Arts

የአድአው ጥቁር አፈር (ዝክረ ተስፋዬ ገብረአብ) ክፍል ፪

ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ

ተስፋዬ ገብረአብ ሀገረ-ሰላም በተሰኘው ገደላማ ሰፈር የሚገኘው የያኔው ኢህአዴግ ሬድዮ ጣቢያ ሲደርስ የኢህአዴግ የበረሃ ጋዜጠኞች ተከታታይ ቃል-ምልልስ አድርገውለታል። የኢህአዴግ መሪዎችም በሬድዮ ጣቢያው እንዲያገለግል መድበውታል። ተስፋዬ የሬደዮው ጣቢያው ባልደረባ ሲሆን ከእርሱ በፊት በሬድዮው ተመድበው የቅሰቀሳ ስራ ከሚሰሩት ሙሉጌታ ገሠሠ፣ አማረ አረጋዊ፣ መዝሙር ፈንቴ፣ ሱለይማን ደደፎ፣ ሱኩቱሬ ጌታቸው፣ አታክልቲ አምባዬ፣ ወዘተ ጋር ነበር የተጣመረው። እነዚህ ሰዎች በሙሉ የሚታዘዙት የኢህአዴግ የፕሮፓጋንዳ ኃላፊዎች በነበሩት ዓለም ሰገድ ገብረአምላክ፣ በረከት ስምኦን፣ ገብረመስቀል ኃይሉ ወዘተ.. ነው። ኢህአዴግ ደርግን ጥሎ አዲስ አበባ ከገባ በኋላም በበረሃው ሬድዮ ይሰሩ የነበሩት ካድሬዎች የኢህአዴግ የፕሮፓጋንዳ ክንፍ አባላት ሆነው ሰርተዋል።

ተስፋዬ ከተምቤን ዋሻዎች በሚተላለፈው የኢህአዴግ ሬድዮ ጣቢያ ያስተላለፈው የመጀመሪያው ጽሑፍ በደብረታቦር ውጊያ ያየውንና የታዘበውን ነገር በጥሩ ብዕር የሚተርክ ነበር። ጽሑፉ ኢህአዴጎች በሚወዱት መንገድ የተቃኘ ቢሆንም የትረካው ለዛ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነበር። በበረሃው ትግል ላይ የነበሩ ታጋዮች የጽሑፉን አቅራቢና ተራኪ ማንነት ለማወቅ ይጓጉም ጀመር። በጥቂት ወራቶች ውስጥም ኢህአዴጎች በደብረታቦር ውጊያ የማረኩት የቢሾፍቱ ቡቃያ ቀደም ብለው በሬድዮ ጣቢያው ሲሰሩ የነበሩትን የፕሮፓጋንዳ ካድሬዎች ሁሉ የሚያስከነዳ እንደሆነ ተረዱ። ወጣቱ በደንብ ከያዙት ብዙ የፕሮፓጋንዳ ስራ ሊሰራላቸው እንደሚችልም ተገንዘቡ።

የድርጅቱ መሪዎች ተስፋዬን ከዋናው የኢህአዴግ ጽ/ቤት አካባቢ ሊያርቁት ያልፈለጉት ለዚሁ ነበር። ተስፋዬም በገጠመው ዕድል ከያኔው ኢህአዴግ ዋነኛ መሪዎች ጋር ሊተዋወቅ ችሏል። ኢህአዴጎችም ዝግ ስብሰባ ከሚያካሄዱበት ጊዜ በቀር በሌሎች ስብሰባዎችና የተሓድሶ ፕሮግራሞች ያሳትፉት ነበር።

ግንቦት 20/1983 መጣ።

የደርግ መንግሥት ህልውና አከተመ። ኢህአዴግም አዲስ አበባን ይዞ ጊዜያዊ መንግሥት ሰየመ። ከሁለት ወር በኋላ ደግሞ ከሃያ አንድ ያላነሱ ድርጅቶች የተሳተፉበት የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ተመሠረተ። አቶ መለስ ዜናዊ የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚዳንት እና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሆኑ። ዶክተር ፈቃደ ገዳሙ የሚባሉት የጉራጌ ብሄረሰብ ተወላጅ የሽግግሩ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኑ። የከምባታ እና ሀዲያ ተወላጅ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ሀቢሶ የሽግግሩ መንግሥት ዋና ጸሐፊ ተብለው ተሰየሙ። በነሐሴ ወር 1983 መጀመሪያ ላይ የሽግግሩ መንግሥት ሚኒስትሮች ተሾሙ። በዚያው ገደማ በመንግሥት ይዞታ ስር ያሉትን ድርጅቶች የሚመሩ የስራ ኃላፊዎች የሽግግሩ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስት በነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ፊርማ ተመደቡ።

በዚያ ሹመት የመንግሥት ባለስልጣን ሆነው ከተመደቡት ሰዎች አንዱ ለዓመት ከስድስት ወር ያህል የኢህአዴግ የፕሮፓጋንዳ ካድሬ ሆኖ ሲሰራ የነበረው ወጣቱ ተስፋዬ ገብረአብ ነው። ለተስፋዬ የተሰጠው ሹመት “የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ኃላፊ” የሚል ነበር። የአድአው ጥቁር አፈር ሹመቱ ሲሰጠው ዕድሜው 23 ዓመት ብቻ ነው። በመሆኑም የሹመት ደብዳቤው ሲመጣበት ድንብርብሩ ነው የወጣው። ተስፋዬ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር አባል የሆነው ከስራ አጥነት ራሱን ለማላቀቅ እና የስነ-ጽሑፍ ፍላጎቱን የሚያሳካበትን መንገድ ለመሻት ብቻ ነበር። ነገር ግን ያሰበው ሳይሆን ቀረና ያላሰበው ሆነ። በጥቂት ዓመታት ውስጥ ምርኮኛ ሆኖ፣ ከምርኮኛነት ወደ ኢህአዴግ ከፍተኛ ካድሬነት ተለውጦ፣ ከካድሬነት የፕሬስ ድርጅት ኃላፊ ሆኖ ተገኘ።

ተስፋዬ ገብረአብ በፍጥነት ወደ ስልጣን የመጣበት መንገድ ያሳደረበትን አግራሞት በአንደኛው መጽሐፉ እንዲህ ብሎ እንደገለጸው አስታውሳለሁ።

“የሄድኩበት ፍጥነት “ሰኞ ተወለድኩ፣ ማክሰኞ ተረገዝኩ፣ ዕሮብ ክርስትና ተነሳሁ፣ ሐሙስ እንጨት ለቀማ ሄድኩ” የሚለውን የስንዝንሮን ታሪክ የሚያስታውስ ነበር”

የተስፋዬ የዚህ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሆኖ መሾም ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ ከመሾሙ አራት ዓመት ቀደም ብሎ (በ1979) በዚህ መሥሪያ ቤት የጋዜጣ ሪፖርተርነት ቦታ እንዲሰጠው በማመልከቻ ጠይቆ በመሥሪያ ቤቱ ኃላፊ ምላሽ ተነፍጎት የነበረ መሆኑ ነው። የያኔው የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊ ታዋቂው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ነበር። ደርግ እስኪወድቅ ድረስ መሥሪያ ቤቱን የመራው እርሱ ብቻ ነው። እርሱ ከስልጣኑ ተነስቶ ነው ተስፋዬ ገብረአብ በቦታው የተሾመው።

እስቲ አንድ አፍታ ወደ ኋላ ልመልሳችሁ!!

ተስፋዬ ገብረአብ በኢህአዴግ ታጋዮች በተማረከበት ወቅት ኦህዴድ የሚባለው ድርጅት ምሥረታ እየተካሄደ ነበር። በምሥረታው ማግስት በተካሄደው የደስታ ማብሰሪያ ፕሮግራም ላይ (እነርሱ “የተሓድሶ ፕሮግራም” ይሉታል) ላይ ተገኝቶ የታዘበውን ሁሉ አውግቶናል። ከዚያ የተሐድሶ ዝግጅት በኋላ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ብዛት ከሁለት ወደ ሶስት አድጎአል (ህወሓት፣ ኢህዴን እና ኦህዴድ ናቸው። “ኢህዴን” በኋላ ላይ ስሙን ወደ “ብአዴን” ቀይሯል)። ከህወሓት በስተቀር ሌሎቹ ድርጅቶች አባላት የሚመለምሉት በምርኮ ተይዘው በእጃቸው ከነበሩት የኢትዮጵያ ጦር ባልደረቦች ነበር። ይህንንም ሲያደርጉ ብሄረሰብን እንደ መመልመያ መስፈርት ያስቀምጡ ነበር። ይሁንና መስፈርቱ ኤርትራዊ ደም በነበራቸው የተስፋዬ ገብረአብ ዓይነት ሰዎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የማይመች ነበር። በመሆኑም ተስፋዬ በመጀመሪያው ላይ የሶስቱም ድርጅቶች አባል ሳይሆን በኢህአዴግ አባልነት ብቻ ይንቀሳቀስ ነበር።

ከአጭር ጊዜ በኋላ በቆቦ አካባቢ በተደረገ ከባድ ውጊያ ላይ የኢህአዴግ ጦር አንድ ጄኔራልን ጨምሮ ብዙ መኮንኖችን ማረከ። የኢህአዴግ መሪዎችም በነዚህ መኮንኖች ለመጠቀም ስለፈለጉ እነርሱን የሚያሰባስቡበት አንድ ድርጅት ፈጠሩ። ድርጅቱም “የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ መኮንኖች አንድነት ንቅናቄ” (ኢዴመአን) ተብሎ ተሰየመ። በዚህ ድርጅት ምሥረታ ማግስት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ብዛት ከሶስት ወደ አራት አደገ። ሻምበል ሱለይማን ደደፎ፣ ኮሎኔል አሳምነው በዳኔ፣ ኮሎኔል ዓለምእሸት ደግፌን ጨምሮ በርካታ መኮንኖች የኢዴመአን መሪዎች ሆነው ተሰየሙ። ምክትል የመቶ አለቃ ተስፋዬ ገብረአብም የዚህ ድርጅት አባል ሆነ።

ይህ ኢዴመአን የሚባለው ንቅናቄ የኢህአዴግ አባል ድርጅት ሆኖ የቆየው ከሁለት ዓመት ተኩል ላልበለጠ ጊዜ ነው። በ1985 አጋማሽ ላይ ግን ፈርሶአል። ለመፍረሱ ምክንያት የሆነው “ወታደሮች የፖለቲካ ድርጅት መመሥረት አይችሉም” የሚል ጭቅጭቅ በያኔው የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በመነሳቱ ነው። ድርጅቱ ሲፈርስ አባላቱ የነበሩት መኮንኖች ወደ ሶስቱ የብሄር ድርጅቶች ተላልፈዋል። በዚህም መሠረት እነ ሱለይማን ደደፎ የኦህዴድ አባላት ሲሆኑ ቤተሰቦቹ ትግርኛ የሚናገሩት ተስፋዬ ገብረአብ ደግሞ የህወሓት አባል እንዲሆን ተደርጓል። ሌሎች መኮንኖች ወደ ያኔው ኢህዴን ገብተዋል (እነ ዓለምእሸት ደግፌ የመከላከያ ሠራዊቱን ተቀላቅለው በውትድርና ሙያቸው ቀጥለዋል)። ኢዴመአን ከፈረሰ በኋላ ኢህአዴግ በደቡብ አካባቢ በየብሄሩ የመሠረታቸውን ድርጅቶች አንድ ላይ አሰባስቦ “ደኢህዴን” የሚባለውን ንቅናቄ በመፍጠር አራተኛው የግንባሩ አባል ድርጅት እንዲሆን አድርጓል። ይህም በ1986 መጀመሪያ ላይ የተፈጠረ ክስተት ነው።

ይህንን ጉዳይ ያነሳሁት ያለ ምክንያት አይደለም። ተስፋዬ ገብረአብ የህወሓት አባል የሆነበት መንገድ በደንብ ስላልተነገረ ነው እዚህ የጠቀስኩት። አንዳንዶችም ተስፋዬ የኤርትራ ማንነቱን ደብቆ ወደ ህወሓት የመጣ ሰርጎ ገብ እና የሻዕቢያ ሰላይ እንደሆነ ሲተርኩ በማየቴም ነው እዚህ የምጽፈው። በተለይም የወያኔ አባላትና ካድሬዎች ተስፋዬ ገብረአብ “የጋዜጠኛው ማስታወሻ”ን ከጻፈ በኋላ ያልሆነ ስም እየሰጡት ሊበክሉት ዳክረዋል። ራሳቸው በግልጽ የተገበሩትን አሰራር እየካዱ ልበ-ወለዳዊ ትርክቶችን በመፍጠር የተስፋዬን የሻዕቢያ ሰላይነት ሊያስረግጡልን ብዙ ጥረዋል።

ተስፋዬ ቤተሰቦቹ ከኤርትራ ወደ መሃል ሀገር መምጣታቸውን ሸሽጎ አያውቅም። ኢህአዴጎቹ የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ background ያለው መሆኑን በማየት የህወሓት አባል አደረጉት። እነርሱ ሊያጠፉት ሲፈልጉት አምልጦአቸው ወደ ውጪ ሲሄድ ደግሞ “የሻዕቢያ ሰላይ” ነው ይሉናል (እንዲያውም አስታወስኩ! የአማራ ተወላጅ የሆነው “ጌታቸው ሴኩቱሬ” እንኳ የህወሓት አባል ሆኖ አልነበር እንዴ? ተስፋዬ የህወሓት አባል ሲሆን “ለስለላ ወደ ህወሓት የመጣ የሻዕቢያ ሰርጎ ገብ ነው” እያሉ ይዘላብዳሉ። የሱኩቱሬ የሕወሓት አባልነት ግን ከመጤፍ አይቆጠርም። ይገርማል እኮ!)።

(ይቀጥላል)

የዚህን ፅሁፍ ተከታታይ ክፍሎች በሚከተሉት ሊንኮች ያግኙ

የአድአው ጥቁር አፈር (ዝክረ ተስፋዬ ገብረአብ) ክፍል ፩  https://bit.ly/3qUYHVI

የአድአው ጥቁር አፈር (ዝክረ ተስፋዬ ገብረአብ) ክፍል ፪  https://bit.ly/3t6G6IY

የአድአው ጥቁር አፈር (ዝክረ ተስፋዬ ገብረአብ) ክፍል ፫  https://bit.ly/3f1MDMQ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s