Arts

“የበረሃው ሲሳይ!”

በዮሐንስ ሞላ

ተስፋዬ ወ/ስላሴ የላከልኝን የጽሁፍ መልእክት አገኘሁ። መስፍን 9ኛው የተባለ ሰው በጂጂ አባይ ዙሪያ የጻፈው ነው። ያው ብዙ ሰው የጂጂ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ተወካይ የሚያደርገኝ ነገር አለ አይደል? ሃሃሃ… (I like that part!) መጀመሪያ እንደማንኛውም አልፎ ሂያጅ ጽሁፍ ነበር ያየሁት፤ ከተስፍሽ ጋር ስናወራ ግን ከዘሀበሻ ገጽ ላይ እንዳገኘው ስለገለጸልኝ፣ የአባይ ጉዳይም አንገብጋቢ ስለሆነ፣ ብዙ ሰው እንደሚያነበው በማሰብ፥ ብዙ ሰው ካነበበው ደግሞ፥ የአንድ ወገን ግራ መጋባት ወይም በጸሐፊው ስለታመነ ብቻ የሚታመን ሆኖ ከሚቀር፣ (ምናልባትም ፀሐፊው የጂጂ አድናቂ መሆኑን በመግለጹ እና፣ ነገሩን “እውቀት” አድርጎ የወሰደው በመሆኑ፥ በቁም ነገር ተወስዶ፣ ከትውልድ ትውልድ ሊተላለፍ የሚችል ክፍተት፥ እውቀት መሰል ግራ መጋባት፥ ጥሎም ሊያልፍ ይችላልና) አንጻሩን ከጎን ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑን በማመን ይኽንን ጽሁፍ ለመጻፍ ወሰንኩኝ። ዋናው ጉዳይ ስለናፈቃችሁኝ ለመመለስ ሰበብ ነው።

ይኽን ሳደርግም፥ እንደ ወዳጅ አድናቂ ከማንም ቀድማ በጥልቅ ተመስጦ በወሳኝ የአገር ጉዳይ/ሀብት ላይ ላጋራችን ቁጭት እና የማንቂያ ደወል፣ ምስጋና መቸር ቢቀር አጓጉል ክስ እንዳናቀርብባት ለመከላከልም ነው። ዘፈኑን ከወንዙ ነጥለነው ልንሰማው አንችልምና!

የመስፍን አንኳር መስመሮች
መስፍን “ጂጂ ዘፈኑ ላይ አባይን ከማወደስ በዘለለ ለግብጽ ያደላች ይመስለኛል።” ይላል። ከዚያም በመቀጠል፥ “አባይ ወንዛ ወንዙ ብዙ ነው መዘዙ” ብላ ሀሳቧን ትደመድማለች። መዘዝ መኖሩ እውነትነት ቢኖረውም የማስፈራሪያ ቃና አለው። ካነሳኋቸው ነጥቦች አንጻር በኔ መረዳት መጠን ጂጂ ለግብጽ አድልታብኛለች።” ብሎ ይደመድማል።

የሀሳቡ ተቃርኖ የሚጀምረው፥ “መዘዝ መኖሩ እውነትነት ቢኖረውም የማስፈራሪያ ቃና አለው” ከማለቱ ነው። በመጀመሪያ ሙዚቃው የተሰራው አንጀት በሚበላ የፔንታቶኒክ ቅኝት ነው። እንጂ በጩኸት፣ በፉከራ ወይ ቀረርቶ አይደለም። በቀላል ምሳሌ ብናየው፥ “አንተ” የሚለው ቃል፥ ለፍቅርም ለቁጣም ለንቀትም እንደሚሆን ቃላቱን በተለያየ ድምጽ ከአፋችን ማውጣት እንችላለን። ከሚባለው ነገር እኩል ወይም በላቀ፣ አባባሉ እና ዐውዱ መልእክቱን ይወስነዋል።

በዚህ ረገድ፥ አባይ የተዜመው በጣም ቁጭታዊ እንጉርጉሯዊ በሆነ ድምጽ፣ በመብሰልሰል ስሜት ነው። ይኽንንም ቁዘማ አጽንኦት ስትሰጥ ቃላት ትደጋግማለች “የበረሃው ሲሳይ!” እና “አባይ” የሚሉትን በመብሰልሰል ስሜት ሆና ትደጋግማቸዋለች። በስነ ግጥም እንዲህ አይነት የቃላት ድግግሞሽ ምክንያታዊ ተደርገው የሚወሰዱባቸው አግባቦች አሉ።

ጂጂ የቃላት ችግር ያለባት እንዳልሆነች በበርካታ ስራዎቿ ተደንቀን መስክረን የተውነው ነው። ሁለት ቃላትን ይዛ ስትደጋግምም አጽንኦት ለመስጠት በምክንያት እንጂ ከቃላት እጥረት እንዳልሆነ እሙን ነው። እንግሊዘኛው rhetoric repetition ይለዋል፣ ቃናዊ ድግግሞሽ እንደማለት፤ በቅኔ ትምህርት ቤት ደጊመ ቃል ይሉታል። ከዚህ ተነስተን የበረሃ ሲሳይነቱን አስታውሰንና ተገንዝበን፣ እንድንነቃ የሚወተውት የሚብሰከሰክ ድምጽ ነው ማለት እንችላለን።

በተጨማሪም ደጋግማ ከምትለው “የበረሃው ሲሳይ” ላይ ብናይም፥ “ሲሳይ” እንዲሁ ሳይለፋ የሚገኝ፣ የሚወርድ መና እንደማለት ነው። (ሰዎች ሳይጠብቁ ያገኙትን ለመግለጽ “ሲሳይ ወረደልኝ” ይባላል። እቃ ሲሰረቁ “የሌባ ሲሳይ ሆነ እቃዬ” ይባላል። ጅብ አህያን “አንቺው ሲሳይ፣ የተጫንሽው ሲሳይ አላት” የሚል እንዲሁም “አይጥ ወልዳ ወልዳ ልጆቿን የድመት ሲሳይ ደረገቻቸው” የሚባሉ ተረትና ምሳሌዎች አሉ።

ስለዚህም የበረሃው ሲሳይ ሆንክ ስትለው፥ የእኛ አያያዝ ችግር መሆኑን የሚያጎላ እንጂ፣ ለግብጽ የሚያደላ አይደለም። ይህንን “ኢትዮጵያ” ከሚለው ዘፈኗ ጋር አሰናስለን ብንሰማውም ስሜቱ ይበልጥ ጉልህ ይሆናል።
“እምዬ እናት ዓለም እስኪ ኣንቂኝ ከእንቅልፌ
ቤቴን ሳላጸዳ እንዳልቀር ሰልፍ!”

እውነታ እና ምኞት!
“አባይ ለጋሲ ነው በዚያ በበረሀ
የሚበሉት ውሃ የሚጠጡት ውሃ
ስነካው ተነኩ አንቀጠቀጣቸው” የሚሉት የሀቅ/እውነታ ስንኞች ናቸው።

ጂጂ እነዚያን እውነታዎች ይዛ፣ የምናብ አድማሷን ዘርግታ፣ የሀሳብ ፈረሷን ርካብ ረግጣ “ቼ” ብላ ነጉዳ ነው የራሷን እይታዎች ቁጭቶች የጨመረችው። ገና ለገና “ከአባይ መጠቀም ይገባናልና፣ ወንዙ ሽቅብ ይፍሰስልን” አይባል ነገር! ስንፍናችንም አባይ ዳር ፎቶ ከመነሳት ያለፈ ያልተጠቀምንበት ነው። ቁጣቸውም፣ የኑሯቸው መሰረት መሆኑም እውነት ነው።
የእውነት መስመሮችን ብትገድፍ ነበር በአድልዎ የሚያስጠረጥራት።

የምናየው እና የሚታየው ልዩነት
እሾሁንም አበባውንም ማድነቅ ቢቻልም፣ ለፍርድ እና ወቀሳ ስንቀመጥ ግን ዛፉን በተናጥል ወይም ጫካውን በወል ተመልክተን ሲሆን ነው ሚዛናችን የሚጠበቀው። ዘፈንን ከሙዚቃውና ከዋናው ጉዳይ ለይተን፣ መስማት እና መተንተን ብንችልም፥ ግጥምንም ፀሐፊው ባለው የመጻፍ ነጻነት መጠን፣ ተደራሲውም “እንዲህ ማለቱ ነው እንዲህ ማለቱ ነው” ቢል ወይም የፈለገውን አይነት መልእክት ወስዶ መረዳት ቢችልም፥ ገጣሚውን በአገር ክህደት ፈርጆ ለመደምደም ስንነሳ ከግምት የምናስገባቸው ጉዳዮች/ነጥቦች ሊኖሩ ይገባል።

ከነዚህ መካከል፥ ሙሉውን ዘፈን ከመሰለኝ በጸዳ መልኩ መስመር በመስመር ማየት አንዱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ገጣሚው ከዚህ ቀደም ያለው የአገር አረዳድ እና በርክቶ ማየት ነው። ሌላው ደግሞ፣ ዜማው እና ሁሉም መስመሮች፣ የታሪኩ ዳራ ናቸው።

የመጽሐፍ ግጥም ሳይሆን የዘፈን ግጥም ነው!
ለማጣጣም ወይ ለመተንተን ካልሆነ በቀር፣ ለባእድ አገር በማድላት ለፍርድ ስንቀመጥ፥ ግጥሙ የዘፈን ነውና፣ ከዜማው ለይተን አንረዳውም። የታተመው የግጥም መጽሐፍ አይደለምና! ግጥሙ፣ ድምጿ፣ ሙዚቃው ተዋህደው ነው ዋናውን መልእክት የሚያስተላልፉት።

የጊዜ ሰሌዳ
ታሪክ እኛ መስማት፣ ማንበብ፣ ማስተዋል ከጀመርንበት ወይ በደቦ መጮህ ከተጀመረበት ጊዜ አይነሳምና በአባይ ዙሪያ እስራ ዓመት ወደኋላ ተጉዘን ሁለት ጊዜያትን እንይ። ዘፈን የወጣበትን እና የግድቡ ሥራ የተጀመረበትን!
ኢትዮጵያ ግድቡን መስራት የጀመረችው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2011 ነው፤ እጅጋየሁ አባይ የተከታተተበትን GIGI (aka ጉራማይሌ) አልበም ያበረከተችልን ደግሞ በ2001 ነው። ይህ ማለት በግልጽ እንደምናየው ዘፈኑን ግድቡ የቆሰቆሰው (inspire ያደረገው አይደለም) የግድብ ሥራው ተከትሎት መጣ እንጂ።

በርግጥ የአባይ ወንዝ ዙሪያ ያሉ ሙግቶችን ብናይ የግድቡ ጉዳይ ግድቡ ከተጀመረበት ቀድሞ የነበረ መሆኑን እንረዳለን። ሌላውን ብንተወው እንኳን፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን፣ የብር ኖት ላይ የግድቡ ምስል መኖሩ እና አፄ ኃይለ ሥላሴ የተናግሩትን ማሰብ የሚያሳየው ነገር አለ። ይኽን የምለው ነገሩን በግርድፉ ለሚረዱት አንባቢዎች ነው እንጂ፣ ስለጉዳዩ ጥልቅ እውቀት ላላቸው አይደለም። ስለዚህ ቀድማ በሰራችው ሥራ ላይ፣ ለግብጽ አደላች ማለት ፍርደ ገምድልነት ነው። ለመንካት ባልተሞከረበት ዘመን፣ ከጊዜ ቀድማ “ልነካው ስሞክር አንቀጠቀጣቸው” ብላለችና፣ ምናልባት ትንቢታዊነቱን ብናደንቅ እንጂ!
(በወረርሽኝ ዙሪያ የተሰሩት እነ ኮንታጀን (contagion) ልሞችስ ለኮሮና አደሉ እንላቸው ይሆን?)

የግጥሙ ዝግጅት
ጂጂ “የመጻፍ ችግር የለብኝም። በጣም ብዙ ነው የምጽፈው። አላቆምም። ግን ያው የጻፍኩት ሁሉ ዘፈኑ ላይ ይካተት አይባልም። የግድ መቁረጥ ማሳጠር ስለሚያስፈልግ የማውቀውን እውነት የተሻለ ይገልጻል ብዬ የማስበውን ነው የምጠቀመው።” ትላለች ከአንድ የውጭ አገር መጽሔት ጋር ባደረገችው ቃለ መጠይቅ (ቃል በቃል አልገለበጥኩትም)

እንዲሁ ከመዓዛ ብሩ ጋር ስለግጥም አንስተው ሲጫወቱ፣ መዓዛ ግጥሙ ሲጻፍ በሀሳብነት 17 ገጽ እንደነበር አውስታ ጠይቃት ነበር። እሷም “እንዲህ ለመደነቅ፣ ይህን ብዬ ሰው ይህን ቢል ቢነጋገርብት ብዬ ሳይሆን የማውቀውን ነው የምጽፈው፤ የማውቀውን ነገር፣ ሰው የሚያውቀውን ነገር በትክክል በአርት፣ በኤክስፕረሽን ደረጃ የምታቀርቢው ነው እንጂ… ብዙ ግጥሞች ነበር የጻፍኳቸው። መርጬ ያወጣኋቸው ናቸው እዚያ ላይ ያሉት።” ትላለች።
የፍቅር ድንግልና የሚለው መጽሐፍ ደራሲ የሆነችው እና በብዙ ማኅበራዊ በጎ ስራዎች የማውቃት እናቷ ወ/ሮ ተናኜ ስዩም፥ ከአራት ወይም አምስት አመታት በፊት ከሸገር ሬድዮ ጋር አድርገውት በነበረ ቃለ መጠይቅ፣ ስለግጥሙ ዝግጅት ስትናገር፥ በጣም ብዙ የተቆረጡ የተተዉ እንደነበሩ ገልጻ ከታች ያሉትን ፕሮግራሙ ላይ ብላቸው፣ እኛም በቃል ተቀብለናቸዋል።

“ከአባይ ወዲህ ማዶ ያለችው አገር
ፍልቅልቅ ፍልቅል አንቺ ውብ ከተማ
አባይ ባልሽ ነው ወይ ሰማሁኝ ሲታማ
አባይን የሚያህል ንጉስ አግብተሽ
ምነው መጠማትሽ ምነው መራብሽ”

እንግዲህ ከላይ ያሉት መስመሮች በጂጂ የተጻፉ ናቸው። ምንም እንኳን ዘፈኑ ላይ የተካተቱት መስመሮች የቁጭት ስሜቷን የማይሸሽጉ ቢሆኑም፣ ግራ ለሚጋባ አድማጭ/አንባቢ እነዚህ ተጨማሪ ማጠናከሪያ ይሆናሉ።
የአባይ ግጥም ጥልቀት በባለሞያዎች አንደበት

የእጅጋየሁን ግጥሞች፥ ተማሪዎች ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለው ይጫወቱበታል፣ ይወያዩበታል። የመመረቂያ ጽሁፍ ማሟያ ለመስራት በርዕስነት ይመርጡታል። ጥበብ የጠራቻቸው በየማዕዘኑ እያነሱ ይጥሉታል። ምሁራን ይወያዩበታል። በጥልቅ የሚረዱት ይበረብሩታል። እንጂ እንዲሁ በአንድ ሰሞን ተሰምተው የሚተዉ፣ በየክለቡ የሚደጋገሙ አይደሉም። በርግጥም ብዙሀኑን የሚያስደስት ላይ ላዩን የተሰራ ስራ ታዋቂ ያደርግ ይሆናል እንጂ አዋቂነትን አይገልጽም። አይፈለቅቅም።
በዚህም የአልበሙ ተቀባይነት እንዴት እንደነበረ ማየት በቂ ነው። አሁን አሁን ነገሩ ገብቷቸውም፣ ሲባል ስለሰሙ ብቻ ለማለትም፣ የተነሱ ብዙ ወጣቶች አሉ እንጂ፥ ብዙዎቻችን አንሰማትም ነበር። ስራዎቿ እንዲሁ ዛሬ ተሰምተው እንዲተዉ ሳይሆን፣ የተወሰኑ የተመረጡ አድማጮችን ማርከው እንዲይዙ የተሰሩ ናቸው ብሎ መደምደም እስኪያስችል ድረስ፣ የጥልቀታቸውን ያህል አላየናቸውም። ይኽንን የምጎዘጉዘው በአባይ ዙሪያ ከተደረጉ ምልከታዎች፥ ሁለት አንኳሮቹን ለማንሳት ነው።

ከዓመት በፊት በፋና ቀለማት በተሰራ ዘጋቢ ፊልም ላይ፤ ኢየሩሳሌም ዳኜ የተባለች የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነጽሁፍ ባለሞያ፥
“የሚበሉት ውሃ፣ የሚጠጡት ውሃ ትላለች። ውሃ በባህሪው የሚበላ አይደለም። የውሃ ባህርይ አይደለም። ሁሉ ነገራቸው ነው እያለች እኮ ነው ለግብጾች! አባይ፥ ዩኒቨርሳልነት አለው ራሱ ተፈጥሮው። ይህንን እውቀት ጂጂ ግጥሟ ውስጥ ስታመጣው፣ አባይ ከጊዜ እና ከስፍራ በላይ ሆኗል። ገዝፏል። እኔ እንዴት ይሰማኛል መሰለህ? የጂጂን አባይ ስሰማ፣ አባይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ አይደለም የሚታየኝ፤ ኢትዮጵያ ናት አባይ ውስጥ ሆና የምትታየኝ፤ ይሄን ያህል ይገዝፍብኛል አባይ።” ብላ ነበር።
በሸገር ሬድዮ ተወዳጅ የነበረው የጣዕም ልኬት ዝግጅት ላይ አቅርበውት የነበረው የአባይ ግጥም ትንተና ደግሞ፥

ይህ ግጥም [አባይ] የአገራችንን ታላቅ ወንዝ አባይን በርዕሰ ጉዳይነት የሚያነሳ የዘፈን ግጥም ነው። ይህ የዘፈን ግጥም በእኔ እምነት እስከዛሬ ስለአባይ ከተቀነቀኑት ዘፈኖች ሁሉ እጅግ የተለየ ጥልቅ እና ምጡቅ ስራ ነው። …አባይ የተሰኘው የእጅጋየሁ ሽባባው ግጥም ከእስከዛሬዎቹ ለአባይ ከተቀነነቁት የረቀቀ ነው።

ግጥሙ ሲጀምር የሚያነሳው ስለአባይ አፈጣጠር እና አመጣጥ በመተረክ ነው። የራሱን ምናባዊ ብየና ይሰጣል። ወደሚቀጥሉት የሀሳብ ድሮቿ ከመሸጋገሯ በፊት፣ ከያኒዋ መሰረቷን አጥብቃ እና አጽንታ ለመሄድ በመሻት፣ ስለአባይ የመነሻ ቦታ፣ አመጣጡን እና አፈጣጠሩን፣ የመጻፍ ነጻነቷን ተጠቅማ ትበይናለች።
የገጣሚዋ ብየና የወንዙን መነሻ ያደረገው አንዱን አህጉር፣ አገር፣ ክፍለ አገር ወይም ግዛት በመጥራት አይደለም፤ የትኛውም ቀበሌና ጎጥም አልተጠቀሰም። ይልቅስ የሀሳብ አድማሷ ወዲያ ተመንጥቆ፣ ዘመን ተሻግሮ፣ አለምን ዘቅዝቆ እያየ አባይ ህይወት እንድትቀጥል ለምድር ከገነት የተቸራት ቅዱስ የጠበል ውሃ መሆኑን ታበስረናለች። “ባናውቅበት ነው እንጂ!” የምትልም ይመስላል።

እነዚህን ሁሉ ሀሳቦች የምናገኘው እንግዲህ በዘፈኑ የመጀመሪያ ክፍል፣ አዝማች ላይ መሆኑን ልብ ይሏል። ይህንን ሁሉ ግዙፍ ፍልስፍና፣ እነኚህን ሁሉ አበይት ሀሳቦች የተሸከመ የስንኞች ህብር ሌሎች ተከታይ ስንኞችን ለማዝመት ብቁ በመሆኑና፣ መንደርደሪያነቱም የጎላ በመሆኑ፣ አዝማች የሚለው ስም ያንስበት ይሆናል እንጂ አይበዛበትም። አባይ ከ- እንጂ እስከ- እንደሌለው አበክረው ይሰብካሉ።” በማለት ትንተናቸውን ይቀጥላሉ።

ፍረጃው ላይ የተዘለሉ መስመሮች …

«የማያረጅ ውብት የማያልቅ ቁንጅና
የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የጸና
ከጥንት ከጽንስ አዳም
ገና ከፍጥረት
የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከገነት
ግርማ ሞገስ
የአገር ጸጋ የአገር ልብስ
ግርማ ሞገስ»

ከላይ ያሉት የግጥሙ መንደርደሪያ መስመሮች እንደሚያሳዩትም፥ አባይ በዋናነት የተዘፈነው የወንዙን ዘፍጥረት፣ ውበት እና ጸጋ በማወደስ ነው። የአባይን ወንዝ በማወደስ እና፣ ከስነፍጥረት ጀምሮ ከኤደን ገነት የፈሰሰ መሆኑን በመግለጽ፥ የወንዞች ሁሉ ወንዝነትን ማዕረግ ታጎናጽፈዋለች። “የሚበሉት ውሃ የሚጠጡት ውሃ” ስትልም፣ ምን ያህል ከራሳቸው ጋር የተሳሰረ እንደሆነ፣ “ሲናይ በረሀ ውስጥ ምን አስቀምጠሃል? ቢጠሩህ ለምን አትሰማም” እያለች ደጋግማ ትጠራዋለች፤ የጥበብ እና የሕይወት ምንጭ እንደሆነ ገልጻ ታወድሰዋለች።

ግርማ ሞገስ መላበሱን የአገር ፀጋነቱን፣ የአገር ልብስነቱን ገልጻ ትጮሃለች። በዚያ ግን አያበቃም። “መልኬ በቃኝ አልክ ምነው?” አልክ ዓይነት ትለዋለች። የማያሞቅ፣ እርቃን የማይሸፍን የገር ልብስ የአገር ጸጋ! አያስቆጭም? (የውዳሴ ግጥሞችን ቢደረድርም፣ ዜማው እንጉርጉሮ ነውና በዚያው ድብልቅ ስሜት ይቃኛል) እውነትም፥ “አላወቅንበትም እንጂ!” የምትል ይመስላል።
“አባይ የወንዝ ውሃ አትሆን እንደሰው (?)
ተራብን ተጠማን ብለው
አንተን ወራጅ ውሃ ቢጠሩህ አትሰማ
ምን አስቀምጠሃል ከግብጾች ከተማ?

አባይ
አባይ
አባይ
አባይ
አባይ ወንዛወንዙ
ብዙ ነው መዘዙ
የበረሃው ሲሳይ
የበረሃው ሲሳይ
የበረሃው ሲሳይ
የበረሃው ሲሳይ”
እንግዲህ እነዚህ መስመሮች የፍርድ ሚዛኑን ያርሙታል ብዬ አስባለሁ። ለላቀ ሥራዋ ምስጋና እና መወድስ ቢቀር እንኳን፣ ባልዋለችበት እንዳናውላት እመኛለሁ። ዛሬ ዛሬም ትንሽ የሚረዷት መጡ እንጂ፣ እሷም እንደ አባይ ከውስጥ ወጥታ ከውጭ ወደ ውስጥ ነው የፈሰሰችልን። የአባይ ወደውስጥ መፍሰስ ገና ትግል፣ ህልምና ተስፋ ላይ ነው።
ያንን ቀን ለማየት ያብቃን!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s