History

​የአቡነ ቴውፍሎስና የቄስ ጉዲና ግድያ መቼ እና በነማንስ ተፈፀመ?

በተለያየ እምነት ውስጥ ያሉ ነገር ግን ለእምነታቸውና ለእውነት ሲሉ በግፍ የተገደሉ ሁለት ታላላቅ ኢትዮጲውያን አባቶች፡፡

አቡነ ቴውፍሎስ በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ፤ቄስ ጉዲና ቱምሳ ደግሞ የኢትዮጲያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ እየሱስ ጠቅላይ ፀኃፊ ነበሩ፡፡

ሁለቱም የእምነት አባቶች ለቤተክርስቲያናቸው ብሎም ለእምነት ነፃነት በነበራቸው ጠንካራ አቋም ከደርግ ጋር ሲጋጩ በዚህም ምክንያት  ሲታሰሩ እና ሲፈቱ ቆይተዋል፡፡ ይህ ደግሞ በደርግ ሰዎች ጥርስ ውስጥ አስገብቷቸዋል… ጥርስ አስነክሶባቸዋል… እልህ አስይዞባቸዋል…. ቀን እየተጠበቀላቸው ነው፡፡ አንድ ቀን!!

ድህረ ታሪክ

ደርግ ስልጣኔን ይጋፉኛል ወይም ህዝብ ያስነሱብኛል ብሎ የሰጋቸውን እና የፈራቸውን በሙሉ ተራ በተራ “አብዮት ልጇን ትበላለች” እያለ መቀርጠፉን ቀጥሏል፡፡ አንድ ሰው በሰራው ጥፋት ወይንም ወንጀል ፍርድ ቤት ሳይቀርብ መግደል የዕለት ተዕለት ስራው ሆኗል፡፡  በመላው ሃገሪቱ ጫፍ እስከጫ ህጋዊ ፍቃድ ተሰጥቶአቸው የፈለጉትን ሰው በፈለጉበት አንቀው የሚወስዱ ገዳዮችን እና አፋኞችን  “ለምን?” ብሎ መጠየቅ  ምላሹ “ፀረ አብዮተኛ!” ተብሎ መረሸን ነበር፡፡ አንድን በህግ የተያዘ እስረኛን የእስር ፍርድ ወደ ሞት መቀየር የሚችሉ ግለሰቦች ፤ የአብዮት ጠባቂዎች፤የቀበሌ ሊቀመንበሮች፤ የድርጅት ፅ/ቤት ሃላፊዎች በሀገሪቱ ነግሰው ከፍርድ ቤት በላይ ሆነው  ሞት በሀገር ምድሩ ላይ አውጀዋል…. ማንም በሰላም ወጥቶ ለመግባቱ ምንም ዋስትና የለውም…. ሁሉም ቦታ ሞት…..ጭንቀት…… ሽብር…ሀገር በስጋት እየተናጠች ነው…m

በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች … በውስን የመንግስት ባለስልጣናት እና የደህንነት ሰዎች ብቻ የሚታወቁ ድብቅ የሆኑ ‘ቤርሙዳ’  ወይንም ‘ሴፍ ሃውስ’  የተባሉ የመግደያና የማሰቃያ ቤቶች በሚስጥር ተደራጅተዋል፡፡ ወደ እነዛ ቤቶች ውስጥ ገብቶ የሚወጣ ሰው ቢኖር ከላይ የተጠቀሱት ባለስልጣናት እና የደህንነት ስፔሻል ፎርስ ወይንም ገዳይ አባላት ብቻ ናቸው፡፡ ሌላው ህዝብ ከስራው፤ ከመንገድ፤ ከቤቱ ታፍኖ እየተወሰደ ሲገባ እንጂ ሲወጣ ታይቶ አይታወቅም፡፡ለዚህም ነው ‘ቤርሙዳ’ የሚል ስያሜን የተጎናፀፉት፡፡

ከእነዚህ ሚስጥራዊ  ቤቶች አንዱ በቀድሞው ከፍተኛ 12 ቀበሌ 07 በአሁኑ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 የሚገኘው  የልዑል አስራተ ካሳ  መኖሪያ ቤት ይገኝበታል፡፡ ልዑሉ በግዜያዊ ወታደራዊ  ደርግ  ወይም መንግስት አባላት ውሳኔ  ህዳር 14/ 1967 ዓ.ም ከተገደሉት 59 ሚኒስትሮችና ጄነራሎች አንዱ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ያለፍርድ በገደላቸው መንግስት መወረስ ብቻ ሳይሆን ለአንድ ልዩ ተልዕኮም ተመርጧል፡፡ በቤቱ ሊካሄድ ለታሰበው ልዩ ሰይጣናዊ ተልዕኮም በሚመለከታቸው ሃላፊዎች የደብዳቤ ልውውጥ ተጀመረ፡፡  በግዜው የግዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደደር ደርግ ረዳት ዋና ፀሃፊ በሆነው ፍሰሃ ደስታ  እጅ የተፃፈ አስቸኳይ ደብዳቤ  የከተማ ልማት ሚኒስትር ለነበረው ካሳ ገብሬ ደረሰ

—————-

ለጓድ ካሳ ገብሬ፤ የከተማ ልማትና ቤት ሚኒስትር

አዲስ አበባ

 

ቀድሞ የልዑል  አስራተ ካሳ መኖሪያ ቤት የነበረው  ለአስቸኳይ  የመንግስት ስራ የሚፈለግ ስለሆነ መጠነኛ እድሳት ተደርጎለት ጓድ ኮለኔል ተስፋዬ ወልደስላሴ የአጠቃላይ መረጃ ማመዛዘኛና ማከፋፈያ ኮሚቴ ዋና ኃላፊ  በሃላፊነት  እንዲረከቡት እንድታደርጉ አስታውቃለሁ፡፡

ፊርማ

ፍሰሃ ደስታ

የግዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደደር ደርግ ረዳት ዋና ፀሃፊ

ግልባጭ

ለጓድ  ኮለኔል ተስፋዬ ወልደስላሴ

————

ተብሎ ለ ሚኒስትሩ ደብዳቤ በደረሳቸው በአጭር ግዜ ሌላ 2ተኛ  ደብዳቤ ደረሳቸው በወመ.አ/1/1681/71 ይህ  ደብዳቤ  አንደሚከተለው ተፅፎአል፡፡

————

ለከተማ ልማትና ቤት ሚኒስትር

አዲስ አበባ

ስለቀድሞው ልዑል አስራተ ካሳ መኖሪያ ቤት  በቁጥር  ወመአ/1/1561/71 ጥር 19 ቀን 1971 የተሰጠውን ትዕዛዝ እናስታውሳለን፡፡ ይህ ቤት ለወደፊት ከውጭ ለሚመጡ እንግዶች  ማረፊያና ልዩ ልዩ ስራዎች ማከናወኛ ስለሚሆን፤ ለቤቱ የሚያስፈልገው ሁሉ የስራና ቤቶች አስተዳደር ከወረሳቸው ዕቃዎች ተፋጥነው እንዲሟሉና ቤቱን መረጃ ማመዛዘኛና ማከፋፈያ ኮሚቴ  በኃላፊነት  እንዲጠቀምበት ሆኖ የቤተመንግስት አስተዳደርም አንዳንድ መሟላት የሚገባውን ነገር እንዲያሟሉ በዚህ ደብዳቤ ግልባጭ  መታዘዙን እናስታውቃለን፡፡

ፊርማ

ፍሰሀ ደስታ

————

ይህ ደብዳቤ የደረሰው የደህንነቱ ቁልፍ ሰው  ተስፋዬ ወልደስላሴ ጉዳዩን ተከታትሎ እንዲያስፈፅም እና በታዘዘው መሰረት ማስታወሻ ወስደው መፈፀሙን ይቆጣጠሩ በማለት  ኮሎኔል መኩሪያ የተባለ ሰው አዘዘ፡፡

ተስፋዬ ወልደስላሴ በሚመራው መረጃ ማመዛዘኛና ማከፋፈያ ኮሚቴ( ደህንንነት) ስር አብዮታዊ ማዕከላዊ ምርመራ መምሪያ  ወይም ድርጅት የሚገኝ ሲሆን  በማዕከላዊ  ምርመራ ስር ደግሞ ልዩ ኃይል( special force)  ቀደም ሲል ተደራጅቶ ነበር፡፡

እነዚህ በማፈን፤ በመግደል፤ በማሰቃየት እና  ሰው በቁሙ እያለ ሞቱን እነዲመኝ ልዩ ስልጠና የተሰጣቸው ከ ኮማንዶ እና ከአየር ወለድ የተውጣጡ የገዳይ ቡድኖች  ልዑልአስራተ ካሳ ቤት ተቀምጠው  እየተቀለቡ እንዲቀመጡ ተደረገ፡፡ ቤቱን የተረከበው ኮለኔል ተስፋዬ ስለነዚህ ልዩ ስፔሻል ሃይሎች ቀለብ በተመለከተም   በግዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በአብዮታዊ ቋሚ ኮሚቴ ለህዝብ ደህንነት ጉዳይ ኃላፊዎች ቀጣዩ ደብዳቤ  መፃፉን  በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል መዝገብ ቁጥር 1/87(401/85) ውስጥ የልዩ ዐቃቤ ህግ ማስረጃ  ህኤግ33.2 ቁጥርወመአ/1/168/71 አስቀምጦታል፡፡ እነሆ ሙሉ ድብዳቤው፡-

————

በክፍላችን በማዕከላዊ ምርመራ ስለሚገኙት የጥበቃ ጓዶች የምግብ ሂሳብ በቁመማማ/2/480/71/አ.1 ጥር 19 ቀን 1971 የፃፍነውን ያስታውሳል፡፡

አባሎቹን በቅርቡ ከተሰጠን የቀድሞው ልዑል አስራተ ካሳ ቤት ከነበረው ግቢ በአንድነት እንዲቀመጡና ለማንኛውም ግዳጅ/ግድያ/ ቀንም ሆነ ለሊት ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ ስላደረግን የጠየቅናቸው ዕቃዎች ከቤተ መንገስት አስተዳደር ለጥበቃ ስራ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ፅ/ቤት እንዳሉት አባሎች ለምግብ የሚሰጡት 45 ብር ስለሆነ የጠየቅነው ድርጅትና ገንዘብ እንዲፈቀድልን ደግመን በትህትና እናሳስባለን፡፡

ኢትዮጲያ ትቅደም

ፊርማ

ኮለኔል ተስፋዬ ወልደስላሴ

————

የተመደበላቸውን የቀለብ ገንዘብ  በማመስገን ብቻ ያልረኩት ከ50 የማያንሱ  የስፔሻል ኮማንዶ አባላት  የሚመጣላቸውን ግዳይም በአንድ ደቂቃ ፀጥ እያደረጉ አለቆቻቸውን ማስደሰታቸው አልቀረም፡፡ በታዘዙበት ስፍራ በመንቀሳቀስ ሲቪል የደርግ ተቃዋሚዎችን ባልታሰበ ግዜ መግደል ወይም ማፈን ዋና ስራቸውም ነበር ፡፡ ሃላፊዎቹም ከኮሎኔል ተስፋዬ በታች  የማዕከላዊ ምርመራ መምሪያ ኃላፊ ( በኋላ ጄኔራል) ለገሰ በላይነህ የነበሩ ሲሆን  ሚስጥራዊውን ቡድን የሚመራውና በበቂ ወታደራዊ አቅምና የአፈና ኃይል አጠናክሮ በስራ ላይ ለማዋል የተመደበው በወቅቱ ሻለቃ የነበረውና  በታማኝነቱ የሌ/ ኮለኔል ማዕረግ በተሰጠው ዘሪሁን አጋፋሪ በተባለ ሰው ነበር፡፡  ከሱ በታችም ጥላሁን መርጊያ/ ቀስቶ/ አሰልጣንኝ ኮማንዶ፤ ተፈሪ ባልቻ፤ የሺጥላ ይርዳው፤ አለምሰገድ ወ/አማኑኤል፤ ደምሴ ንጉሴ / ሞርሴ/ ልዩ ፀሃፊ ዘውዱ ገ/ ማርያም የነበሩ ሲሆን ከአየር ወለድ የመጡት ደግሞ ተስፋዬ ነጋሽ፤ ግርማ ቅጣው፤ደባልቄ ተፈራ የተባሉ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

የሚገርመው እና የሚደንቀው ነገር በዛ ሚስጥራዊ ግቢ ውስጥ ያ ሁሉ ግድያ እየተከናወነበት  መንግስቱ ኃይለማርያምን  ጨምሮ እነለገሰ አስፋው፤ ሃዲስ ተድላ፤ ተስፋዬ ገ/ኪዳን፤ ተስፋዬ ወልደስላሴፍቅረስላሴ  ወግደረስ ና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ቢያንስ በወር አንድ  ግዜ እየመጡ ይዝናኑበት ነበር፡፡ ይብስ የሚደንቀው በዚሁ ቤት የደህንነት መስሪያ ቤት ያዘጋጀው  የፎቶ ኤግዚቢሽን  በተለያዩ መስሪያ ቤት ሰራተኞች እንዲጎበኝ የተደረገ ሲሆን  በኤግዚቢሽኑ ላይ የቀረቡት ምስሎች በደርግ እርምጃ የተወሰደባቸውና  በህዝብ በይፋ የሚታወቁትን ግለሰቦች ፎቶ ግራፍ ያካተተ ነበር፡፡ በፎቶግራፎቹ አናት ላይም “ፀረ ህዝብ” ወይም  “በኢህአፓነቱ” የሚል እንዲሁም እርምጃ ለመወሰዱ በቀይ ቀለም ኤክስ የተደረገበት ነበር፡፡

አባ ጳውሎስ

አባ ጳውሎስ ወልደማሪያም ውቤ አቡነ ባሲልዮስን በመተካት  እ.ኤ.አ በ1971 ዓ.ም 2ተኛው የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ጳጳስ የነበሩ ሲሆን  የካቲት 9 / 1968 ዓ.ም እንዲያዙ በደርግ በታዘዘው መሰረት ጳጳሱ ከሁለት ቀናት በሁዋላ ተይዘው  በብሄራዊ ቤተመንግስት ውስጥ በእጥፍ  ዘብ ከማንም ሳይገናኙ በጥብቅ ታስረው  እንዲጠበቁ  በኮሎኔል ዳንኤል አስፋው  የደርጉ ዘመቻና ጥበቃ መኮንን ፊርማ የካቲት 11/1968 ታዘዘ፡፡ በትዕዛዙ መሰረትም አባ ቴውፍሎስ በድንገት ተይዘው ታሰሩ፡፡

ዓለም በቃኝ ብለው ነፍስ እና ስጋቸውን ለፈጣሪ አስገዝተው የሚኖሩት እና ውሎ እና አዳራቸው ፈጣሪን በማመስገን በዝማሬ እና በቅዳሴ መሃል የሚያሳልፉት አባት  ያሉበት ቦታ ሰላም ቢያሳጣቸው እና ከለመዱት ህይወት የማይገናኝ ቢሆንባቸው  ከአንድ ወር በሁዋላ መጋቢት 10/1968 ዓ.ም ወደ ገዳም ተልከው እንዲቆዩ ለመጠየቅ ለደርግ የሚከተለውን ማመልከቻ አቀረቡ፡-

————

ለ ኢትዮጲያ ግዜያዊ ወታደራዊ ደርግ የሚቀርብ ማስታወሻ

የዓለም ቤተክርስቲያን  ከኀዋርያት ጀምሮ የተመሰረተቸው በማይናወጥኛ በማይፋለስ መንፈሳዊ ስርዓት መሆኑ በሁሉም የተገለፀና የታወቀ ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ቤተርስቲያንም ህግና ስርዓት በሶስቱ በኒቂያ፤በቆስጠንጥንያ፤ በኤፌሶን ጠቅላላ ቅዱስ ሲኖዶስና ሳይፋለስ ሲወርድ ሲዋረድ በቆየው ህግና ቀነኖ ፀንቶ ኖሯል፡፡ ከተቀደሰችው የኦርቶዶከስ ቤተክርስቲያንም ታላላቅ ስርዓቶች የመጀመሪያውና ተቀዳሚው ቅዱስ ሲኖዶስ ስርዓት ይህ ነው፡፡

አንደኛ  አንድ ፓትሪያርክ በህይወት ካለ ራሱ ተከሳሽ ቢሆንም እንኳን ስራ መሪነትና ሊቀመንበርነት  ካልሆነ በስተቀር  በሌላ ሰው በሚደረግ ስብሰባ  የሚደረግ ውሳኔ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሊሆን አይችልም ፡፡ ሁለተኛ ፓትርያርክ በሞት የተለየ እንደሆነ ሊቃ ጳጳሳት ሙሉ ስብሰባ አድርገው በሹመት ቅድሚያ ምከንያት ከጳጳሳት መካከል ይመርጣሉ እሱ ጊዜያዊ ሊቀመንበር ይሆናል በዚህ መሰረት ካልተመረጠ ግን ምርጫው ህጋዊ ሊሆንና የሲኖዶሱ  ሰብሳቢ ሊሆን አይችልም፣ ሶስተኛ አንድ ፓትርያርክ ሊከሰስና ከመንበሩም ሊወገድ የሚችለው በሁለት ነገር ብቻ ነው 1ኛ/ ኃይማኖቱን የለወጠ፣ የካደ እንደሆነ 2ኛ/የታመመ አዕምሮውን ያጣ፣ ጆሮው የደነቆረ፣አይኑ የታወረ በታለቅ ስጋ ደዌ የተያዘ እንደሆነና የመዳን ተስፋ ከሌለው ከመንበሩ እንዲወገድ ይደረጋል፡፡

ይህንንም መርምሮ አጣርቶ ተገቢውን ውሳኔ  ማሳለፍ የሚችል ከታላላቆች ፓትሪያርኮች ሶስት በተገናኙበት ያገሩ ቅዱስ ሲኖዶስ በሙሉ በፓትርያርኩ ሰብሳቢነት በሚደረግ ከፍተኛ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ በአሁኑ ግዜ በኢትዮጲያ  ቤተክርስቲያን ላይ በመንግስት አሰራር ቀጥታ ስልጣን የተሰራውና በመሰራት ላይ ያለው አሰራር ከ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ህግና ስርዓት ውጭ መሆኑን ኦርቶዶክሳዊያን አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ የማይቀበሉትና  የሚቃወሙት ፤ የሚያወግዙት መሆኑ  ታውቆ አስፈላጊውን እርምጃ ወስዶ ከታሪክ ወቃሽነት ይድን ዘንድ በራሴና በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስም አሳስባለሁ፡፡

አባ ጳውሎስ

የኢትዮጲያ ፓትርያርክ

————

ይኸውም ጉዳይ እስኪወሰን ድረስ የኢትዮጲያ  ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ህግ በሚፈቅደው መሰረት መንግስት በሚፈቅደው  ገዳም እንድቆይ ይደረግልኝ፡፡

ይሁን እንጂ የደርግ ምርጫ ሌላ ነበር፡፡

ቄስ ጉዲና ቱምሳ


በኢትዮጲያ  ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስትያናት ( የኢትዮጲያ ወንጌላውያን አብያተ ቤተክርስትያን፣ የኢትዮጲያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያንና የኢትዮጲያ  ካቶሊካዊት ቤተክርስትያንን ጨምሮ) በጋራ  በሆኑ ጉዳዮቻቸው ላይ አብረው የመስራትን ራዕይ ፀንሶ የተነሳው ጉባኤ በቄስ ጉዲና ያላሰለሰ ጥረት  ህልውና  ያገኘ  ቢሆንም  ለህልፈተ ህይወታቸው ምክንያት ከሆኑት ነገሮች  መካከል  ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ የመተባበር ጉባኤው መስከረም 1969 ዓ.ም  ሲመሰረት  ከመንግስት ዕውቅና የጠየቀው ግን  በ1971 ዓ.ም  እንደነበር  ሰነዶች ያወሳሉ፡፤ በመተባበር ጉባኤው ውስጥ የነበሩ  የሃይማኖት ተወካዮች  እንደሚናገሩት “የእውቅና ስጡን” ጥያቄው  ለመንግስት የሚዋጥለት  ሆኖ አልተገኘም፡፡

በወቅቱ በርካታ የውጭ መገናኛ ብዙሃን  በኢትዮጲያ  ውስጥ  የሃይማኖት ነፃነት እንደሌለና  አማኞችም እየታሰሩ ፤ እየተሰቃዩና  እየተገደሉ እንዳለ ቢዘግቡም  መንግስት ይህን ዘገባ ለማስተባበል ከፍተኛ ጥረትና ሙከራ  አድርጓል፡፡ በ1970 ዓ.ም ሁኔታውን  እንዲመረምር በመንግስት የተሰየመው  ኮሚቴ የተለያዩ  የአገር  ውስጥና የውጭ አገራት የሃይማኖት ድርጅት ተወካዮች በተገኙበት  በአፍሪካ አዳራሽ  አንድ ስብሰባ ጠራ ፡፡ በስፍራው የመተባበር ጉባኤ አባላትም ተገኝተዋል፡፡

ስብሰባው የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች  የቀረቡበት አካሄዱም መንግስት በቀደደለት ቦይ የፈሰሰ ቢሆንም በመጨረሻው ተናጋሪ በቄስ ጉዲና ቱምሳ  ንግግር ግን ብርቱ የሆነ ተግዳሮት ነበር የጠበቀው፡፡ ቄሱ በድፍረት በጉባኤው  ላይ የተነገረው ቅጥፈት ሁሉ እንዳሳዘናቸው ከገለፁ በሁዋላ  በኢትዮጲያ ውስጥ  እርሳቸው እስከሚያውቁት ድረስ የሃይማኖት መረገጥና የምዕመናን ስቃይ እያየለ መምጣቱን ስፍራና በታ ጭምር በመጥቀስ የተፈፀመውን ግፍ  ሁሉ እየዘረዘሩ ባስቀመጡት መረጃ ሀቁን አወጡ፡፡ የስብሰባው አካሄድ ከታለመለት ፈር እያፈነገጠ መምጣቱ ያስደነገጠው ደርግ ሁኔታዎችን በማረጋጋት  ጉባኤውን የበተነ ቢሆንም ቄስ ጉዲናን ግን በመንጋጋው ለማድቀቅ ጥርስ ውስጥ አስገባቸው፡፡

የመንግስት አካላት ቄስ ጉዲናን በመጥራት  አብዮቱን መቃወማቸውን እና ተቃዋሚ የፖለቲካ እንቅስቃሴም የሚደግፉ መሆናቸወን ከገለፁላቸው በሁዋላ ያም ሆኖ ከመንግስት ጋር የሚተባበሩ ከሆነ በአንድ አለም አቀፍ ኃላፊነት ቦታ ላይ እንደሚመደቡ በመግለፅ ሊያግባቧቸው ቢሞክሩም  እሳቸው ግን አሻፈረኝ  አሉ፡፡ በአንድ ወቅት ለሴት ልጃቸው በፃፉት ደብዳቤ ላይም  “ከዚህ የሰውን መብት በሰፊው ከሚረግጥ መንግስት ጋር ከመስራት ሞት ይሻለኛል”  በማለት መግለፃቸው የአላማቸውን ጥንካሬ የሚያሳይ ሆኖ  እናገኘዋለን፡፡

የመጨረሻዎቹ ቀናት

በልዑል አስራተ ካሳ ሚስጥራዊ ግድያ ቤት ውስጥ ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ በሹፌርነት ይሰራ የነበረ እና በወ.መ.ቁ 206/90 የልዩ አቃቤ ህግ 32ኛ ምስክር የነበረ ግለሰብ በአይኑ የተመለከተውን ምስክርነቱን በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 6ኛ ችሎት  በእንዲህ መልክ ነበር ያቀረበው፡-

————

ስለ ቄስ ጉዲና ቱምሳ ትዝ የሚለኝ  ይፈለጋሉ እና  ክትትል ተደርጎ እንዲያዙ ሻለቃ ዘርይሁን አጋፋሪ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ የደህንነት  አባላት በግል መኪና ጭምር ቀንና ማታ ክትትል ያደርጉ ነበር፡፡ በ1971 ክረምት ውስጥ  በእኔ መኪና  አስር አለቃ  አለምሰገድ ወ/ አማኑኤል፣ ሻንቆ ጉተማ ፣ተፈሪ ባልቻ እና ሌሎች ለግዜው ስማቸውን የማላስታውሳቸው  ሆነው ቄስ ጉዲናን ለመያዝ ጉዞ ተጀመረ፡፡ ከአስመራ መንገድ ቤታቸው ከባለቤታቸው ጋር ወጥተው  ጉዞ እንደጀመሩ በመኪና ክትትል ተደረገ፡፡ ቄስ ጉዲና ከአንድ ቤት ግቢ ገቡ፡፡ አንዱ አንዱን በር ሌላው ሌላውን በር ይዞ አድፍጦ ጠበቃቸው፡፡ በግምት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ሲሆን  ከግቢው ሲወጡና  ጉዞ ሲጀምሩ አንዱ መኪና ከፊት  አልፎ መኪና ዘጋባቸው፡፡ሻንቆ ጉተማ ወረደና  መሳሪያ ደቀነባቸው ቄሱ  ከመኪና  እንደወረዱ አፍነው  ሌላ መኪና ውስጥ አስገቧቸው፡፡ ሻንቆ ጉተማ  በፔጆ 404 መኪና የቄስ ጉዲናን  ባለቤት ይዞ  በሌላ በኩል ፤ተፈሪ ባልቻ በሚነዳት ቮልስ ውስጥ ቄሱን አስገብተው እኔን የቄሱን መኪና ንዳ ብለውኝ (ትዝ ይለኛል ማዝዳ 818 ሞዴል ይመስለኛል) በተለያ አቅጣጫ ጉዞ ተደረገ፡፡ እኔ መኪናዋን ለብቻዬ እየነዳሁ ወስጄ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ አጠገብ አቆምኳትና መስኮቱን ከፈት አድርጌ ቁልፉን ወደ ውስጥ ጣልኩት፡፡ ይህን መመሪያ የሰጠኝ ዘሪሁን አጋፋሪ ነው፡፡

በማለት ምስክርነቱን ሲቀጥል

ከዛም ወደ ልዑል አስራተ ካሳ ግቢ በሰርቪስ አደረሱኝ ፡፡ ግቢ ስደርስ ከዘርይሁን አጋፋሪ ቢሮ ጎን ላይ ቀደም ሲል ምሽግ ተብሎ በተቆፈረ ቦታ ላይ  ከነልብሳቸውና ከነ ጫማቸው ሲቀበሩ እና አፈር ሲመለስባቸው  ደረስኩ፡፡ አፈር እየተመለሰባቸው የነበሩት ሟች ቀደም ሲል የተያዙት  ቄስ ጉዲና ቱምሳ ነበሩ፡፡  ሲቀብሯቸው የነበሩት ደግሞ ተፈሪ ባልቻ፣ ዓለምሰገድ ወ/ ኣማኑኤል፣ ጥላሁን መርጊያ  እና ዘሪሁን አጋፋሪ ነበሩ፡፡ በዚሁ  ወቅት  በሶስት የተለያዩ ግዜያት  ከአራት  ኪሎ ቤተመንግስት  እስር ቤት ወደዚህ እየተጠሩ መጥተው  ዘሪሁን አጋፋሪ ቢሮ ካስገቧቸው በሁዋላ  በገመድ ታንቀው ተገድለው ተደርድረው እስከማታ  ቆይተው ለምሽግ የተባለው ስፍራ አንድ ላይ ከተቀበሩት ውስጥ  አባ ቴውፍሎስ ወልደማርያም፣ ዶ/ር ሃይሌ ፊዳ፣ ዶ/ር ንግስት አዳነ፤ጄኔራል ሳሙኤል እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

————

32ኛ ምስክር በበኩሉ

————

ምሽት 3፡00 ላይ  ጥላሁን መርጊያ ወደ ዋናው በር ጥበቃ ቦታ መጥቶ ጠርቶኝ ወደ ቪላው ቤት ይዞኝ ሄደ፡፡ እንደገባሁ ከሻለቃ ዘሪሁን አጋፋሪ ቢሮ ቀጥሎ ከሚገኘው ቢሮ ቀጥሎ ከሚገኘው  ክፍል ውስጥ ከሌሎች አባላት ጋር እንድንቆይ  አደረገ፡፡ በኋላም  ሁላችንም ሰብሰብ አድርጎ ብዛታችን35 እንሆናለን፤ በአስቸኳይ እዚህ ውስጥ ያለውን ዕቃ እያወጣችሁ በተቆፈሩት ጉድጓዶች ውስጥ እንድትቀብሩ ሲል አዘዘን፡፡  በዚሁ መሰረት  የተባለው በርተከፍቶ ስንመለከት ቀን በመኪኖች ሲጓጓዙ  የዋሉት እነአባ ቴውፍሎስ ወ/ማርያም እና ብዛታቸው 17 የሚሆኑ ሲቪሎች እና በውል ያላወኳቸው የጦር እና ፖሊስ አባላት በገመድ ታንቀው አንዱ በአንዱ ላይ ተደራርበው  ለማየት ቻልኩ፡፡ እነዚህ የተገደሉ ሰዎች አባ ቴውፍሎስን ጨምሮ ለምሽግ ተብሎ በተቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ  ተቀበሩ፡፡

በሚቀጥለው ቀን ከምሽቱ በግምት 4፡00 ሰዓት  ገደማ እኔና  ሌሎች ጥበቃ ባልደረቦቼ ከምናድርበት ቦታ ድረስ በቀለ ሞላ የተባለው መጥቶ ለስራ ትፈለጋላችሁ ብሎ ብዛታችን 10 የማናንስ ሰዎችን ወደ ቪላው ቤት ዋናው በር ወሰደን እንደደረስንም  የመካነ እየሱስ ፀሃፊ  በዓይን የማውቃቸው ቄስ ጉዲናን በተመሳሳይ ገመድ አንቀው በረንዳው ላይ አጋድመዋቸው ተመለከትኩ፡፡ ለመቅበር በምንሸከምበት ግዜ የእያንዳንዱ አስክሬን አንገት ላይ ከፕላስቲክ የተሰራ ሰማያዊ ቀለም ያለው  ገመድ ተቋጥሮ ነበር ፡፡ ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡

————

በስልጣኑ ለመጡበት ወይንም ስልጣኔን ይነቀንቁብኛል ብሎ ለገመታቸው ሁሉ ምህረት የማያውቀው ቡድን በእጃቸው መሳሪያ ሳይሆን መስቀልና ለወንጌል ማስተማሪያ መፅሃፍ ቅዱስን ይዘው እውነት የተናገሩትን ሁለት አባቶች በእንዲህ አይነት ጭካኔ ግድያን አስፈፀመባቸው፡፡

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s