Arts

​የ ‘ኢትዮጵያ’ አልበሜ ዋናው አላማ ኢትዮጵያዊነትን ከአደጋ ማዳን ነው -ቴዲ አፍሮ

(Ethionewsflash/ AP)
ጥያቄ: የአዲሱ ‘ኢትዮጵያ’ አልበምህ ዋና መሰረት እና ለመዳሰስ የሚሞክራቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

ቴዲ: አርእስቱ ‘ኢትዮጵያ’ እንደመሆኑ መጠን ዋናው አላማ ኢትዮጵያዊነትን ከአደጋ ማዳን ነው። ይህ አልበም በዚህ አይነት ሀሳብ ላይ እንዲያተኩር የፈለግኩበት ምክንያት አንድነታችን አስፈላጊ ስለሆነ ነው። ብዙ አመት ተደክሞበታል። አሁን እንደሚታወቀው በሀሳብ ከመደራጀት ይልቅ በዘር መደራጀት ይታያል። ያ ደግሞ አዝማሚያው ወደ አደጋ ያመጣው ይመስላል። እና ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊነትን ማዳን አላማ አድርጎ ነው የተሰራው።


ጥያቄ: እንዳልከው አንዳንዶቹ ስራዎችህ በኢትዮጵያውያዊነት እና በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያጠነጥናሉ። እዚህ ላይ በጣም ትኩረት ለማረግ የፈለግክበት የተለየ ምክንያት ምንድን ነው?
ቴዲ: አገር እንግዲህ ብዙ ግዜ የሚቆመው ለሀገር ባለውለታ በሆኑ ሰዎች እና ብዙ የህብረተሰቡ አካላት በሚሰሯቸው ተግባራት ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያዊነት በነፃነት የመኖር ምልክት ነው። ድል ለማግኘት ምኒሊክን የመሰለ ጥሩ መሪ ያስፈልጋል። እንደገና ደግሞ እንደ ሀይለስላሴ ያሉ ትላልቅ ነገስታት ከአለም መንግስታት ጉባኤ ጀምሮ ያደረጓቸው አስተዋፆዎች እና የነበራቸው ተቀባይነት፣ ለሀገራቸው የሰሩት ተግባር ሳይደመር ኢትዮጵያ የምንላት ሀገር ልትኖር አትችልም። ይህ እንዳለ ሆኖ ምንግዜም ነገስታት የሚወክሉት ህዝብን እንደመሆኑ መጠን ከስሮቻቸው ደግሞ ያሉ ብዙ ባለውለታዎቻችንን እብሮ ለማየት የሚያስችል ትልቁ መስኮት ከፊት ያሉት ሰዎች ናቸው። በዚህ መሰረት ምልክቶች ካልተበረታቱ እና የሚገባቸውን ክብር ካላገኙ የሚቀጥለው ትውልድ ጥሩ ተግባር ለመፈፀም የሚያነቃቃ መሳርያ አያገኝም። ሁለተኛ ደግሞ ባለፉት ጥቂት አመታት ታሪክ የሚባለው ነገር እና ብሄራዊ ስሜት በብዙ ሁኔታ ፈተና ውስጥ ወድቋል። ስለዚህን ይሄንን አጠናክሮ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የትውልድ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል። እኔ ደግሞ የዚህ ትውልድ አካል እንደመሆኔ መጠን ያንን ተግባር ለመፈፀም ነው የሞከርኩት። አፄ ቴዎድሮስ ደግሞ እንደሚታወቀው በአንድ ወቅት ዘመነ መሳፍንት በሚባለው እና ኢትዮጵያ በጎሳ መሪዎች እና በጎበዝ አለቆች ተከፋፍላ በነበረችበት ወቅት ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ህልም ይዞ ተነስቶ ከውጪ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም በገጠመው ብዙ የመረዳት ችግር ባክኖ የወደቀ ትልቅ ጀግና ነው። ከምንግዜውም በላይ ደግሞ የእርሱ መንፈስ አሁን አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ ምክንያቱም አስተሳሰባችን አገር ማከል አለበት። 

ጥያቄ: በርካታ ሰዎች አዲሱ አልበምህ ምናልባትም ኢትዮጵያ ውስጥ ከተሰሩ የሙዚቃ ስራዎች በብዙ ረገድ የገዘፈ እና በሽያጭ ረገድም ሪከርድ የሰበረ ነው ይላሉ። ምን ያህል አልበም ታተመ እና ተሸጠ? አንተስ ይህንን ያህል ተቀባይነት ገምተህ ነበር?
ቴዲ: እውነት ለመናገር ከተለመደው ውጪ ይመስላል። ምን ያክል ኮፒ እንደተሸጠ ግን ለመግለፅ የሚችሉት አሳታሚዎቹ ናቸው። እና ስራው ወደ 600,000 ኮፒ አካባቢ ታትሞ እንደነበር አውቃለሁ። ይሁንና አሁን ያለውን ያክል ተቀባይነት ያገኛል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር።
ጥያቄ: ሁላችንም እንደምናውቀው ኢትዮጵያ በአሁን ሰአት ለየት ባለ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ትገኛለች። ብዙ ሰዎች ደግሞ ቴዲ አፍሮ በቀደምትም ይሁን በአሁን ስራዎቹ የፖለቲካ መልእክቶችን አስተላልፏል ይላሉ። በስራዎችህ ላይ እነዚህን መልእክቶች አስተላልፈሀል? ከሆነስ እነዛ መልእክቶች ምንድን ናቸው?
ቴዲ: በኔ እምነት ብቻም ሳይሆን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ማንም ሰው ከፖለቲካ ውጪ ሊሆን አይችልም። የፖለቲካዊ ጉዳይን ማንሳት ደግሞ እንደ ኩነኔ የሚታይ ነገር መሆን የለበትም። ሁላችንም ጉዞአችን አንድ እንደመሆኑ መጠን የኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጉዳይ እንደ ዜጋ ይመለከተናል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ማተኮር መለመድ እና መበረታታት አለበት። የነገሮቹ ጥልቀት በአልበሙ ላይ በዝርዝር ተጠቅሰዋል።
ጥያቄ: የአንተ በጣም ከፍተኛ አድናቂ እና ተከታታይ የሆነ ህዝብ የመኖሩን ያክል ሌሎች ደግሞ አንተን በብዙ መስኩ የሚወቅሱ ወገኖች አሉ። አንዳንዶቹ የተወሰነ የሀገሪቱ ህዝብ ላይ ብቻ ያተኮረ አርቲስት ሲሉህ ሌሎቹ ደግሞ የኢትዮጵያን ታሪክ በቅጡ ያልተረዳ ይሉሀል። ለዚህ ያንተ መልስ ምንድን ነው?
ቴዲ: እንግዲህ የሁላችንም መገለጫ ኢትዮጵያዊነት ነው። ኢትዮጵያዊነት የሚሻክረው ክፍል ደግሞ ተፈጥሯል። ይህንን እውነት መቀበል ያስፈልጋል። እና ሁሉንም ለማስደሰት አይቻልም። ጠቃሚውና የሚያስፈልገው መንገድ የትኛው ነው ብሎ ባመኑበት ነገር ላይ ማተኮር ነው የኔ አካሄድ። በዚህም መሰረት የተለያዩ አቀባበሎች ይኖራሉ። እንዳየኸው ግን ሁሉም ሰው ኢትዮጵያዊነት ውስጡ ያለ፣ የነበረ ነው። ኢትዮጵያዊነት ሊጠፋ የሚችል ነገርም አይደለም። እንደ ሀይማኖት የጠለቀ ነው። ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ሚስጥር አለው። ኢትዮጵያዊነት ረጅም መሰረት ያለው ነው። ይህንን ካለመረዳት አብረን ባደረግናቸው ብዙ መልካም ነገሮች ላይ መስማማት ስንችል፤ አብረን ባጎደልናቸው ነገሮች ላይ ዝም ብለን ግዜ ማጥፋት ጠቃሚ አይደለም። እኔ ልጅ ወልጃለሁዝ፤ አሁን አራት አመት ሆኖታል። ይሄ ልጅ ከፍቅር እና ከጥላቻ የቱ እንደሚሻል ብጠይቀው የሚነግረኝ ስለ ፍቅር ነው። ያንተም ልጅ ሊነግርክ የሚችለው ስለ መከፋፈል ሳይሆን ስለ አንድነት ነው። ይሄንን ልጆች ሊመልሱት የሚችሉትን ጥያቄ በእድሜ በልፅገን እንኳን በማንግባባቸው ነገሮች ላይ በማተኮር ነው የብዙ ወጣቶች ህይወት እንዲደናቀፍ የሆነው። የቀደሙት አባቶቻችን ግን ከዚህ የተሻለ ቅርፅ የነበራቸው ናቸው። ለዚህ ነው እነሱ ላይ ያተኮረ ስራ የምሰራው። ሁሉም የራሱን አመለካከት የመግለፅ ደግሞ ተፈጥሮአዊ መብቱ ነው። በማንኛውም ሁኔታ ግን ሁሉንም ማስደሰት ባይቻል በተቻለ መጠን ሁሉንም የሚያግባባ ቅርፅ ይዤ ለመቅረብ ነው የሞከርኩት። 
ጥያቄ: ወደፊት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ ሀሳብ አለ? 
ቴዲ: (ከረጅም ዝምታ በሁዋላ) እስቲ ባለሁበት ስራ ልክረምና የወደፊቱን ደግሞ አብረን እናያለን።
ጥያቄ: አልበምህን ከሰራህ በሁዋላ ሴንሰር ተደርጎ ነበር የሚል ወሬ በቅርቡ ሰማሁ። ትክክለኛነቱን ታረጋግጥልኛለህ?
ቴዲ: አላጋጠመኝም። እንደጨረስኩ ነው ያወጣሁት። 
ጥያቄ: ይህንን ‘ኢትዮጵያ’ አልበም ስትሰራ ትልቁ ተግዳሮት ምንድን ነበር?
ቴዲ: በአጭር ግዜ ውስጥ አለቀም ባይባልም በሁለት አመት ነው የስቱድዮ ስራው ያለቀው። ከዛ በፊት እቤት ውስጥ ዜማ እና ግጥም ማዘጋጀት ነበር። ግን በየቀኑ ነበር የምሰራው። እና ከባዱ እንቅልፍ ማጣት እና የአመጋገብ ችግር ገጥሞኛል። ከዛ በተረፈ በጥሩ ሁኔታ ደስ ብሎኝ ነው የጨረስኩት። 
ጥያቄ: አልበምህን ተከትሎ ሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ኮንሰርት እያሰብክ ነው? 
ቴዲ: ወደፊት ይኖራል። አሁን ለግዜው ግን ከዛ ሀሳብ ትንሽ ገለል ብሎ እረፍት ያስፈልጋል። በሚመጣው ኮንሰርት ግን ከበፊቱ በተለየ እና ከፍ ባለ ፐርፎርማንስ ለማካሄድ አስበናል። ይሄ ደግሞ ግዜ ይፈልጋል።
ጥያቄ: ከዚህ በፊት የተወሰኑ ኮንሰርቶችህ በተለያዩ ምክንያቶች በመንግስት ሀላፊዎች ትእዛዝ እንዲሰረዙ ተደርገዋል። ይህ ነገር በድጋሚ ይከሰታል የሚል ስጋት አለህ?
ቴዲ: ብዙ ግዜ የዚህ አይነት ነገሮች ሲደጋገሙብህ የምትለማመደው የስሜት ማመጣጠን አለ። ከዛ በተረፈ እንደ ዜጋ ደግሞ መከልከሉ ተገቢ አይደለም። ወደፊትም ያለ በቂ ምክንያት መከልከል ተገቢ አይሆንም። ይሄንን የሚመለከተው ክፍል ሊያስብበት ይገባል። 

እንደማንኛውም ሙዚቀኛ ሙዚቃችንን ለማቅረብ ተገቢው ፈቃድ ሊሰጠን ይገባል። ለቀደመው ሁኔታም የተጠየቅነው ይቅርታ የለም። ብዙ ኪሳራዎች ነበሩ። ምናልባት ሞራል ጋር አልደረሱ ሊሆን ይችላል ግን በብዙ መልኩ በማቴርያል ጎድቷል። ይህ ደግሞ ተገቢ አይደለም። 
ጥያቄ: በአሁን ሰአት በኢትዮጵያውያ ያለውን የማህበረሰብአዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዴት ትመለከተዋለህ? በአንተ አስተያየት በእነዚህ መስኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየሆነ ነው? 
ቴዲ: ሀገር የትውልድ ቅብብል ውጤት ነው። ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል። የኔ አባቶች የከፈሉት ዋጋ እንዲህ በቀላሉ የሚጠቀስ አይደለም። በጣም ጨዋ ሰዎች ነበሩ። ግንዛቤያቸው በጣም ሰፊ ነበር። የመረዳት አቅማቸው በጣም ከፍተኛ ነበር። በጣም የሰለጠኑት ሀገራት ላይ የነበሩትን ሰዎች የሚፈትሽ ስራ ሰርተዋል። በጦር ሜዳ ብቻ ድል ያደረጉ ሰዎች ሳይሆኑ የመንግስታቱን ማህበር ጭምር የፈተኑ፣ ለሀቅ የቆሙ እና በወረቀት ላይ የተፃፈን ነገር ለማስፈፀም የፀኑ ጨዋ ሰዎች ነበሩ። ፈትሸዋቸዋል! በርብረዋቸዋል! እንደዚህ አይነት አባቶች ክብር ሳይሰጣቸው የምንኖርበት ሀገር ላይ እንደነዚህ አባቶች አይነት ልጆች ሊፈጠሩ አይችሉም። የሰው እዳ እየበላን ሀገር ለማስቀጠል አይቻልም። ይህ ነው እንደ ሀገር የገጠመን ችግር። ወጣቶች ወደየት እንደሚሄዱ የሚያሳይ ያለፈው ክፍል እነሱ ላይ የሚያተኩር አካሄድም የለውም። ስለዚህ በመጀመርያ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ሀገር ማዳን ነው። 
ጥያቄ: በኢኮኖሚ መስኩስ ምን ይታይሀል?
ቴዲ: ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚያስፈልገውን ነገር ለማድረግ ህዝብ መተባበር አለበት። አድዋ ላይ በአንድ ላይ ያዘመትከውን ሀይል በዛ ሀይል ወደ ልማት ለማሳተፍ ይቻላል። መንገዱም ይሄ ነው። ግን የአካሄድ ጉድለት አለ። የሚያሳዝን ትውልድ ነው። የዛ ትውልድ አካል ስለሆንኩኝ ነው እንደዚህ አይነት ጉዳይ ላይ ለማተኮር ግድ ያለኝ። 
ጥያቄ: ለኢትዮጵያ ያለህ ምኞት ምንድን ነው? ወደፊትስ የት ደርሰን መታየት አለብን ትላለህ?
ቴዲ: ኢትዮጵያ ልጆቿ የተባበሩባት ሀገር እና ለሀገር የለፉ ሰዎች የሚከበሩበት ሀገር እንድትሆን እመኛለሁ። የሚያሳዝነው ግን አፍሪካን አንድ ለማድረግ የሞከረ ህዝብ ለራሱ አንድ መሆን አቅቶት ስቃይ ውስጥ ነው ያለው። በሚያስገርም ሁኔታ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ የሚባል ሀገር ቁጭ ብለው የተባበሩ ህዝቦችን፣ ገና መብላት ያቃተን ህዝቦች ላይ እንደገና መከፋፈል የሚሰብኩ ብዙ ህዝቦች አሉ። መብታቸው ሊሆን ይችላል፤ አደገኛ መሆኑ ግን ሳይነገር አይታለፍም። እኛ ሰላም እንፈልጋለን።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s