History

​ንጉሱን ለሞት ያበቃው 11 ሚሊየን ዶላርና መዘዙ

መስከረም 2 ቀን 19667 ዓ.ም በሻለቃ መንግስቱ ኃይለማርያ የሚመራው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ንጉስ ግርማዊ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ በመንፈቅለ መንግስት ከመንበራቻው አውርዶ 59 ሚንስትሮቻቸውን በጅምላ ረሽኖ  ህዳር 15 ቀን ‹‹1967 ዓ.ም  መንግስት በሚያስተዳድረው የሬዲዮና ቴሌቭዥን ጣቢያ በማርሽ  ታጅቦ  ‹‹…….በጨቋኞች ላይ ዛሬም ሆነ ወደ ፊት የምንወስደው  እርምጃ በንፁሃን ሠዎች ላይ እንደተወሰደ ወይም የንፁሃን ደም እንደፈሠሠ የማንቆጥረው መሆኑን እናረጋግጣለን።›› ሲል የሚኒስትሮቹን መገደል ይፋ አድርጎ የግድያ ዜናውንም
‹‹የፍየል ወጠጤ ትከሻው ያበጠ ልቡ ያበጠበት

እንዋጋ ብሎ ለነበር ላከበት

የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች

ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ትሞታለች›› በሚል ዜማ አጀበው።
ቅድመ ታሪክ  

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴን  ‹‹ሞላ› የሚል የሚስጥር ስም በመስጠት ቀድመው ታስረውበት ከነበረው  ከ4ኛ ክፍለ ጦር  በማንሳት በታላቁ ቤተመንግስት ውስጥ በሚገኘው በቀድሞው የግቢ ሚኒስቴር ቢሮ ውስጥ እንዲታሠሩ ተደረገ ። እስር ቤቱን ለመቆጣጠር  እና ለመፈተሽ ለመግባት የሚችሉት የደርጉ ዋናና ምክትል ሊቀመንበሮች፤  የደርጉ እስር ቤት አስተዳደር ኮሚቴ፤ የደርግ አባላት፤ የደርጉ ሥራ አስፈፃሚ ሃላፊ፤ የደርጉ የዘመቻ መኮንን፤ የእስረኛ ጥበቃ ክፍል ሹምና የመ/አለቃ ዳዊት ገብሩ (የቀ.ኃ.ሥ ጥበቃ ተቆጣጣሪና አስተባባሪ) ብቻ ነበሩ።

‹‹ለእስረኛው የሚቀርብ ምግብ መጠጥና ልብስ እንዲሁ ወደ እስር ቤት የሚገቡ ሠራተኞች እንዲሁም ማንኛውም ሠው ከደርግ አባሎች ከደርጉ ዘመቻና ጥበቃ መኮንን (ሌተናል ኮሎኔል ዳንኤል አስፋው) እና ከእስረኛ ጥበቃ ክፍል ሹም በስተቀር ሳይፈተሸ እንዲገባ አይፈቀድም።
የንጉሡን ጤና የሚቆጣጠር ሐኪም በፈለጉ ጊዜ ቀንም ሆነ ሌሊት ተጠርቶ ሊጎበኛቸው የሚችል ሲሆን በተለይ የግል ሐኪማቸው  ዶክተር አስራት ወልደየስና ዶክተር ዮሐንስ ወርቅነህ በየጊዜው እየገቡ ሊመረምሯቸውም እንደሚችሉ ግንቦት 4 ቀን 1967 የእስረኛ ጥበቃ ትዕዛዝ ቁጥር 5 ለሻለቃ የጎራው ከበደ (የእስረኞች ጥበቃ ሹም) እና ለሻለቃ ስለሺ መኩረያ (የደርጉ የሠፈር ጥበቃ ሹም) በደርጉ ዘመቻና ጥበቃ መኮንን በሌተናል ኮሎኔል ዳንኤል አስፋው ተሠጠ። የጥበቃው አላማ እስረኛው እዳያመልጡ ወይም አደጋ እንዳይደርስባችው በሚል ነበር።

ንጉሡ ከሞላ ጎደል በእንክብካቤ ተይዘው ነበር ማለት ይቻላል። እንግዶች ይጎበኟቸዋል ሐኪሞች ያዩአቸዋል። የታሠሩት ብቻቸውን ነው። ምግብ ከቤተመንግስት ይቀርብላቸዋል ። ይህ ሁሉ ሆኖ እስረኛ ናቸው። የሁዋላ ዋላ አንክብካቤውም እንደ ነበር አልቀጠለም። የኮንጎ ዘማቾችን ክፍያ ገንዘብና ንጉሡ በስዊዝ አገር በሚገኝ ባንክ  አስቀምጠውታል የተባለ ገንዘብ ንጉሡ እና ደርግን ሲያነታርክ ቆየ። በተለይ በስዊዝ አገር ተቀመጠ የተባለውን  11 ቢሊዮን ዶላር  ማግኘት የደርጉ ዓላማ ስለነበር በአንድ በኩል ንጉሡን በእንክብካቤ እየያዘ በፈቃዳቸው ገንዘቡን እንዲመልሡ፤ ልጆቻቸውና ወዳጆቻቸው እንዲያሳምኑአቸው በማድረግ በሌላ በኩል ደግሞ የራሱን ምርመራ ሲያደርግ ቆየ።
ጳግሜ 5 ቀን 1966 ዓ.ም ደርጉ ባደረገው ስብሰባ ቀደም ሲል ግርማዊ ንጉሠ ነገስት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ገንዘብ ስዊዝ ሀገር እንዳላቸው ተጠይቀው የለኝም በማለታቸው ከደርጉ የተውጣጡ ሠዎች እንዲጠይቋቸው ወሠነ። በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል መዝገብ ቁጥር 1/87 (401/85) ውስጥ የልዩ አቃቤ ህግ ማስረጃ  የደርጉ ጠቅላላ ጉባኤ 2ኛ መዝገብ ገፅ 25-26 ላይ ንጉሡ ሲጠየቁ የለኝም የሚል መልስ መስጠታቸውን እና (በአሁኑ ጊዜ ገንዘብ አለዎት ከማለት ለምን ማስረጃ አታመጡም ?  ለልጆቼ እንደማንኛውም ሠው ገንዘብ ሠጥቼ ይሆናል።) ብለው መመለሣቸው ተቀምጧል።
መስከረም 12 ቀን 1967 በተደረገ የደርጉ ጠቅላላ ስብሰባ ‹‹በልዑል ራስ እምሩ እንዲነገራቸው። እምቢ ቢሉ የሚደረግላቸውን የምቾት አገልግሎት ማቋረጥ ይኖርብናል›› በማለት ተወሰነ።
ጥቅምት 5 ቀን 19677 በተደረገ ሌላኛው  የደርጉ ጠቅላላ ስብሰባ ላይ የሚከተለው ሀሳብ እንደቀረበ በፌ.ከ.ፍ.ቤት  ወንጀል መዝገብ ቁጥር 1/87 (401/ 85) ውስጥ የል.ዐ.ህግ ማስረጃ የደርጉ ጠቅላላ ጉባኤ እኛ መዝገብ ገፅ 171-172 ድረስ ተቀምጧል።
‹‹አንዳንድ እርምጃ ስንወስድ ማስፈፀም አለብን በውጭ ሀገርና በሀገር ውስጥ  ድጋፍ ያጣነው በንጉሡ ስለሆነ ንጉሡን መግደል አለብን። የታሠሩትን የባለሥልጣን  ልጆችንም ማሠርና የሞት ፍርድ መስጠት አለብን…..››
በዚሁ የደርጉ ጠቅላላ ስብሰባ ላይ የደርጉ እስረኛ አስተዳደር ኮሚቴ በቤተሠቦቻቸው በሳምንት አንድ ቀን መጥተው ጃንሆይን ቢያዩአቸው የቤት እንስሳዎች ቢፈቀድላቸው በማለት ለቀረበው ጥያቄ ከደርጉ ያገኘው መልስ እንዲጎበኙ የማይፈቀድ የመሆኑን ውሳኔ ነበር።
ጥቅምት 8 ቀን 1967 የደርጉ ጠቅላላ ስብሰባ ውሳኔ ሠጠ

ውሳኔውም

‹‹በውጭ ሀገር እና  በሀገር ውስጥ ያለውን ማንኛውንም ተንቀሳቃሽ ሀብት አክሲዮን ገንዘብ የከበሩ ድንጋዮች ሁሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ እዲያወርሱ ቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴን መጠየቅ። መተማመኛ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ ። እንዲፈርሙ። ልዑል ራስ እምሩ አቶ ተፈራ ደግፌ አቶ ዮሐንስ ኪዳነ ማርያም የውጭ ባንኮች የሚገኙበት አምባሳደር የውጭ ሳይሆን የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞችና ቴሌቭዥን አንሺዎች እንዲገኙ››

በተባለው መሠረት በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴና በደርግ ተወካይ ውይይት መካከል በውሳኔው ማግስት ጥቅምት 9 ቀን 1967 ዓ.ም ተጀመረ። ውይይቱም ጥብቅ ሚስጥር በሚል እንዲያዝ ተደረገ።
የንጉሡን እና የውይይቱ መንፈስ ይህንን ይመስል ነበር።
ልዑል ራስ እምሩ፡ ለመጠየቅ ነው የመጡት አሁን።
ጃንሆይ ፡- ለምን?
የደርግ ተወካይ፡- ግርማዊነትዎ ባለፉት ጥቂት ጊዜያቶች ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በግርማዊነትዎና እንዲሁም በቤተሰብዎ እጅ በውጭና እንዲሁም በከተማ ክልል አለ ተብሎ በሚነገረው ጉዳይ እናንተ አለ የምትሉት ቢኖር እኛ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፤
ጃንሆይ ፡- እኮ!
የደርግ ተወካይ፡- እኔ የምለው አለ የሚባል ነገር ቢኖር እኛ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጉሮሮ ነጥለን ራሳችንን ለመጥቀም ፍላጎት የለንም። እና አለ የምትሉት ነገር ቢኖር እንዲታዘዝና በዚሁ በተፈጥሮ ጉዳት ድርቅ ለጎዳው ሕዝብ እንዲውል በማለት ነው። ይኸው በሰጡን ተስፋ መሠረት ይኸንኑ የርስዎን ፈቃድ ያዘለ ፁሁፍ አሰናድተን አቅርበናል። ግርማዊነትዎ ጹሁፉን  ሰምቶ ፈቃዱ እንደሆነ አንዲያዝልን ነው እና ይነበባል።

ለኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ መንግስት አዲስ አበባ እኛ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በኢትዮጵያ  ላይ በደረሰው አደጋ ምክንያት የተጎዳው የኢትዮጵያ ሕዝብ የደረሰበትን ከፍተኛ ጉዳትና ችግር በማሰብ በስማችን በኛም ጥያቄ በግርማዊነት እቴጌ መነን በልጆቻችንና በልጅ ልጆቻችን  ስም እኛ በኢትዮጵያ  በሚገኙ ባንኮች     2ኛ  ከኢትዮጵያ  ውጭ በሚገኙ ባንኮች 3ኛ በወከልናቸው ድርጅቶች ኩባንያዎች ግለሰቦች የሚገኘውን ገንዘብ የባንክ ሂሳብና ሰነዶች እንዲሁም ወርና ሌሎችም የከበሩ ድንጋዮች በጠቅላላው በሀገራችን ውስጥና ከሀገር ውጭ ያለውን የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ  ንብረት ሁሉ የሚሸጠው ተሽጦ በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ ተዛውሮ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሂሳብ ቁጥር 246 ድርቅ ለመታቸው ክፍለ ሀገሮች ዕርዳታና መቋቋሚያ ማስተባበሪያ ኮሚሽን በሚል ስም በሚገኘው ሂሳብ ገቢ እንዲሆን የማይሸጠው ደግሞ በቋሚ ለሕዝብ መተዳደረያ እንዲሆን እናስታውቃለን። የሚል ነበር ያዘጋጀነው፡
ጃንሆይ፡-  ለማወቅ የሚፈለገው ምንድን ነው?
የደርግ ተወካይ፡- /አንድ የጦር  መኮንን/ ካሁን ቀደም  እዚህ ቦታ መጥተን ግማዊነትዎን አነጋግረን ነበር።
ጃንሆይ፡- ኦዎ።
የደርግ ተወካይ፡- በእርስዎ ስም’ በእቴጌ መነን ስም’ በልጆችም ስም ያለው ሂሳብ ይታወቅና ለሕዝቡ እርዳታ እንዲውል እንፈቅዳለን የሚል መፈቀዱን ነበር። እኛም ራሳችን 1ኛ ይህንን አዘጋጅተናል 2ኛ ደግሞ ያገኘናቸው ማስረጃዎች አሉ ለምሳሌ በዙሪክ ባንክ ውስጥ ናሽናል ሲቲ ባንክ፣ አሜሪካ ዌስት ሚኒስቴር ባንክ ደግሞ ኢንግላንድ መኖሩን አውቀናል። በነዚያ አክሲዮኖችና ባንኮች ምን ያህል አክሲዮን እንዳለ እንዲገልፁልን በግርማዊነትዎ ፊርማ እንዲተላለፍ በእንግሊዘኛ የተፃፈ ሪፖርት አዘጋጅተናል። እነሱ መልስ ይሰጡናል። ከዚያ ከመልሱ በኋላ ደግሞ’
ጃንሆይ፡- ባንኮቹ የሚያውቁት ማለት ነው?
የደርግ ተወካይ፡- አዎ’ እስካሁን ድረስ ምን ያህል ሂሳብ እንዳለ’ምን ያህል ገንዘብ እንዳለ’ ምን ያህል አክሲዮን እንዳለ’ ባንኮቹ ይገለፁልናል። እነዚያ ደግሞ ባንኮች መልስ ሲሰጡን ያ ውጭ ያለው ሀብት ድርቅ ለመታቸው ቀበሌዎች ለእርዳታ እንዲውል ግርማዊነትዎ እንዲያስተላልፉልን የተዘጋጀ የእንግሊዘኛ ጹሑፍ አለ። ይህ አሁን በአማርኛ ያነበብኩት አጠቃላይ ሃሳቡን የያዘ ነገር ነው።
ጃንሆን፡- ቆይ ግልጥ ያለ ነገር መግለጥ ያስፈልጋል። የመንግስት ገንዘብ ውጭ አለ ለማለት ነው። አሁን የምትጠይቁት ምን እንድንገልጽላችሁ ነው?
የደርግ ተወካይ፡- 1ኛ ይኸ ጠቅላላውን ውጭ አገር በልጆችም ሆነ በእቴጌ ወይም በግርማዊነትዎ በኩል ውጭ ያለ ሀብት ካለ በአጠቃላይ ድርቅ ለመታቸው ቀበሌዎች እርዳታ እንዲውል በስጦታ መልክ ግርማዊነትዎ የፈቀዱ ለመሆኑ እንዲያረጋግጡልን ነው።በየባንኮቹ ገንዘብ መኖሩን ፣አክሲዮን መኖሩን ያረጋገጥነው አለ። ያዘጋጀናቸው ጹሁፎች በመጨረሻ ጊዜ  ያለውን ሂሳብ አያስረዱም፣ አይገልጹም። እነሱ ራሳቸው እስከ አሁን ድረስ ያለው ሂሳብ ምን ያህል እንደሆነ ሲያረጋግጡ’ ግርማዊነትዎ በተለይ ደግሞ ያ የተገኘው ገንዘብ ለነዚህ ለድርቅ ቀበሌዎች እንዲውል እዲያረጋግጥልን ነው አንጂ ሌላ ነገር አይደለም።
አቶ ዮሐንስ ኪዳነማርያም አራት ደብዳቤዎች በእንግሊዝኛ ተዘጋጅተዋል። ይኸውም
ጃንሆይ ፡- አራት ደብዳቤዎች?
አቶ ዩሐንስ፡- ይኸውም ግርማዊ ጃንሆይ እንዲፈርሙ አንዱ ለዙሪክ ባንክ፣ ሁለት ናቸው እዚህ ያሉት ባንኮች ዩኒየን ባንክና ባንክ ኮሜርሻል የሚል።
ጃንሆይ፡- እኮ ምንድናቸው?
አቶ ዮሐንስ፡- እዚያ ላይ ያለውን ሒሳብ አስታውቁን የሚል ጥያቄ ነው።
ጃንሆይ፡- እኮ የት ያለውን?
አቶ ዮሐንስ፡- በግርማዊነትዎ ትዕዛዝ የተቀመጡ ሂሳቦች
ጃንሆይ፡- ሁሉን የምታውቀው ነው’ የምትጠይቀኝ ምንድን ነው?
የደርግ ተወካይ፡- ያንን ግን ማረጋገጫ’እዚህ ያሁኑ ሁኔታ ሒሳብ መዝገብ ውስጥ ስላልተገኘ እነሱ እንዲያረጋግጡ ነው’ ደብዳቤው የተፃፈው።

ጃንሆይ፡- ማን እንዲያረጋግጥ?
የደርግ ተወካይ፡- እነዚያ ባንኮቹ ‘ ጃንሆይ ካላዘዙዋቸው ደግሞ እሽ ብለው አያረጋግጡም ‘ ለዚህ ነው ደብዳቤው የተዘጋጀው ‘ ይኽ የአማርኛው ሌላ ነው’እዚህ ጃንሆይ የሚወስኑት ነገር ነው ያኛው ግን…
እራስ እምሩ፡- ያለውን ሒሳብ አስታውቁን ብለው ግርማዊነትዎ ይፈርሙልን ነው አሁን እነሱ የሚሉት’
ጃንሆይ፡- የምንፈርመው ምንድን ነው?
ራስ እምሩ፡- ከዚያ ወዲያማ እነሱ ለእርዳታና ለምናምን እዚሁ መጥቶ ለዚህ ለተጎዳውና ለዚህ ለምናምኑ ገንዘብ እንዲውል እንዲያደርጉ ነው።
ጃንሆይ፡- እኮ የምንጠይቀው ማንን ነው?
ራስ እምሩ፡- ባንኩ ሲያስታውቅ መልሱን ነው።
ጃንሆይ፡- እዚያ ባንኩን ምን ያህል አለ ብሎ ለመጠየቅ ነው?
ራስ እምሩ፡- አዎን ምን ያህል ነው ያለው ገንዘብ
አቶ ዮሐንስ፡- በአጭሩ ግርማዊ ጃንሆይ….
ጃንሆይ፡- አይሸፋፈን
አቶ ዮሐንስ፡- የለም የሚሸፈን ነገር አይደለም። ዋናው ነገር የሚጠየቀው ምንድን ነው? የሚጠየቀው ምንድን ነው? የሚጠየቀው አሁን በግርማዊነትዎ ስም’ በልጆቹ’ በልጅ ልጆቹ  ያለው ገንዘብ በሙሉ ለድርቅ ቀበሌዎች እንዲውል ነው የሚፈለገው’ መሰረቱ ይኸ ነው’የመንግስት ሳይሆን በግል የተያዘው ብቻ ለዚህ እንዲውል ነው የሚፈለገው’
ጃንሆይ፡- የሚፈለገው አሁን ላላው ችግር በአገሩ ባንክ የተቀመጠው ገንዘብ
አቶ ዮሐንስ፡-  ገንዘቡ በሙሉ ለዚህ እንዲውል ‘ የግርማዊነትዎ የልጆችም
ጃንሆይ፡- የት ባንክ ነው የሚቀመጠው አለ ወይ?
አቶ ዮሐንስ፡- የለም አንዳንድ ሰነዶች ተገኝተዋል። ግርማዊ ጃንሆይ አሁን ለምሳሌ ዙሪክ ባንክ ኮሜርሻል አሁን እንዳስረዳነው አንዳንድ ሰነዶች ተገኝተዋል። ለምሳሌ በነዚያ ሰነዶች አንዳንድ ተቀማጭ ገንዘብ ተገኝቷል።
ጃንሆይ፡ የት?
አቶ ዮሐንስ፡- ዙሪክ ባንክ’ናሽናል ሲቲ ባንክ’ኒውዮርክም ተገኝቷል’ ዌስት ሚኒስቴር ባንክም ተገኝቷል።
ጃንሆይ፡- ዙሪክ ያለውን ገንዘብ አግኝተህ የለም?
አቶ ዩሐንስ፡- አዎ ተገኝቷል ብቻ….
የደርግ ተወካይ፡- የቆየ ነው
አቶ ዮሐንስ፡- አሁን የሚጠየቀው ግርማዊ ጃንሆይ ትንሽም ቢሆን ትልቅም ቢሆን ለዚህ ለድርቅ ለተመታው ሀገር እንዲውል በማሰብ ነው።

ጃንሆይ፡- ትልቅም ትንሽ እዚያ ዙሪክ ባንክ እንዳለ ለማስታወቅ
አቶ ዮሐንስ፡- አንዱ ለመጠየቅ ነው’ ሁለተኛው
ራስ እምሩ’ ተጠይቆ መልሱ በኋላ ቢሆን አይሻልም?ልኩ ታውቆ ከዚያ የሚሆነውን ነገር ደግሞ ብታደርጉ አይሻልም? መጀመሪያ ጥያቄው ይሁን’ ያ ሲመጣና ሲታወቅ’ ልኩ’እንግዲህ ደግሞ የሚመጣውን የሚቀርም ቢሆን ምናለ ከዚያ ወዲያ ብታደርጉ አይሻልም ወይ?
የደርግ ተወካይ፡- በዚሁ መንፈስ ነው የተዘጋጀው።
ራስ እምሩ፡- አሁን ማነባበራችሁና መጠየቁ ነው እንትን የሆነው

የደርግ ተወካይ፡- የለም አልተነባበረም የመጀመሪያ በአማርኛ የተገለፀው በጠቅላላው ግርማዊነታቸው ለኢትዮጵ ሕዝብ
ጃንሆይ፡-ምን?
የደርግ ተወካይ፡-  ግርማዊነትዎ የመጀመሪያው አሁን በአማርኛ የተገለፀው ነገር በአጠቃላይ በውስጥም ቢሆን ውጭ በግርማዊነትዎም ስም  ሆነ በቤተሰቡ ያለው ቋሚም ሆነ ተንቀሳቃሽ ንብረት አሁን ኢትዮጵያ ለደረሰባት ጉዳት ማሻሻያ እንዲውል በአጠቃላይ ፈቃድዎ መሆኑን የሚገልጽ ብቻ ሲሆን’ ሌሎቹ በእንግሊዝኛ የተዘጋጁት ለምሳሌ ቀደም ብለን ባገኘናቸው ማስረጃ መሠረት የተጠቆመ’
ጃንሆይ፡- የተዘጋጀው ምንድን ነው?
የደርግ ተወካይ፡- እንዲህ ነው የተዘጋጀው እንደመሰለኝ ገልፀውታል’ ለምሳሌ ኢንግላንድ በዌስት ሚኒስቴር ባንክ’አሜሪካም እንዲሁም ደግሞ ዙሪክ የአራት ባንኮች የተለያዩ ሂሳብ እንደያዙ ማስረጃ ተገኝቷል። ግን ይህ ማስረጃ ቀደም ብሎ ገና
ጃንሆይ፡- ባንኮች ተገኝተው የለም?
የደርግ ተወካይ፡- አዎ።
ጃንሆይ፡- የተገኘው ምን ይላል?
የደርግ ተወካይ፡- የተገኘው ገንዘብ መኖሩ እንጂ’ ምን ያህል ገንዘብ መኖሩን የሚስረዳ አይደለም። ደግሞ ቆየት ያለ።
ጃንሆይ ፡- እኮ ምን ልናደርግ መሆኑን?
አቶ ዮሐንስ፡- አሁን የእንግሊዝኛው ደብዳቤ የሚለው ምንድን ነው? ግርማዊ ጃንሆይ በእናንተ እጅ በግርማዊነታቸው ‘በግርማዊት’ በልጆችዎ’ያለውም ሒሳብ አስታውቁን ነው።
ጃንሆይ፡- ለመጠየቅ?
አቶ ዮሐንስ፡- ለመጠየቅ አንድ እሱ ነው’ ግርማዊ ሆይ ሁለተኛ ደግሞ
ጃንሆይ፡- እኔ ምንም ቅር የሚለኝ አይሆንም።
አቶ ዮሐንስ፡- አንዱ እሱ ነው ደግሞ ከዚህ ቀደም ያስታውሱ እንደሆነ
ጃንሆይ፡- ሕዝብ በረሃብ ሲሞት የምንረዳበት ምክንያት ከተገኘ በደስታ የምናደርገው ነገር ነው እንጂ ሰው ከእግዚአብሔር የሚሰውረው ነገር የለም። የሆነ ሆኖ የአገሩ ሕዝብ በምንም ዓይነት እሱ የሚሰማው ለኛም ይሰማናል።
ራስ እምሩ፡- ጥያቄው ተነባበረና የመስለኛል።
ጃንሆይ፡- አዎ ግልጥልጥ ያለ ነገር ይሠራ።
ራስ እምሩ፡-  አስቀድሞ ይጠየቅና የገንዘቡ ልክ ይምጣ ነው የምለው። ከዚያ ወዲያ የምታድረጉት ሁለተኛ ጉዳይ ይሁን ነው የምለው እኔ። አይሻልም?
የንጉሱ እና የደርጎች ውዝግብ እንደቀጠለ ነው። የንጉሱ እድሜ ተጨምሮበት እና በደርግ በኩል በተለያዩ የውጭ ባንኮች ንጉሱ ደብቀው አስቀምጠውታል ያሉትን 11 ቢለየን ብር  ለመቀበል መጓጓት ተጨምሮበት መግባባት የሚባል አጠገባቸው አልደርስ ብሏል።

ንጉሱ በታሰሩበት በአንዱ ቀን እንዲህ ሆነ…….

ሻለቃ አጥናፉ አባተ ንጉሱን ማነጋገር እፈልጋለሁ በማለት ወደ ክፍላቸው ገባና  “ጃንሆይ እኛ እኮ ውጭ ያለዎትን ገንዘብ ቢሰጡን ይሄን ያህል ባልታሰሩ ነበር” አላቸው። ንጉሱም “የምን ገንዘብ?”  በማለት ጠየቁት “በአለም ጋዜጣ ተገልጿል አንብቤ ነው” በማለት መለሰ ንጉሱ ፊታቸው በቁጣ ተለዋውጦ “ለመሆኑ ማንበብ ትችላለህ እንዴ?” በማለት መልሰው ጠየቁት። ሻለቃውም በንዴት “ክፉ ሽማግሌ!” ብሎ  እየተነጫነጨ ከአጃቢዎቹ ጋር ተመልሶ ሄደ።

ንጉሱን ለማሳመን ከደርግ በተመረጡ እና እና ይቀርቧቸዋል በተባሉት( ራስ እምሩ ፤አቶ ተፈራ ወርቅ፤ አቶ ዮሀንስ) በደርግ በኩል በቀረበው ከስዊዝ ባንኮች ገንዘብ ይዙር የሚል ሰነድ ላይ እንዲፈርሙ ጥረቱ እንደቀጠለ ነው ። ንጉሱ እድሜያቸው እንደገፋ በሚያስብቅ ሁኔታ ቀድመው የጠየቁትን መልሰው መላልሰው ይጠይቃሉ ፤ ተስማሙ ሲባል ነገሩን ከመነሻው ይጀምሩታል ሁኔታው ሁሉ እዛው በእዛው ቀጠለ። እነሆ አለፍ አለፍ ብለን የመጨረሻ ክፍሉን ለአንባቢያን እንዲመች አድርገን አሰናድተነዋል።

ደርግ፡- አለ የተባለው ገንዘብ ማስረጃው ቢገኝም ገንዘቡ ገና ሲቀመጥ የተያዘው ሂሣብ እንጂ ዛሬ ያለውን ትክክለኛ ነገር የሚያስረዳ ባለመሆኑ ሂሣቡ እዲታወቅ።

ጃንሆይ፡- የምን ገንዘብ ነው?

ደርግ፡- ከታወቀ ዘንድ ያው ሂሣብ ደግሞ ካለበት ቦታ ወደ ኢትዮጵያ ናሽናል ባንክ እንዲዛወር የሚል ነገር ነው።

ል.ራስ.እምሩ፡- ሁለቱም እንዲፈፀም ነው የምትሉት?

ደርግ፡- ሁለቱም አንዴ መሆን አለበት።እንግዲህ እዚህ ላይ እንዴት ነው እየቀደምን እኛ ራሳችን እየመጣን ግርማዊነታቸውም ከማስቸገር አንደኛ  ባንኩ ራሱ ሂሳቡን እንዲያሳውቅን ነው። ሁለተኛ ደግሞ ያ ያሳወቅን ባንክ ደግሞ ይነስም ይብዛ ለሕዝቡ እርዳታ እንዲውል የግርማዊነታቸውን ፈቃድ የጠየቅንበት ነው። እነዚህን ሁለቱ ደብዳቤዎች አንድ ጊዜ እንዲፈረም ነው።

ጃንሆይ፡- እኮ ተጠየቀ ወይ?

ደርግ፡- ይኸው አዘጋጅተናል።

ጃንሆይ፡- እንዲጠየቅ?

ደርግ፡- አዎን፣ እና ያ የሚጠየቀው ደግሞ ለሕዝቡ እርዳታ እንዲውል።

አቶ ዮሐንስ፡- ግርማዊነትዎ እንዲረዳው ያስፈልጋል፣ ጥያቄው ሁለት ነው አንዱ ሂሳቡ ተጣርቶ ይምጣ ነው……

ጃንሆይ፡-  አይደለም !አሁን የሚፈለገው እዚያ ባንክ ገንዘብ እንዳለን እና እዚያ ያለውን ገንዘብ እንዲያስታውቁ እንድንፈቅድ አይደለም?

አቶ ዮሐንስ፡- አዎን አንዱ እሱ ነው ሁለተኛው ደግሞ ግርማዊ ጃንሆይ እዲረዳው የሚያስፈልገው ያለው ሂሳብ ደግሞ ለዚሁ በድርቅ ለተመታው ቀበሌ እንዲውል ግርማዊነትዎ እንዲፈርምላቸውና በማስታወሻ መልክ እንዲያዝ ይፈለጋል ነው። ሁለት ነው ጥያቄው

ጃንሆይ፡- እኮ ያለንን ለማወቅ? ሂሳቡን እንዲያስታውቀን አይደለም?

አቶ ዮሐንስ፡- አንዱ እሱ ነው። ሁለተኛ ደግሞ የተገኘው ሂሳብ ለዚህ በድርቅ ለተመታው  ቀበሌ እንዲውል ግርማዊነትዎ እዲፈርም ነው የሚፈልገው።

ጃንሆይ፡- አለ ወይ?

አቶ ዮሐንስ፡- መቸም ከተገኘ እዚያ ይገባል ካልተገኘም ይቀራል።

ተፈራ ወርቅ፡- እኔ እንደማውቀው በጃንሆይ ስም በኔ በኩል የተቀመጠ ገንዘብ የለም። ነገር ግን በልዑል መኮንን ልጆች ስም የተቀመጠ ገንዘብ አለ። አሁን የሚፈለገው ጃንሆይ በእርስዎ ስም ያለ ገንዘብ ፣ በልጆቹም ስም ያለ ገንዘብ ቢገኝ በድርቅ ለተመቱ ቀበሌዎች እርዳታ እንዲውል ጃንሆይ ይፍቀዱ ነው።

ጃንሆይ፡- ባንኩን ለመጠየቅ ነው?

ተፈራ ወርቅ፡- መጀመሪያ ገንዘቡ ይጠየቃል፣ ባንኩ ይኽን ያህል አለ ካለ…..

ጃንሆይ፡-እኮ ባንኩ እንዲጠየቅ አይደለም?

ተፈራወርቅ፡- አዎ

ጃንሆይ፡- ይኽንን ማን ይጠላል፣ሕዝቡ የእግዚአብሔር ነው። የኛ አይደለም። ግን ለዚህ ሕዝብ የተቻለንን እንድናገለግል እግዚአብሔር ከመረጠን ቢጠየቅ ምናለበት።

አቶ ዮሐንስ፡- ግልጽ ነው ግርማዊ ጃንሆይ ብቻ ሁለተኛው ጥያቄ

ል.ራስ.እምሩ፡- አንዱ እንዲታወቅ፣ሁለተኛው የተባለውን ገንዘብ ግርማዊነትዎ ፈቅደው

ጃንሆይ፡- ገንዘብ እንዳለ አስታውቁን ብለን ለመጠየቅ አይደለም?

ጃንሆይ፡- ሁለተኛው ምንድን ነው?

ል.ራስ እምሩ፡- ፈቅደው ግርማዊነትዎ ከዚያ ወደ ኢትዮጵያ መንግስት ይዛወር ብለው እንዲዛወር ነው።

ጃንሆይ፡- ምኑ?

ል.ራስ.እምሩ፡- ፈቅደው ግርማዊነትዎ ያንኑ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ መንግስት እንዲዛወር ተብሎ ተዛውሮ…

ጃንሆይ፡- ያስቀመጥነው ገንዘብ እንዳለ?

ል.ራስ.እምሩ. የልጆችም ቢሆን የሁሉም ቢሆን ነው የሚሉት።

ጃንሆይ፡-  በዚህ በችግር ሕዝቡ የሚጎዳበት ነገር የማይሰማኝ አይደለሁም። እግዚአብሔር ለዚህ ከመረጠኝ ይኽን ያህል..

ል.ራስ.እምሩ፡- አሁንኮ የሚሉት እነሱ ቢሰማዎትም ግርማዊነትዎ ባይሰማዎትም ያንን ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ መንግሥት ይዛወርና የተቸገው ይረዳበት ነው።

ጃንሆይ፡-  የቱ ገንዘብ ነው?

ል.ራስ.እምሩ፡- የልጆቹም ገንዘብ ቢሆን።

ጃንሆይ፡- አለ ወይ? ታውቋል ወይ?

ል.ራስ.እምሩ፡- የታወቀ ታውቆ ያልታወቀው እንዲጣራ አሁን አንድ ወረቀት እንዲፃፍ ነው።

ጃንሆይ፡- እኮ የታወቀውን ማን ያቀርብልናል?

ደርግ፡- ግርማዊ ሆይ ቢኖር እንዲዛወር ፣ የለም ከተባለ የለም ነው። አይደለም እንዴ?እርስዎ ፈቃድዎ ብቻ ነው የተፈለገው።እዚያ ቢኖረን በኛ ስምና በልጆቻችን ስም እዚያ ያለው ይታወቅ ከታወቀም በኋላ ደግሞ ያለው መቶም ብር ይሁን

ጃንሆይ፡- ያለውን ገንዘብ አስታውቁን ለማለት አይደለም?

ደርግ፡- ልዑል ጌታዬ ዋናው አሁን ፀሐፊ ትዕዛዝ እነዳስረዱት እኔ ባየሁት ወረቀት ውስጥ ያሉት ሂሳቦች የልዑል መኮንን ልጆች ሆኖ በጃንሆይ ስም ያለ ሂሳብ እስካሁን አላየንም። አንዱ ብቻ ይኽ  ያለው ባንክ ድሮ የቆየ አንድ መዝገብ ስለተገኘ እንዳለ አስታውቁን የሚል ደብዳቤ ተፅፏል ለማረጋገጥ።

ጃንሆይ፡- የሚፈለገው ይኽን እንድንል ነወይ?

ደርግ፡- አንዱ እሱ ነው ግርማዊ ጃንሆይ፣ አንደኛው ደብዳቤ ባንኮቹ ጋ ያለው ሂሳብ በጃንሆይ ስም በእቴጌም በልጅ ልጆችም ስም ያለውን አስታውቁን ይላል።  ሁለተኛው ደግሞ ከዚያው ጋር አብሮ እንዲፈረም የተዘጋጀ  ይህ ከታወቀ ገንዘቡ ወደ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ መንግስት እንዲዛወር የሚል የጃንሆይን ፈቃድ የሚጠይቅ ነው።

ጃንሆይ፡- እኮ የቱ ገንዘብ? የማንን ገንዘብ ነው?

አቶ ዮሐንስ፡- ግርማዊ ጃንሆይ የኢትዮጵያ መንግስት ገንዘብ አይደለም በግርማዊነትዎ ፤ በግርማዊት፤ በልጆቹ ስም ያለ ገንዘብ ነው በባንኮቹ።

ጃንሆይ፡- የት ነው ያለው የት ነው የተቀመጠው?

አቶ ዮሐንስ፡- ዙሪክ

ጃንሆይ፡- ዙሪክ እዚያ የተቀመጠ ገንዘብ እንዳለ አስታውቁን ለማለት?

አቶ ዮሐንስ፡- አዎን አስታውቁን እንግሊዝም አገር ያለ አስታውቁን ናሽናል ሲቲ ባንክ።

ጃንሆይ፡- የት አለ ወረቀት?

አቶ ዮሐንስ፡- ግርማዊነትዎ እንዲረዳው ነው። አንዱ እሱ ነው፣ ሁለተኛው ደግሞ ይኽ የሚገኘው ገንዘብ ትንሽም ቢሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲውል ነው።

ጃንሆይ፡- እኮ ተጠይቆ አይደለም ወይ?

አቶ ዮሐንስ፡- አንዱ ለባንኮቹ  ጥያቄ ነው ። ሁለተኛው ደግሞ እንዲዛወር ነው ግርማዊ ጃንሆይ ሁለት ጥያቄ ነው ።

ጃንሆይ፡- እኮ ሁለትም ጥያቄ ቢሆን ባንክ ነውና ጥርት ባለ መንገድ እንዲሄድ ። እዚያ ባንክ እንዳለ። ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ረሃብ ላይ እያለ አይሰማንም አንልም።የሚሰማን የኛው ጉዳይ ነው። ይኸው ብቻ የሚፃፈው መልክ ያለው ወረቀቱ ይቅረብና የውጭ ባንክ ነውና የሚጣራው ያጥራው ….. ዞሮ ዞሮ በኢትዮጵያ ሕዝብ የምንለውጠው ነገር የለም።

አቶ ዮሐንስ፡-  ሁለተኛው ጥያቄ አለች እሷ ደግሞ እንዳትዘለል ያስፈልጋል። ሁለተኛው ጥያቄ ባንኮቹ ውስጥ ያሉ ገንዘቦች ወይም አክሲዮኖች ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲውሉ ግርማዊነትዎ እንዲፈቀድና

ጃንሆይ፡- ተጠይቆ ነው ሳይጠየቅ?

አቶ ዮሐንስ፡- ሳይጠየቅ ነው ብለው የሚጠይቁት የለም ይረዱት ብየ ነው። በኋላ ይህ ነው ያ ነው እንዳይባል ፣ ግማዊነትዎ እንዲያውቁት ነው። ሳይጠየቅም ግርማዊነትዎ ፈቅዶ ማስታወሻ እንዲፈረም ነው የተፈለገው።

ጃንሆይ፡- የባንክ ነገር…. ተፈራ ያውቀዋል’ የሚጻፈው ነገር ያልተሰናከለ ይሁን እንጂ እኛ በሕዝባችን የምንለውጠው ነገር ምንም የለም።

አቶ ዮሐንስ፡- ብለውታልኮ ግርማዊነትዎ ባለፈው ቀን ያለም የሌለውም ያው ካመጣችሁልን እኛ አስፈላጊውን እናደርጋለን ብለው ግርማዊነትዎ አረጋግጠዋል።

ጃንሆይ፡- ታዲያ ሌላ ምን ይፈለጋል;

አቶ ዮሐንስ ፡- እሱን አዘጋጅተው ነው የመጡት አሁን

ጃንሆይ ፡- ተመልሰው ማለትህ ነው; ለመጠየቅ;

አቶ ዮሐንስ፡- የለም ሁለት ነው ግርማዊ ጃንሆይ አንዱ ጥያቄ ነው ሁለተኛው ሂሳቡ እንዲዛወር ነው’

ል.ራስ.እምሩ፡- ነገሩ ለግርማዊነታቸው ሳይገባቸው የቀረ አይመስለኝም። አሁን የምንነጋገረው ሁሉ ሳይገባዎት የቀረ አይመስለኝም። ነገር ግን የልጆቹን ሁሉ አስረክቡ ለማለት ይኽ ነው ያስቸገራቸው ይመስለኛል።

የደርግ ተወካይ፡- ጥያቄ ነበረኝ። ግርማዊነትዎ እንዴት ነው ለምሳሌ እኛ ራሳችን በውርስ በእቴጌ’ በልዑል መኮንን ልጆች’በልዑል ሣህለ ስላሴ ልጅ ስም ገንዘብ መኖሩን አውቀናል አረጋግጠናል። ብዛቱ ይኽን ያህል ነው አይባል እንጂ ግርማዊነትዎ በልጆችዎ ወይም በልጅ ልጆችዎ ስም ያለው ገንዘብ ለዚህ በድርቅ ቀበሌው እንዲውል ፈቃደኛ ነዎት ወይ;

ጃንሆይ፡- እኮ ለልጆቹ ምን የሚሆን ገንዘብ ነው ያስቀመጥነው; እኛ የሰጠናቸው ነው; ወይስ የራሳቸው ነው; በምንም ዓይነት አሁንእኮ ግልጥ ብሎ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር ላይ የምለውጠው የለኝም ብዬ እኮ አጠቃልዬ ነው የተናገርኩት የማሻሽለው ነገር የለም።

ል.ራስ.እምሩ፡- የሚሉት( ደርጎች)  እንደዚህ ይመስለኛል አሁን ሁሉንም ያለውን ግርማዊነትዎ ያስታውቁን ለኛ እና ይዘዙልን’ ወደ መንግስት ይግባ። ለሌላው የሚሆነውን አኳኋን ሁሉ እኛ አይተን በኋላ እንወስናለን አይደለም የምትሉት; ለልጆቹም ለምኖቹም የሚሆነውን እኛ አይተን እወስናለን። አሁን ግን ሁሉንም ለእኛ ይዘዙልን ነው።

ጃንሆይ፡- እንድናስታውቅ የሚፈለገው ዙሪክ ያቀመጥነው ገንዘብ እንዳለ እንድናውቀው አይደለም;

ል.ራስ.እምሩ፡- እንዲያውቁ ብቻ አይደለም

ጃንሆይ፡- ታዲያስ;

ል.ራስ.እምሩ፡- ያንኑም እንዲሰጠን ነው የሚሉት እነሱ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን።

ጃንሆይ፡- እኮ እዚህ ብቻ ያስቀመጥነው ካለ ይኽንንም አልከፍልም ።

ል.ራስ.እምሩ፡- ….እ;

ጃንሆይ፡- ይኽንንም ዛሬ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር ቆርሰን የምናስቀረው የለም ብቻ ጥርት ያለ አፃፃፍ ባንኮች ናቸውና።

ል.ራስ.እምሩ፡- ቆርሰን የምናስቀረው የለም ካሉ ግርማዊነትዎ አንግዲያው እንዳቀረቡት ሁሉ እንዳሁኑ መወሰንና መፈረም ነዋ የሚያስፈልገው።

ጃንሆይ፡- ምኑን ያንኑ አስታውቁን ለማለት;

ል.ራስ.እምሩ፡- አንዱ አስታውቁን’ ሁለተኛው ወደ ኢትዮጵያ መንግሥት ይዙር።

ጃንሆይ፡-  አስታውቁን እንበልና እንዳለ አዛውሩ እንበል;

አቶ ዮሐንስ፡-  አዎን ይኽ ነው።

ል.ራስ.እምሩ፡- የታወቀም አለኮ።

ጃንሆይ፡- ቀላል ነገር ነው ማንን ማ ይሸፈጠዋል;

አቶ ዮሐንስ፡- ቢገኝ ትንሽም ትልቅም ቢሆን።

ጃንሆይ፡- አለ;

ተፈራ ወርቅ፡- አለ እሱ በልዑል መኮንን ልጆችና በልዑል ሳህለ ስላሴም ስም እንዲሁ አንዳንድ ሺ ይሁን ሁለት ሺ ይሁን ያለው….

ጃንሆይ፡- እኮ ያ ለልጆቹ የተሰጠ ገንዘብ እኮ ነው።

ደርግ፡- ሁለቱ ጋ የልጅ ልጆቹ ሂሳብ መሆኑ ማስረጃው አለ። አንዱ ዌስት ሚኒስትር ባንክ ሌላው ናሽናል ሲቲ ባንከ ነው።

ጃንሆይ፡- ….ከሰጠሁስ በምን ዓመተ ምህረት ነው? ከየት የመጣነው? ያንን የተሠጡትን ገንዘብ ይወረሱ ነው የሚባለው? ጥርት አድርጉና አምጡልን።

ልዑል ራስ እምሩ፡- የተጣራ ነው! የልጆቹም ገንዘብ ቢሆን የእርስዎ ገንዘብ ነውና ያም ጭምር ይወሰዳል ነው የሚሉዎት።

ጃንሆይ፡- ምን በወጣቸው።

ደርግ፡-  የኢትዮጲውያኖች ገንዘብ ነው፤የልጆቹ አይደለም።

ጃንሆይ፡- ልጆቹ ከኢትዮጲያዊነት ተፍቀዋል?

ደርግ፡- ግርማዊነትዎ አሁን በልጆቹ ስም  ውጭ ሀገር ያለው ገንዘብ እርስዎ የሚያዙበት ወደ ኢትዮጲያ እንዲመለስ ፍቃደኛ ነዎት አይደሉም ?ይህን እንዲመልሱልኝ ይህን ብቻ ነው የምለምነው ? ጃንሆይ፡- እኮ ይወረሱ?

ደርግ፡- ልጆቹ ይህን ገንዘብ አያውቁትም ግርማዊነትዎ ነው የሚውቁት።

ጃንሆይ፡- እኔ በነሱ ገንዘብ የማዘው ነሱ ወኪል ሁኜ አይደለም? ባለቤቱ እነሱ ናቸው ። እዚህ ላይ ምን ላድርግ ታዲያ?

ደርግ ፡-ስለዚህ በነሱ ስም ያለው ገንዘብ ወደ ኢትዮጲያ ተመልሶ መንገስት እንዲገለገልበት ቃደኛ ነዎት ወይስ አይደሉም? ጃንሆይ፡- የማዝበት ነው? ደርግ፡- ግልፅ ነገር እኮ ነው ሞግዚት ከሆኑ፤ ባላደራ ከሆኑ የሚያዙበት እርስዎ ነዎት። ጃንሆይ፡- ሞግዚት ነበርኩበት ግዜ አልፏል።

ደርግ፡- ሞግዚት ነበሩበት ግዜ አላለፈም። ልጆቹም ቢሄዱ አያገኙትም።

ጃንሆይ፡- ሞግዚትም ብንሆን በምን ምክንያት ይወሰድባቸው?

ደርግ፡- ምክንያቱ ተነገርዎት እኮ። የኢትዮጰያ ህዝብ አሁን ያለው በታላቅ ችግር ላይ ነው፤ ገንዘቡ መጥቶ ህዝቡ ይጠቀምበት፤ የልጆቹ ጉዳይ ደግሞ ሁለተኛ ጥያቄ ነው። ጥያቄው ገንዘቡ እንዲመጣ ያድርጉልን።

ጃንሆይ፡- የምፈቅደው ምነድነው?

ደርግ፡- ስጧቸው ብለው።

ጃንሆይ፡-የልጆቹን ገንዘብ?በምን ምክንያት ልቅጣቸው?

ደርግ፡- እነሱ አስረድተውናል። ስም ሆነባቸው እንጂ ገንዘቡን አያውቁትም።

ጃንሆይ፡- ስም ሆነባቸው አትበል። እኔ ከፍዬ ሰጥቻለሁ ። አሁን ችግር ከመጣ በፊት የሆነ እንደሆነ  ባለገንዘቦቹ እነሱ ናቸው። በኔ ስም ሆኖ ማዝበት ተገኝቶ እነደሆነ የሚያዙበት ነውና ይሰጠን ካላችሁ ከኢትዮጲ ህዝብ የሚብስብኝ ለም። እኔንም እንደፈጠረኝ፤ ህዝቡንም እንደፈጠረው በህዝቡ እጨክንበት እንደሆነ እግዚአብሄር ያውቃል።

ደርግ፡- እኔ ብቻ ልገልፅ የወደድኩት ህዝብን ወደጭካኔ ባንገፋፋው ጥሩ ነው። እስካሁን ድረስ በጣም በአንክሮና በጥሞና የሚያስብ ህዝብ ነው። ጥሩ ነው። እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

( ጥብቅ ሚስጥር ከቀድሞ ንጉስ  ጋር ጥቅምት 9ቀን 1967)

የውይይቱ ውጤት ፍሬ አልባ  ከሆነ በሁዋላ ደርግ  ንጉ በውጭ ሀገር ያካበቱትን ገንዘብ ወደ ብሄራዊ ጥቅም እንዲመልሱ ቢጠየቁ ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ገለፁ  ሲል መግለጫ አወጣ። ቀጥሎም ደርግ ከህዝቡ ድጋፍ ያጣው በንጉሱ  በህይወት መኖር ነው ነውና መገደል አለባቸው ተባለ። በዚህም መሰረት ነሃሴ 17 ቀን ከሚቀመጡበት ወንበር ስር ኤሌክትሪክ በማገናኘት ለመግደል ተሞክሮ ሳይሳካ ቀረ በድጋሚ ነሀሴ 19 ቀን በግድ በገዳይ ኪኒን ለመግደል የተደረገው ሙከራ በሳቸው አሻፈረኝ ባይነት እና በመጮህ ሰው ስለጠሩ ሳይሳካ ቀረ። በመጨረሻም የነበረውን የግድያ ሁኔታ በግዜው ቦታው ላይ የነበሩ እማኞች ለልዩ አቃቤ ህግ ምስክርነታቸውን በእንዲህ አይነት መልኩ ነበር የገለጹት፡-

“  ጃንሆይ የታሰሩበት ቤት መጀመሪያ ስትገባ አንድ ሳሎን ክፍል አለ። ይህ ሳሎን ሁለት ዘቦች እና የእሳቸው አሽከሮች የሚቀመጡበት ነው። እሱን አልፎ ከፊት ለፊት የጃንሆይ መኝታ ቤት አለ። ከሳሎን በስተግራ መፀዳጃ አለ። በስተቀኝም የተረኛ መኮንን መኝታ ክፍል አለ። የቤቱ ይዘት ይህን ይመስላል።አሽከሮቻው  እዛ ማደራቸውን እንጂ በየትኛው ክፍል እንደሚያድሩ በግሌ አላስታውስም። የሳሎን በር መለስ ይላል እንጂ በቁልፍ አይቆለፍም።ጃንሆይ መኝታ ቤታቸውን ሲፈልጉ ራሳቸው ይቆልፉታል።ካላስፈለጋቸውም ያለቁልፍ ይዘጉትና ያድራል።ከሳቸው መኝታ ክፍል ወደ ሳሎኑ የዘበኞች ወንበር አለ።

ጃንሆይ ሰውን መጥራት ከፈለጉ ዘበኛውን ይጠሩና አለቃህን ጥራልኝ ይሉታል፤ይጠራላቸዋል።አስፈላጊውን ከመኮንኑጋ እንጂ ከዘበኛው ጋር አይነጋገሩም ።የግል አሽከሮቻው ግን የሚተኙት ጃንሆይን ካስተኙአቸው በኋላ ነው።እኔ በ20/12/67 ጠዋት ሁለት ሰአት ገብቼ በጥበቃ ቦታዬ ነበርኩ።ማታም ከመኮንኑ መኝታ ቤት ተኝቼ ማለትም ጋደም ብዬ መጽሀፍ ሳነብ ነበር።ጃንሆይም የብስራት ወንጌል ሬድዮ ዝና ካዳመጡ በኃላ በሰላም መኝታ ቤታቸው ውስጥ ነበሩ። ከምሽቱ ሶስት ሰአት ይሆናል በግምት እራታቸውን አቅራቢዎች አቅርበውላቸው በልተዋል።ከዚህ በኃላ ሰአቱን አላስታውሰውም ሻለቃ ዳንኤል አስፋው ፤እንዳለ ገላንና ሻለቃ የጎራው የሚባል ይመስለኛል 3ተኛውን በደንብ አላስታውሰውም መጡና የውጭ በር ማን እንደከፈተላቸው አላውቅም ግን ዘበኞች ስላሉ እነሱ ከፍተውላቸው ይሆናል ብዬ  እገምታለሁ ፤ በቀጥታ ወደ ሳሎኑ ገቡ።የሳሎኑ ውስጥ ዘበኛ ከነበርኩበት የመኮንኑ መኝታ ክፍል እነ ሻለቃ አስፋው መጡ አለኝ።ከዛ ብድግ ብዬ እነሱ ወደ ቆሙበት መኝታ ክፍሉን ከፍቼ ወጣሁኝ። ሶስቱም ሰዎች ቆመው አየሁና ሰላምታ ሰጠሁዋቸው። መጀመርያ እንዳለ ገላን የጃንሆይን መኝታ ቤት በር ከፍቶ ሊገባ ብሎ ነበር የደረስኩት ። በኋላ ምንም ሳያናግረኝ እንዳለ ገላን በሩን ከፍቶ ሲገባ ተከትሎ ዳንኤል አስፋው ከሻለቃ የጎራው ጋር ገቡ ፤በሩን ዘጉት። በውስጥ ሆነው በግምት ከሰላሳ እስከ አርባ አምስት የሚሆን ደቂቃ ድረስ ቆዩ። በቆዩበት ጊዜ የሚሰማ ነገር አልነበረም። ከላይ ከገለጽኩት ጊዜ በኋላ ተከታትለው ዳንኤል አስፋው’ ሻለቃ የጎራው እነዳለ ገላን ወጥተው  ሄዱ። እኔ ከ ጃንሆይ ምን እንደተፈፀመባቸው ገብቼ አላየሁም። ምክንያቱም ራሳቸው ካልጠሩ መኝታ ክፍላቸው ድረስ መግባት ስለማይቻል ነው። ከዛ እነ ዳንኤል አስፋው ወጥተው እንደሄዱ በቀጥታ ወደ መኝታ ክፍሌ ገብቼ ተኛሁ።

ጠዋትም ጃንሆይን እንዴት እንዳደሩ ሣላይ ለተረኛ መኮንኑ አስረክቤ በሁለት ሰዓት ወጣሁኝ። ስወጣ ቤቱን እንጂ ጃንሆይ በህይወት ይኑሩ አይኑሩ ግን ለይተን አልተረካከብንም። ከዚህ በፊት ማታ እንዳለ ገላን ወደ ጃንሆይ መጥቶ አያውቅም። ዳንኤል አስፋውም ሆነ ሻለቃ የጎራውም መጥተው አያውቁም። ነሐሴ 20 ቀን 1967 ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የመጡት። የጠራቸው ሰው አልነበረም። ራሳቸው ናቸው የመጡት።   የሕክምና መሣሪያ ነገር እዳለ ገላን ይዞ ነበር። ጃንሆይ ግን በሽታ አልነበራባቸውም። ሃኪምም ጥራልኝ አላሉም። በሽታ አልነበራቸውም ያልኩትም  በጤንነት ሲበሉ ሲጫወቱና ሬዲዮ ሲያዳምጡ ስለአመሹ ነው። እኔ የጃንሆይ ሁኔታ ማለት አሟሟት የመመርመርና የማወቅ ችሎታ ባይኖረኝም እንዲሁም ሬሣቸውንም አላየሁም እንጂ በእኔ ግምት ዳንኤል አስፋውም ሆነ እንዳለ ገላን የመጡት ሳይጠሩና ሳይጠየቁ በራሳቸው  ስልጣን ስለሆነ እኔም እነሱን ለመጠየቅ ከአቅም  በላይ በመሆኑና አለቆቼ ስለነበሩ እንጂ የመጡት እና የፈፀሙት ተልዕኮ ጃንሆይን በአደንዛዥ ነገር በመርፌ ወይም በታብሌት ገድለዋቸዋል ብዬ እገምታለሁ። ምክንያቱም ለሞት የሚያደርሳቸዉ ምንም ሁኔታ ስላልነበር። የንጉስ አልባሽ የነበረዉ የእለቱ ተረኛ እሸቱ ተክለማሪያም ዉጭ እንዲያድርና እንዲባረር የተደረገበትን ምክኒያት ለግድያዉ ቅንብር እንዲያመች ተብሎ ነዉ ብዬ እገምታለሁ። ዳንኤል አስፋዉ በሚገባበት ሆነ በሚወጣበት ጊዜ ፊቱን በጣም አኮሳትሮ ነበር። ጃንሆይ ከመኝታቸዉ የሚነሱት እንደራሳቸዉ ፕሮግራም ሲሆን በተለይ በባእላት ቀን ግን ለፀሎት አዘዉትረዉ ጠዋት በ12 እና 12፡30 ይነሱና ፀሎት ያደርጋሉ። በሞቱበት እለት ግን ቀኑ የማርያም እለት ቢሆንም ጠዋት ያልተነሱበት ሁኔታ ትዝ ስላላለኝ በወቅቱ ለምን አልተነሱም ብዬ ኣላስታወስኩም።”

በፌ.ከ.ፍ.ቤት ወንጀል መዝገብ ቀ.1/87( 401/185) ውስጥ የል.ዐ.ሕግ ማስረጃ አስራ አንደኛ ምስክር
በማለት ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ሌላኛው ምስክር በበኩላቸው
በ20/12 67 ተዋት ለተረኛ አሽከራቸው እሸቱ ተክለማሪያም አስረክቤ ወጣሁኝ በዚህ ግዜ ፍፁም ጤነኛ ነበሩ። በ21/12/67 ውጭ ያደርነው ቁርሳቸውን ይዘንላቸው መጣን። እሸቱን ስናገኘውከአጥር ውጭ ስለነበር አዲስ ነገር ስለሆነብን ምነው ትተሃቸው ወጣህ አልነው? ማታ አስወጥተውኝ ነው አለን። እንዴት ይሆናል ብለን በጣን ተደናገጥን ከዛ ቁርስ ይግባላቸው አሉና  እሸቱ አንድ እግሩን ገባ እንዳደረገ ተገድለው አልጋ ላይ ተጋድመዋል።አደራረጉበዘዴና ሆነ ተብሎ የተደረገ ነው። ይህም ተጠቅልለው እያሉ ምግብ ይግባላቸው ያሉት ራሳቸውን የገደሉ ለማስመሰል ነው። ጃንሆይ የሞቱበት ቤት የመርዝ ሸታ ይሸት ነበር። በዚህ ምክንያት በመርዝ እንደገደሏቸው ጠረጠርን። በሌላም በኩል ለበሱት አንሶላ በሰው ሃይል የተሳሳበና የተጨማደደ ስለነበር በአንሶላቸው ገድለዋቸዋል ብለን ተጠራጠርን። በአጠቃላይ ግን በወቅቱ ምንም በሽታ ስላልነበረባቸው ደርጎች እንደገደሏቸው አሳምኖኛል።  በ17/12/67 ነበረው ሙከራ በ19/12/67 የነበረውን ሙከራ ስለማውቅ በ20/12/67 የነበረን ተረኛ አስወጥተው ካባረሩ በኋላ የገደሏቸው መሆኑን አምናለሁ።

በፌ.ከ.ፍ.ቤት ወንጀል መዝገብ ቀ.1/87( 401/185) ውስጥ የል.ዐ.ሕግ ማስረጃ ዘጠነኛ ምስክር

“የኢትዮጲያ መሬትም፣ ህዝብም፣ህጉም በጠቅላላው ንጉሰ ነገስት ከኢየሩሳሌም ንጉስ ከሰለሞንና ከሳባ ከተወለደው ከቀዳማዊ ምኒልክ ነገድ ተያይዞ ከመጣው ከንጉስ ሳህለ ስላሴ ዘር ከተወለደው ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ትውልድ እንዳይወጣ በህግ ተወስኗል!”  የሚለው1923 ህገ መንግስት አንቀፅ 2 እና 3 ላይመለስ ተሸሮ ንጉሱ ተከብረው እና ታፍረው በኖሩበት እና ህዝቡን በመልካምም ይሁን በተቃራኒ መንገድ ባስተዳደሩበት ቤተ መንግስታቸው ህይወታቸው ፍፃሜ ሆነ።

Loo

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s