በተወዳጅ መፃህፍት ታሪኮች ላይ ተመስርተው በመሰራታቸው ዝናቸው የገነነ አለም አቀፍ ፊልሞች ጥቂት አይደሉም፤ The God Father, Color Purple, The Shawshank Redemption, Schindler’s List, . . .ወዘተ እያልን ብዙ መጥቀስ እንችላለን።
እጅግ ተወዳጅ ስራዎችን ካፈራው የኢትዮጵያ የስነ-ፅሁፍ ውስጥ ግን ሙያዊ በሆነ ብቁ አሰራር ወደ ፊልም የመቀየር እድሉን ያገኙ ስራዎች የሉም ማለት ይቻላል።
በዚህ ረገድ በቅርቡ ስራ በጀመረው Arts TV ላይ “ትዕይንተ መፃህፍት” በሚል ርዕስ ከተወዳጅ የአማርኛ መፃህፍት ማራኪ ገፆችን በመውሰድ ከ30 ደቂቃ ባልበለጠ ርዝማኔ ወደ ፊልም በመቀየር የቀረቡት ስራዎች በተለየ ሁኔታ አስደንቀውኛል። በፊልም ስራ ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎችም አይነተኛ ማሳያ እንደሚሆኑም አምናለሁ። ካለንበት የፊልም አሰራር ጥበብ ደረጃ አንፃር ሲኒማቶግራፊው፣ ቦታና ተዋንያን አመራረጡ፣ አልባሳቱ፣ ዳይሬክቲንጉና ኤዲቲንጉ እንዲሁም በእንደ ደበበ እሸቱና ደረጀ ሀይሌ አይነት ድንቅ ባለሙያዎች የቀረበው ትረካ እንከን የማይወጣለት ነው። እዚህ ላይ ስለ እርሷ ባላውቅም ዳይሬክተሯን ቅድስት ይልማን ሳያደንቁ ማለፍ ንፉግነት ነው። ሆኖም ቴሌቪዥኑ እነዚህን ፊልሞች ከቀረቡት በጣት የሚቆጠሩ ስራዎች በላይ ለምን ማስቀጠል እንዳልቻለ ጥያቄ ሆኖብኛል።
ከ “ትዕይንተ መፃህፍት” እነዚህን ከ በአሉ ግርማ “ከአድማስ ባሻገር” እና ከ አሌክስ አብርሃም “ዙቤይዳ” መፃህፍት ተወስደው የተሰሩትን ቪድዮዎች እንዲመለከቷቸው ተጋብዘዋል።