Arts

ብርሀኑ ገበየሁን ስናስታውስ

(አሌክስ አብርሃም)

“ፈልገነው ነበር ባለበት ከተማ

ዱዓ አድርገን ነበር በወሎ መንዙማ

አልተገናኘንም ጀሊሉም አልሰማ “

በሕይዎት እያለ በአካል አግኝቸው  ለማላውቀው …ዩኒቨርስቲ ገብቸ እፊቱ ተቀምጨ መማር ብጓጓም  እኔ ስደርስ ይችን ዓለም በሞት ስለተሰናበተ ታላቅ መምህሬ ላወሳ ወደድኩ!በኢትዮጵያ ስነፅሁፍ በተለይም በስነግጥም እንደዚህ ሰው የተመራመረ ፣ያጠናና ያስተማረ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ! የማወራችሁ ስለረዳት ፕ/ር ብርሃኑ ገበየሁ ነው !…በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነጽሑፍ ፣ በተለይም በስነ ግጥም መምህርነትና ተመራማሪነት ይታወቅ ስለነበረው ብርሃኑ ገበየሁ! ብርሃኑ ገበየሁን ያወኩት ገና ስራዎቹ በመፅሃፍ ሳይታተሙ ደሴ የሃይስኩል ተማሪ እያለሁ ነበር ፡፡ ማወቅ ብቻ አይደለም ያወራ የተነፈሰው የፃፈ ያስተማረውን ሁሉ የማግኘት እድል ነበረኝ፡፡ በርቀት አስተማረኝ ብል ምንም ግነት የለውም፡፡

በታላቅ ወንድሜ አማካኝነት ነበር የመጀመሪያ ትውውቄ ! የብርሃኑ ገበየሁ የነፍስ አድናቂ ነው! “ሃንድአውቱ”  ከእጁ ፣ ስሙም ከአፉ የማይጠፋ አድናቂው!  (እዚህ ላይ ስለወንድሜ ትንሽ ማለት ተገቢ ነው…እድሉ ስለተሰጠኝ አመሰግናለሁ) ታላቅ ወንድሜ የመጀመሪያ ድግሪውን የሰራው በቋንቋና ሥነ ጽሁፍ  …ሁለተኛ ድግሪውንም የሰራው በቋንቋና ሥነ ጽሁፍ…እና ሶስተኛ ድግሪውንም እየሰራ ያለው በቋንቋና ሥነ ጽሁፍ ! ገና ከህፃንነት ዕድሜ ጀምሮ የማንበብ ፍቅርን አንብብ ሳይል ያሳደረብኝ እሱ ነው ! እንደውም በሕይዎቴ ውስጥ ካነበብኳቸው መፅሃፎች ምርጦቹ ከዚህ ወንድሜ በስጦታ የተበረከቱ …መስጠት ካልፈለገም ካስቀመጠበት እየሰረኩ ያነበብኳቸው ናቸው! አንድም ቀን ግን ስጦታ ብሎ ሰጥቶኝ አያውቅም ‹‹እነዚህ አንተ ጋር ይቀመጡ ስፈልጋቸው እወስዳቸዋለሁ›› ይላል፡፡

አንብብ አታንብብ ብሎኝ አያውቅም …አሪፍ አንባቢ ነው ! በተለይ የሃይስኩል ተማሪ እንደነበርኩ በየቀኑ በሚባል ሁኔታ መፅሐፍት እየያዘ ይመጣና ደብቆ ያስቀምጣቸዋል …እኔ ደግሞ በቀላሉ ነበር ከተደበቁበት የማገኛቸው …ይሄ ብቃቴ ወደፊት “ዲቴክቲቭ” ብሆን ሁሉ ይዋጣልኛል ብየ ራሴን እንዳዳንቅ አድርጎኝ ነበር! ሌሊቱን ቁጭ ብየ ሳነብ አድርና ቦታቸው እመልሳለሁ … ከብዙ ዓመት በኋላ በቅርቡ ሲነግረኝ …ለካስ የሚደብቃቸው እንዳገኛቸው አድርጎ ነበር …እንደማነባቸውም ያውቅ ነበር ፡፡ ‹‹የተደበቀ ነገር ትወድ ነበር ለዛ ነው ›› አለኝ ! በዚህ መንገድ አስነበበኝ !

ከነአጋታ ክርስቲና ኧርቪንግ ዋላስ ገራገር ንባብ ቀስ አድርጎ ወደነሄሚንግ ዌይ ፣ዲዮቶቭስኪ ፣ ቶልስቶይ ፣ጎረኪና ሌሎችም ታላላቅ ፀሐፍት መንገድ የመራኝ እንደዛ ነበር፡፡ አስቂኙ ነገር ብዙ ጊዜ ሰርቄ ማንበቤን እየረሳሁ ቋንቋው ሲከብደኝ ፣ ወይም ፍልስፍናው ሲወሳሰብብኝ  መፅሃፉን አንከርፍፌ ሂጀ ራሱን መልሸ እጠይቀው ነበር !ያብራራልኛል…አፌን ከፍቸ እሰማለሁ ! ከዛ ‹‹ግን እንድታነብ ማን ፈቀደልህ?›› የሚል የውሸት ቁጣ ይመርቅበታል ! ነገም ግን ያው ነው! ካልጠየኩት ቃል አይተነፍስም ‹‹ከራስህ ሲመጣ ነው አሪፍ ›› ይላል፡፡ መምከር አይወድም! ብዙ ያነባል ፣ ስለማንበብ ግን  አንድም ቀን ሲያወራ ሰምቸው አላውቅም! ካልጠየኩት በስተቀር!  በርካታ ፅሁፎችን በራሱ የእጅ ፅሁፍ እየተረጎመ በልጅነት አስኮምኩሞኛል! አንብብ ብሎ አይደለም ‹‹እንዳትነካ›› ብሎ መንካት የምችልበት ቦታ በማስቀመጥ እንጅ!እንዳትነካ ከተባልኩ እንቅልፍ የለኝም!

ታዲያ ይሄ ወንድሜ ዩኒቨርስቲ እንደነበር ለእረፍት ወደቤት ሲመለስ ብዙ  ሃንድ አውት ተሸክሞ ይመጣል …የሚበዙት በስነፅሁፍ ዙሪያ ሲሆኑ የብርሃኑ ገበየሁ ሃንድ አውቶች ግን የእኔ አንደኛ ተመራጮች ነበሩ!   ፕሮስ ፊክሽን /prose fiction/  የሚል ስለልብወለድ  ምንነት ከስር መሰረቱ የሚያስተምር አንድ ኮርስ  እንደዳዊት ነበር የደገምኩት ! Survey of Ethiopian literature (ይሄንኛው ሃንድ አውት የዶ/ር(?)  ፕ/ር (?) አብርሃም ዓለሙ  ይመስለኛል) (ሌላው ትንታግ )  ለመጀመሪያ ጊዜ ካነበብኩባቸው ጊዜ ጀምሮ ያልሰበሰብኩት የብሬ ፅሁፍ አልነበረም፡፡ ከጋዜጦች ላይ ሁሉ የእርሱን አርቲክሎች በመቀስ እየቆረጥኩ አስቀምጥ ነበር !  የብርሃኑ ገበየሁ ፅሁፎች የታተሙባቸው በርካታ የአዲስ አድማስ ጋዜጦች ነበሩኝ! በተለይ ስለስነግጥም ያስተማረባቸውን ሃንድ አውቶች ሙሉ ለሙሉ የተማሪዎቹን ያህል አጥንቻቸው ነበር ቢባል ግነት አይደለም፡፡ በዛ ላይ የወንድሜ ሌክቸር ይጨመርበታል፡፡ (ሰርጌም እንዲህ አልደመቀ)

በሥነጽሑፍ፣ ግጥምና ፎክሎር ብሬ የእኔ ንጉስ ነበር! ታዲያ የሆነ ጊዜ አዲስ አበባ ‹‹ናይል ቤዚን ኢንሸቲቭ›› የሚባል ድርጅት ስለአባይ ወንዝ አጠቃቀም ባዘጋጀው የፎቶግራፍ ውድድር አሸንፌ ዝግጅቱ ላይ ለመገኘት ከደሴ ወደአዲስ አበባ ሄድኩ (ያኔ ፎቶግራፊ ላይም እንደሆቢ ተፍ ተፍ እል ነበር) … ይችን አጋጣሚ ተጠቅሜ አዲስ አበባ ላይ ለማግኘት ከቋመጥኩላቸው ሰዎች የመጀመሪያውና ብቸኛው ብርሃኑ ገበየሁ ነበር፡፡ አሁን ላይ ሳስበው ባገኘው ምን እለው እንደነበር አላውቅም! ያኔ ታዲያ ስድስት ኪሎ ይማሩ የነበሩ የማውቃቸውን ልጆች ብርሃኑ ገበየሁን አሳዩኝ ብየ ለመንኳቸው ! ተያይዘን ወደስት ኪሎ ሄድን!

ታዲያ ባዶ እጀን አልነበረም! ወደ ሶስት ዓመት አካባቢ የሰበሰብኩትንና የተጠረዘ የወሎ መንዙማ ግጥሞች  ተሸክሜ ነበር ! እጅ መንሻ ! ምክንያቱም ብሬ ስለወሎ መንዙማ ግጥሞች እያጠና እንደነበረ በመስማቴ ምናልባች ይፈልጋቸው ከሆነ በማለት ፣ ወዲህም መቀራረቢያ እንዲሆነን ነበር ! በአጋጣሚ በደይቃዎች ልዩነት ብሬ ወጥቶ ተላለፍን  …ደግሞ ለትንሽኮ ነው …ከሩቅ የሆነች መኪና ውስጥ ሲገባና ሲሄድ ያውና እዛጋ አሉኝ …ሹራብ የለበሰ ሰው … ከሩቅ ያውም ከኋላው ለቅፅበት በውልብታ አየሁ ! መኪናዋ ውስጥ ሌሎችም ሰዎች ነበሩ ….የኋላ በር ከፍቶ ነው የገባው! እንዲህ ነበር የሩቅ መምህሬን ለመጨረሻ ጊዜ በሩቅ የተሰናበትኩት ! በቀጣዩ ቀን ወደደሴ ተመለስኩ! 2002 ዓ.ም ሐምሌ ወር ላይ የብርሃኑ ገበየሁን ድንገተኛ ሞት ሰማሁ!

ከብሬ ሞት በኋላ በጣም ያሳዘነኝና እኛ ኢትዮጵያዊያን አንዳንዴ ቂማችን እስከመቃብር እንደሚዘልቅ የተረዳሁት 1990ዎቹ ውስጥ  በትንታግ ብዕሩ በጋዜጦች ላይ  የግጥምም ሆነ ሌሎች የስነፅሁፍ ስራቸውን የተቸባቸውና በህይዎት እያለ እንኳን መልስ ለመፃፍ ለመተንፈስ ከብዷቸው የተደበቁ ‹‹ምሁራን›› ከሞተ በኋላ እየተነሱ የግጥም አዋቂነቱን ለማጣጣል ሲፍገመገሙ ማየቴ ነበር! ከነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ውሃ የማያነሳ ትችታቸውን ከቂም ጋር ቀላቅለው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ሲደፉ ተመልክቻለሁ!

አንዱ እንደውም (በወቅቱ የአዲስ አድማስ አምደኛ ይመስለኛል )  በብርሃኑ ገበየሁ ‹‹የአማርኛ ስነግጥም ንድፈ ሐሳብ ፣ማብራሪያ ትንታኔ ›› የሚል መፅሐፍ ላይ የፃፈው ትችት በጣም አሳዝኖኝ በዚሁ ጉዳይ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ረዥም ጊዜ ወስጀ ያዘጋጀሁትን ምላሽ እቢሯቸው ድረስ ሂጀ ሰጥቻቸው ነበር ! አልታተመም ! ለምን እንዳልታተመ አላውቅም አልጠየኩምም! የፃፍኩት ግን ብሬን ስለምወድ ብቻ ሳይሆን ነገሩ ቂም በቀል ስለሚመስል ነበር ፡፡ ቆየት ባሉት ጊዚያት ይሄው አምደኛ በኢትዮጵያ ግጥሞች እና ገጣሚያን ዙሪያ  አዲስ አድማስ ላይ በፃፋቸው ፅሁፎች ፣ ብርሃኑ ገበየሁ ተደጋጋሚና አስገራሚ ምላሽ ሰጥቶ ነበር … እንግዲህ ከሞተ በኋላ ቂሙን ታጥቆ ብቅ እንዳለ አስባለሁ ! ምናልባት እኔም ተሳስቸ ይሆናል …ድጋሜ ፅሁፎቹን ባገኝ አነባለሁ እስቲ !

 የሆነ ሁኖ ታላቁ የስነፅሁፍ ሰው ረ/ፕ/ር ብርሃኑ ገበየሁ …ለአገራችን ስነፅሁፍ ትልቅ ቦታ ያለው ‹‹የአማርኛ ስነግጥም ንድፈ ሐሳብ ፣ማብራሪያ ትንታኔ›› መፅሐፉን አበርክቶልን በ45 ዓመቱ ነበር ይችን ዓለም በድንገት የተሰናበተው! እነሆ ነፍሱ ትሰማንም ከሆነ ሳያውቅ ብዙ ያስተማረኝ ተማሪው ዛሬ ስለተወልን ነገር ሁሉ እድሜውን ሙሉ ስለደከመበትም የአገራችን ስነፅሁፍ ላመሰግነው ወደድኩ ! ነፍስህ በሰላም ትረፍ! አመሰግናለሁ !!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s