Culture & Lifestyle / Features/ Reviews

የበኒ ዐምሩ ወጣት

ኤርትራ አሁን ባላት አከፋፈል መሠረት ምዕራባዊ ክፍሏ “ጋሽ ባርካ” በተባለ ዞን ስር የተዋቀረ ነው፡፡ ይህ የጋሽ ባርካ ዞን ኩናማ፣ ናራ እና ህዳሬብ የሚባሉ ብሄረሰቦች መኖሪያ ነው፡፡ የዞኑ ዋነኛ ህዝብ ግን “ትግረ” ይባላል፡፡ ከኤርትራ ብሄረሰቦች መካከል በህዝብ ብዛቱ ከብሄረ-ትግርኛ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ይህ የትግረ ብሄር ነው፡፡ በብዙ የዓለም ክፍሎች ከፍተኛ ዝና ለመጎናጸፍ የቻለው ኤርትራዊም ከዚህ ህዝብ ነው የተወለደው፡፡ እርሱም ለኛ በጣም ቅርብ ሆኖ የኖረው ሳቂታው የበኒ ዐምር ወጣት ነው፡፡

የበኒ ዐምሩ ወጣት ለብዙ ዓመታት አነጋጋሪ ሆኖ ዘልቋል፡፡ ወጣቱ የበርካቶች መነጋገሪያ ለመሆን የበቃው ፖስተሩ የሚታወቀውን ያህል ማንነቱ በደንብ ስለማይታወቅ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እርሱን የሚመለከቱ የተለያዩ ታሪኮች ተፈጥረዋል፡፡

ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች “ክረስት የሚባለው ታዋቂ የአሜሪካ የጥርስ ብሩሽ አምራች ኩባኒያ ማስታወቂያ ሊያሰራው ወደ ኒውዮርክ ወስዶታል” ይላሉ፡፡ የተወሰኑት ደግሞ “አንዲት ፈረንሳዊት ሀብታም የወጣቱን ፎቶግራፍ ስታይ በውበቱ ተማረከችና እስከ መኖሪያው ድረስ መጥታ አግብታው ወደ ፓሪስ ወሰደችው” ሲሉ ይሰማሉ፡፡

ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ተረት መሳይ ታሪክ የነገሩኝ ሰዎችም ገጥመውኛል፡፡ እነዚህ ሰዎች የነገሩኝ ተረት የሚከተለው ነው፡፡

“ወጣቱ ጥብቅ ባህል ከሚከተል ቤተሰብ ነው የተወለደው፡፡ ቤተሰቡ ሳይፈቅድለት ነው ፎቶውን የተነሳው፡፡ ታዲያ አንድ ቀን አባቱ ወደ ተሰነይ ሲመጣ ከተማዋ በልጁ ፎቶግራፍ ተወርራ አገኛት፡፡ በዚህም አባት ተናደደና ወደ ቤት ሄዶ ልጁን ገደለው”

እንግዲህ ሁሉም የየራሱን መላምት ነው የሚወረውረው ማለት ነው፡፡ ታሪኩ በደንብ ያልተመዘገበለት ሰው እንዲህ የፈጠራ ታሪኮች ሰለባ ይሆናል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባደረግኩት ፍተሻ እንደተረዳሁት የወጣቱን ፎቶግራፍ ያነሳው ለአሜሪካው ናሽናል ጂኦግራፊክ ሶሳይቲ ይሠራ የነበረ ጀምስ ብሌር የሚባል የፎቶ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ብሌር ፎግራፉን ያነሳው እ.ኤ.አ. በ1965 በያኔዋ ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ (በአሁኗ ኤርትራ ምዕራባዊ ክፍል) በምትገኘው የተሰነይ ከተማ አቅራቢያ ነው፡፡ ወጣቱ የበኒ ዐምር ጎሳ ተወላጅ ስለመሆኑ በናሽናል ጂኦግራፊ መጽሔት ላይ ተገልጾ ነበር (በድረ ገጹም ላይ ይገኛል)፡፡

የሚገርመው ታዲያ ብሌር ፎቶውን ባነሳበት ወቅት አንድ ታላቅ ኢትዮጵያዊ አብሮት የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ኢትዮጵያዊ ለሃያ ዓመታት ያህል በጀርመን ድምጽ ሬድዮ (ዶቼ ቬሌ) ውስጥ ሲያስገመግም በኖረው ድምጹ የምናውቀው ተወዳጁ ጋዜጠኛ ጌታቸው ደስታ ነው፡፡ ጌታቸው ደስታ በሀምሌ ወር 2009 “ኢትዮጵያ ኦብዘርቨር” ከተሰኘው የእንግሊዝኛ ድረ-ገጽ ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ የወጣቱ ፎቶግራፍ የተነሳበትን ኩነት እንዲህ በማለት ተርኳል፡፡

“ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እ.ኤ.አ. በ1963 አሜሪካን በጎበኙበት ወቅት አንድ የናሽናል ጂኦግራፊክ መጽሔት የጉዞ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ጥናታዊ ዘገባ ለመሥራት እንዲፈቀድለት ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም ሐሳቡን በደስታ ተቀበሉት፡፡ በዚሁ መሠረት ቡድኑ በ1965 ወደ ኢትዮጵያ መጣ፡፡ እኔ በዚያን ጊዜ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሠራተኛ ነበርኩ፡፡

ታዲያ አለቆቼ ከቡድኑ አባላት ጋር ተጉዤ በአስተርጓሚነት እና በአስጎብኝነት እንድረዳቸው አዘዙኝ፡፡ እኔም ከቡድኑ ጋር ተቀላቅዬ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ተጓዝኩ፡፡ ጉዞአችንን ያከናወነው በጊዜው “እጅግ ዘመናዊ ሞዴል ናቸው” በተባለላቸው የላንድሮቨር መኪናዎች ነው፡፡ እያንዳንዱ መኪና ማቀዝቀዣ ነበረው፡፡

የጉዞ ቡድኑ በያዘው ፕሮግራም መሠረት ላሊበላን፣ ጎንደርን፣ አክሱምንና ምጽዋን ጎበኘን፡፡ ከዚያም ከአስመራ ጀምረን እስከ ተሰነይ ያለውን ክልል ለመጎብኘት ሄድን፡፡ በጉዞአችን ላይ ሳለን በአቆርዳትና በተሰነይ መካከል በርከት ያሉ ግመል ጠባቂዎች አጋጠሙን፡፡ ይህ ሳቂታ ወጣትም ከእነርሱ ጋር ነበረ፡፡

የፎቶ ጋዜጠኛው ብሌር በወጣቱ አስተያየት ተማረከና ፎቶ ያነሳው ጀመር፡፡ ብዙ ፎቶግራፎችን አነሳ፡፡ እያንዳንዱን ፎቶ ሲያነሳም በአድናቆት “አታይም እንዴ?” ይለኝ ነበር፡፡ በስተመጨረሻ ግን ልጁ ተቆጣ፡፡ እኔም ቶሎ ብዬ ኮካ ኮላ ሰጠሁት፡፡ ልጁም ወደ አፉ ወሰደውና በአንድ ትንፋሽ ጠጣው፡፡ ከዚያም በከፍተኛ ድምጽ አገሳ፡፡ በመጨረሻም “አልሐምዱሊላህ” ብሎ ተነፈሰ፡፡

አሜሪካዊያኑ ጋዜጠኞች ወደ ሀገራቸው ሄደው ዘገባቸውን በሠሩበት መጽሔት ላይ (እ.ኤ.አ. April 1965 የታተመ) ይህንን ሁሉ ገልጸውታል፡፡ ዘገባው ቆንጆ ነበር፡፡ ከዘገባው በላይ ገንኖ የወጣው ግን የወጣቱ ፎቶግራፍ ነው፡፡ ይኸው ፎቶው ዛሬም ድረስ በየቤቱ ተለጥፎ ይታያል”

ጌታቸው ደስታ የሰጠን መረጃ በዚሁ የተገደበ ነው፡፡ ሌሎች የጽሑፍ ምንጮች ደግሞ የእርሱን ያህል ስለወጣቱ አይናገሩም፡፡ በመሆኑም ስለወጣቱ ማንነት በትክክል ለመናገር ብዙ የተጓደሉ ነገሮች አሉ፡፡ ሌላው ነገር ሳይቆጠር የወጣቱ ስም እንኳ በመጻሕፍት፣ በመጽሔቶችና በድረ-ገጾች ላይ አልተጻፈም፡፡ ማንነቱ በደንብ ካለመታወቁ የተነሳም “ሳቂታውን ወጣት በሕይወት ባገኘሁትና ታሪኩን በጻፍኩለት?” የሚል ፍላጎት ተፈጥሮብኝ ቆይቷል፡፡

አዎን! ለብዙ ዓመታት ከርሱ ጋር ስለመገናኘት ሳልም ኖሬአለሁ፡፡ እርሱን የሚያውቅ ሰውም ሳስስ ከርሜአለሁ፡፡ ይሁንና ሙከራዎቼ ሁሉ አንዳች ውጤት ላይ ሳያደርሱኝ ቀርተዋል፡፡ ኤርትራዊያንም ሆኑ ኢትዮጵያዊያን ዛሬም ድረስ በልጁ ማንነት ዙሪያ ያላቸው እውቀት በጣም ውስን ነው፡፡

በቅርቡ በወጣቱ ዙሪያ ሲቀርቡ የነበሩትን ጥያቄዎች በከፊል ለመመለስ የሚያስችሉ የቃል መረጃዎችን ለማግኘት ችዬአለሁ፡፡ ለዚህም የረዳኝ እንደ ሳቂታው ወጣት የበኒ ዐምር ተወላጅ ከሆነ ኤርትራዊ ጋር መተዋወቄ ነው፡፡ ይህ ወዳጃችን ጃዕፈር ዑሥማን ይባላል፡፡ ጃዕፈር የተወለደው በሰሜን ኤርትራ በምትገኘው የናቅፋ ከተማ ነው፡፡ ነገር ግን ወጣቱ የኖረበትን የምዕራብ ኤርትራ ክልልንም በደንብ እንደሚያውቀው ይናገራል፡፡ ሳቂታው ወጣትም በፎቶግራፉ ሳቢያ በሁሉም የበኒ ዐምር ተወላጆች ዘንድ እንደሚታወቅም ያስረዳል፡፡

ጃዕፈር የበኒ ዐምሩን ወጣት በሕይወት መገኘት በተመለከተ ለጠየቅኩት ጥያቄ ተስፋ የሚያስቆርጥ ምላሽ ነው የሰጠኝ፡፡ እንደ ጃዕፈር አባባል ከሆነ ሳቂታው ወጣት እ.ኤ.አ. በ1989 አርፏል፡፡ ይህም የዛሬ 30 ዓመት ገደማ መሆኑ ነው፡፡ ወጣቱ ፎቶውን ሲነሳ በግምት አስራ ሰባት ዓመት ሆኖት እንደነበረ ይገመታል፡፡ በዚህም መሠረት ከላይ በተጠቀሰው ዓመት ሲያርፍ ዕድሜው ከአርባ ዓመት ተሻግሮ ነበር ማለት ነው፡፡

“የበኒ ዐምሩ ወጣት ብዙ ልጅ አልወለደም” ይለናል ጃዕፈር፡፡

ከእርሱ አብራክ የተገኘችው አንዲት ሴት ልጅ ብቻ እንደሆነችና ይህቺ ሴት ዛሬ በሱዳኗ የከሰላ ከተማ እንደምትኖርም ይናገራል፡፡ ጃዕፈር እንዳጫወተኝ ከሆነ የበኒ ዐምሩ ወጣት ስም ዑመር ሙሐመድ ኢድሪስ ነው፡፡ ይህ ወጣት ሐጂ ሙሐመድ አል-ከቢር ከሚባሉ ታዋቂ ሼኽ መወለዱና የቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ መሆኑም ከጃዕፈር ተነግሮኛል፡፡

በርካታ ኤርትራዊያንና ኢትዮጵያዊያን ከሊኦናርዶ ዳቪንቺዋ “ሞናሊዛ” በላይ የሚሳሱለት የሳቂታው ወጣት ጉዳይ በዋዛ መታለፍ የለበትም፡፡ ስለሆነም የኤርትራ ልጆች በደንብ ያልተገለጠውን የወጣቱን ታሪክ ፈትሸው እውነታውን በጽሑፍ ሊያስቀምጡልን ይገባል እንላለን፡፡

—–

አፈንዲ ሙተቂ፡ “የኤርትራ ህልም”፡ ገጽ 152-155

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s