያ  በመፅሀፍ ቅዱስ ላይ የተፃፈውን በጥልቀት ከተረዳነው በወቅቱ ለዛር ፤ ለአጉል እምነት የሚጨፍሩና የሚዘፍኑትን ለማስጠንቀቅ ብቻ አይመስልህም?

ሙሉ ቀን – እሱ አንተ እንደተረዳኸዉ ነዉ፡፡ ቃሉ ግን ዘፋኝ ገነት አይገባም ነዉ የሚለዉ፡፡

ጥያቄ፡- ለሃገር ፍቅር ፤ለሚስት ፍቅር ፤ ለኣባትና እናት ፍቅር የሚዘፈኑ ዘፈኖች ሁሉ ወደ ሲኦል ይመሩሃል ማለት ነው?

ሙሉ ቀን – እንግዲህ እንዳንተ ፍላጎት ቃሉን መቀየር አይቻልም፡፡ ከዘፈንክ ትደንሳለህ ፤ታመነዝራለህ  ሌላም አብሮ የሚመጣ ኃጥያት አለ፡፡ ስለዚህ የገነትን በር አታይም፡፡
ጥያቄ፡-  ሙሉ ቀን አንተ እኮ እንደምትለዉ ከሆነ የሰዉ ልጅ ከተወለደባት ቀን ጀምሮ ይህቺን ዓለም መናቅና ጠዋትና ማታ በመፀለይ ብቻ መኖር አለበት ነዉ የምትለኝ፡፡ ይሔ ፈጣሪን ማስጨነቅ አይሆንም? አምላካችን በዚች አለም ተባዝተን እንድንኖርና ከበረከቷም እንድንቋደስ ነዉ የፈጠረን፡፡ አንተ በምትለዉ መንገድ ግን በአለም ላይ የሰዉ ልጅ ምንም የምርምር ሥራና በፈጠራ ስራ ሳይሳተፍ ወደመጣበት እንዳለቀሰ ተወልዶ እያለቀሰ እንዲሞት ነዉ የምትመክረዉም የምትሰብከዉም፡፡

ሙሉ ቀን – ቃሌን እየቀየርክ ነዉ ያለኸዉ፡፡ እኔ የምለዉ ጌታን ተቀበሉ፡፡ ከእሱ የምታገኙት በረከት ይበልጣል  ምርምርም ሆነ ፈጠራ የሱ ብቻ ነዉ፡፡ ዘፈን የሰይጣን ማሳደጊያ ጡጦ ነዉ የምልህ፡፡

One thought on “​”እኔን የሚያክል ዘፋኝ በኢትዮጵያ አልተፈጠረም፣ ወደፊትም አይፈጠርም- አርቲስት ሙሉቀን መለሰ

  1. እንደ ሙሉቀን መለሰ ያለ ዘፋኝ እስከ ምፅአተ ዐለም ራሱ አይገኝም።የ ዉበትዋ ግርማ ከ ሩቅ የ ሚስበዉ ዳሌ ተረከዝዋ ሽንጥዋ የ ረቀቀዉ አይንዋ እንደ ጦረኛ የሚያስበረግገዉ………..አድምጡት!!!

    Like

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s