Arts

የአድአው ጥቁር አፈር (ዝክረ ተስፋዬ ገብረአብ) ክፍል ፫

ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ

ተስፋዬ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ኃላፊ ሆኖ በመሾሙ አልተደሰተም። “ከችሎታዬ በላይ እና ከፍላጎቴ ውጪ ነው የተሾምኩት” እያለ ለኃላፊዎቹ ይናገር ነበር። እያደር ደግሞ መሥሪያ ቤቱ የጭቅጭቅና የአምባጓሮ መድረክ ሆኖ አገኘው። የኢህአዴግ የፕሮፓጋንዳ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ የነበረው በረከት ስምኦን እና የደህንነት መሥሪያ ቤቱ በፕሬስ ድርጅት ስር በሚታተሙት ጋዜጦች ላይ ለሚወጡ እንከኖች የተለያዩ ትርጉሞችን እየሰጡ ያጨናንቁት ጀመር። በውስጥ ደግሞ ኢህአዴግን የሚቃወሙ የደርግ ዘመን ጋዜጠኞች በጋዜጦቹ ላይ በረቀቀ ሁኔታ መልእክታቸውን እያወጡ ተስፋዬንና ሃላፊዎቹን ያጋጩ ነበር (ለምሳሌ በአንደኛው እሁድ በክፍሌ ሙላት ሃላፊነት ይዘጋጅ በነበረው “አድማስ” የተሰኘ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመዝናኛ አምድ በወጣ ግጥም በመጀመሪያ ረድፍ ላይ ያሉት ፊደሎች ከላይ ወደ ታች በአንድ ላይ ሲነበቡ “ትግራይ እስክትለማ፣ ሌላው ሀገር ይድማ” የሚል ዐረፍተ ነገር ይሰሩ ነበር። በግጥሙ መውጣት አዲስ አበባ በሙሉ ነበር የታመሰው። እኛ ገለምሶ ያለነው በኢህአዴግና በኦነግ መካከል በተፈጠረው ጣጣ ሳቢያ ጋዜጣው ባይደርሰንም ወሬው በጣም popular ሆኖ ተወርቶ እንደነበረ አስታውሳለሁ)።

ተስፋዬ ገብረአብ የፕሬስ ድርጅት ኃላፊነትን የጠላበት ሌላ ምክንያትም ነበር። ይህም አዲስ ዘመን፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ በሪሳ፣ Ethiopian Herald እና “አል-ዐለም” የተሰኙት ጋዜጦች የመንግሥትን ፕሮፓጋንዳ ከማራገብ በስተቀር ከተስፍሽ ውስጥ ሲንተከተክ የነበረው የስነ-ጽሑፍ ጥሪ ምላሽ የሚያገኙበት መድረክ ለመሆን የማይችሉ መሆናቸው ነው። በዚህም የተነሳ ወደ ሌላ ምድብ የሚቀየርበትን አጋጣሚ ይጠባበቅ ጀመር።

ተስፋዬ ሲጠብቀው የነበረው አጋጣሚ በመጋቢት ወር 1984 ተከሰተ። የያኔው የሽግግር መንግሥት “ማንኛውም ጋዜጠኛና የስነ-ጽሑፍ ሰው መንግሥት ያወጣውን ህግ ተከትሎ የግሉን ጋዜጣ እና መጽሔት መክፈት እንደሚችል አወጀ። በ1966-1969 በነበሩት ዓመታት በደበዘዘ መልኩ ታይቶ የጠፋው የፕሬስ ነፃነት በ1984 በድጋሚ በሀገራችን ተከሰተ።

ተስፋዬ ገብረአብ በአጋጣሚው ለመጠቀም ወሰነ። ዓለም ሰገድ ገብረአምላክ፣ በረከት ስምኦን፣ ገብረመስቀል ኃይሉ ከመሳሰሉት የኢህአዴግ የፕሮፓጋንዳ ኃላፊዎች ዘንድ ቀርቦ “የደርግ ስርዓት የሰራቸውን ወንጀሎች የሚያጋልጥ፣ የድርጅታችንን ዓላማ እና ግብ በተዋዛ መንገድ የሚያሳውቅ፣ ህብረተሰቡንም እያዝናና የሚያስተምር፣ የንባብ እና የጽሑፍ አብዮትን የሚያቀጣጥል የራሳችንን መጽሔት እንድከፍት በጀትና ሎጂስቲክስ ይፈቀድልኝ” በማለት ጠየቀ። የኢህዴን/ብአዴን ሁነኛ ሰው የነበረው አቶ በረከት ስምኦን ከተስፋዬ ገብረአብ ጋር በገባበት ጠብ የተነሳ ሀሳቡን ውድቅ አደረገው። የፕሮፓጋንዳው ወሳኝ ሰው የነበረውና ስለዘመኑ ሁኔታ ከበረከት በተሻለ መንገድ ይገነዘብ የነበረው ታጋይ ዓለምሰገድ ገብረአምላክ ግን በሀሳቡ ተስማማ።

ተስፋዬ ገብረአብ በፕሬስ ድርጅት ኃላፊነቱ እየሰራ አዲሱን መጽሔት ለመመሥረት የሚያስችሉ ስራዎችን በፍጥነት ከወናቸው። ሀሳቡን የገለጸላቸው የዘመኑ ታዋቂ ጋዜጠኞች እና ደራሲዎች አብረውት ሊሰሩ ፈቃዳቸውን ገለጹ። ስብሓት ገብረእግዚአብሄር፣ የሺጥላ ኮከብ (የ“ወገግታ” መጽሐፍ ደራሲ)፣ ቴዎድሮስ ሙላቱ (የ“አኬል ዳማ” መጽሐፍ ደራሲ)፣ ደምሴ ጽጌ (በኋላ ላይ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው)፣ ደረጄ ደስታ (አሁን የቪኦኤ ባልደረባ ነው)፣ መኩሪያ መካሻ (አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር ሆኗል) እና ሌሎችም በመጽሔቱ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሆነው ይጠብቁ ጀመር። ተስፋዬም አዲሱን መጽሔት የሚያሳትመውን ድርጅት “እፎይታ ጋዜጣና መጽሔት ኃ/የተ/የግል ማህበር” በማለት ሰየመው። ይህም ከያኔው የማስታወቂያ ሚኒስቴር እውቅና ያገኘ የመጀመሪያ ድርጅት ለመሆን በቃ (ያኔ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት ለረጅም ጊዜ ከኦነግ አመራር አባላት መካከል አንዱ ሆነው የሰሩት አቶ ዲማ ኖጎ ናቸው)።

እነሆ! ከተስፋዬ ገብረአብ ጋር ስሙ የተያያዘው “እፎይታ” የተሰኘው ዝነኛው መጸሔት በሚያዚያ 1984 ተወለደ። የአድአው ጥቁር አፈርም ለረጅም ጊዜ ሲመኝ የነበረውን የጋዜጠኛነትና የጸሐፊነት ጉዞውን በዚህች መጽሔት ልደት ማግስት ጀመረ። ከ1985 መጨረሻ ጀምሮ ራሱን ከፕሬስ ድርጅት ኃላፊነት በማግለል በመጽሔቱ ላይ አተኮረ።

ጓዶች!

“እፎይታ” የኢህአዴግ የፕሮፓጋንዳ መጽሔት የነበረ መሆኑን አልዘነጋውም። ይህ መጽሔት በተለያዩ ወቅቶች ባወጣቸው ዘገባዎቹም ልባችንን አቁስሎአል። ይሁንና በጅምሩ ላይ የነበረው እፎይታ መጸሔት ሲሄድበት የነበረው መንገድ በኋላ ላይ ካመጣው ደረቅ የፕሮፓጋንዳ ወጀብ በእጅጉ የተለየ መሆኑን ማስታወስ አለብን። በርግጥም የእፎይታ መጽሔት ቀዳሚ እትሞች በምርጥ ጽሐፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ደራሲዎች የተቀናበሩ፣ እንደ ሃላዋ የሚጣፍጡ ጽሑፎችን ይዘው ነበር የሚወጡት። ተስፋዬ ገብረአብም በአብዛኛው በብዕር ስሞች እየተጠቀመ ጣፋጭ ጽሑፎችን ይጽፍ ነበር። ይህንንም ለማረጋገጥ ካሻችሁ የአዲስ አበባው ፒያሳ ሲኒማ ኢትዮጵያ አካባቢ ሄዳችሁ የቆዩ መጽሔቶችን ከሚሸጡ ልጆች ላይ የተወሰኑ እትሞችን ግዟቸው።

በእፎይታ መጽሔት ላይ ከወጡት የተስፋዬ ጽሑፎችና ዘገባዎች መካከል “የእድሩ ስም ጠሪ”፣ “የልደት በዓል ጥሪ” ፣ “የቁርቁራ ራእይ” ፣ “ወንድሙ ጩበሮ”፣ የመንግሥቱ አንጋች ትዝታ፣ “አግዓዚ ኦፕሬሽን”፣ “ጆሃንስበርግ ደርሶ መልስ”፣ ከአዲስ አበባ እስከ ጨንቻ፣ የቁንድዶ ፈረሶች፣ የመቀሌ ጥንታዊ ቀልዶች፣ “የአፍሪቃ ልጆች” ፣ ትዝ ይሉኛል። እንደ ጋዜጠኛ ሆኖ ካጠናቀራቸው ቃለ ምልልሶች መካከልም ከኦሮሚያ ክልል የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት አቶ ሐሰን ዓሊ፣ ከመዐህድ መሥራች ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ ከኤርትራዊው ጄኔራል ስብሓት ኤፍሬም፣ ከአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ እና ጄኔራል ኃየሎም አርአያን ከገደለው ጀሚል ያሲን ጋር ያደረጋቸው በጣም ይታወሳሉ። ከተስፋዬ ሌላም ጋሽ ስብሓት ገብረእግዚአብሄር አጋፋሪ እንደሻው ከሞት የሚያደርጉትን ሽሽት የሚተርኩባቸው ተከታታይ የልብ ወለድ ጽሑፎች በመጽሔቱ ላይ እየቀረቡ ከፍተኛ አድናቆት አትርፈዋል። ደረጄ ደስታ በሰላ ብዕሩ ይጽፋቸው የነበሩት መጣጥፎችም ዘወትር ይታወሳሉ። “ቆምጬ አምባው” ለሚባሉት ኢትዮጵያዊ ቃል ምልልስ አድርጎ በእርሳቸው ስም ከሚነገሩት አዝናኝ ቀልዶች ጋር በማዛነቅ ለብዙ አንባቢያን ያስተዋወቃቸው ደረጄ ደስታ ነው። ይህም የተፈጸመው በእፎይታ መጽሔት አማካኝነት ነው። በሩሲያ ሀገር የተማረው ጋዜጠኛ መኩሪያ መካሻ ደግሞ የእነ አንቶን ቼኾቭን፣ የነ ኒኮላይ ጎጎልን፣ የነ ኢቫን ቱርጊኔቭን አጭጭር ታሪኮች ወደ አማርኛ እየተረጎመ ለመጽሔቱ ተወዳጅነት የበኩልን አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ከሁሉ በላይ የማልዘነጋው አንድ የእፎይታ መጽሔት ቀዳሚ አምደኛ አለ። ይህ ሰው በትክክለኛ ስሙ “ፍቅሩ ዮሴፍ” ይባላል። የኢህአፓ ታጋይ ከሆነ በኋላ ደግሞ “ህላዌ ዮሴፍ” ተብሏል። ህላዌ ከኢህአፓ ወጥቶ ከጓደኞቹ ጋር ኢህዴንን ሲመሠርት የድርጅቱ አመራር አባል ሆኖ ነበር። ከደርግ ውድቀት በኋላ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባነትን ጨምሮ የተለያዩ ስልጣኖች ተሰጥተውት እንደነበረ ይታወሳል።

“ፍቅሩ ዮሴፍ” በእፎይታ መጽሔት መጻፍ የጀመረው ከአንደኛው እትም ጀምሮ ነው። እርሱ ያተኮረበት ርእስ ደግሞ ደርግ በአዲስ አበባ ከተማ “ቀይ ሽብር” የተባለውን ዘመቻ አውጆ በኢህአፓ አባላት ላይ ያካሄደው አሰቃቂ ምንጠራ ነው። በዚያ ዘመን በቀይ ሽብር የተሳደዱና የተሰቃዩ በርካታ ሰዎች በሕይወት ነበሩ። በመሆኑም የፍቅሩ ዮሴፍን ጽሑፎች በከፍተኛ ጉጉት ነበር ያነበቡት። እንደዚሁም ደግሞ ፍቅሩ ሞተዋል ብሎ የጠቀሳቸው ብዙ ሰዎች “አረ አልሞትኩም! ደርግ ሊረሽነን ከወሰደኝ በኋላ አምልጬ ወደ ውጪ ሀገር ወጥቻለሁ” እያሉ በመጽሔቱ ላይ ትዝታቸውን እንዲጽፉ ቀስቅሶአቸው ነበር። በሌላ በኩል በኮሎኔል መንግሥቱ ላይ መስከረም 13/1969 የተካሄደውን የግድያ ሙከራ የመራውንና መምህር በላይነህ ገበረማሪያም” የሚባለውን ዝነኛ የኢህአፓ አባል ጨምሮ ሌሎች ስመጥር የኢህአፓ ሰማእታትን ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሑፍ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስተዋወቀው ፍቅሩ ዮሴፍ ነበር። አንጋፋው የኢህአፓ አባል አቶ ክፍሉ ታደሰ ከዓመታት በኋላ የኢህአፓን የትግል ታሪክ የሚዘክረውን “ያ ትውልድ!” የተሰኘ መጽሐፍ ሲጽፉ ፍቅሩ ዮሴፍ በእፎይታ መጽሔት ላይ የጻፋቸውን ጽሑፎች እንደ ዋቢ አድርገው በሰፊው ተጠቅመዋል። በነዚያ ቀዳሚ ዓመታት በመጽሔቱ የወጡት የፍቅሩ ዮሴፍ ጽሑፎች ለእፎይታ መጽሔት ተወዳጅነት ከፍ ያለ ሚና ተጫውተዋል።

በእርግጥ ነው የምላችሁ!! “እፎይታ” መጽሔት በኋላ ላይ “ኦሮሞ ጥቁር ጀርመን ነው?”፣ “ኦነግ ከባሕር የወጣ አሳ”፣ “የመዐሕድ የጎሸ ፖለቲካ”፣ “ጂሃዳችን ያነጣጠረው በሻዕቢያ ላይ ነው” በሚሉት ውሸት ቀመስ መጣጥፎቹ አንጀታችንን ቢያሳርርም በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ሰፊ የእውቀት መድረክ ሆኖ አገልግሏል። በዚያ ለጋ ዕድሜያችን በቋሚነት ከምንከታተላቸው መጽሔቶች አንዱ “እፎይታ” መሆኑን አልደብቃችሁም (እኔ አፈንዲ ከእፎይታ ሌላ “ሳሌም”፣ “አሌፍ”፣ “ቢላል” እና “ሩሕ” የሚባሉትን መጽሔቶች በፍቅር እከታተላቸው ነበር። “ጦቢያ”፣ “ኢትዮጲስ”፣ “ማለዳ”፣ “ሙዳይ” የመሳሰሉት ግን ከመነሻው ጀምሮ ደባሪዎች ነበሩ። “ጦቢያ” መጽሔት በብዙዎች የተነበበው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። እርሱም በቅርቡ ያረፉት የደርግ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን አቶ ካሳ ከበደ ለመጽሔቱ ቃለምልልስ የሰጡበትና ዶክተር መረራ ጉዲና ከብዙዎች ጋር ያስተዋወቃቸውን አነጋጋሪ ጽሑፋቸውን በተከታታይ በመጽሔቱ ላይ ያቀረቡበት የ1987 የበጋ ወራት ወቅት ነው)።

“እፎይታ” መጀመሪያ ሲወጣ መጽሔት ብቻ ነበር። በኋላ ደግሞ “ጋዜጣ” ጭምር ሆኖ መጥቷል። ታዲያ ተስፋዬ ገብረአብ የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ ቢሆንም አንድም ጊዜ “አዘጋጅ” በሚል ስሙ በመጽሔቱ ላይ ተጠቅሶ አያውቅም። በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የዋና አዘጋጅም ሆነ የምክትል አዘጋጅ ስም በመጽሔቱ ላይ ወጥቶ አያውቅም። ከዓመታት በኋላ ግን ዋና አዘጋጁ “ዋለልኝ ብርሃነ” መሆኑ ተነገረን። ምክትል ዋና አዘጋጁም “ሱልጣን አባዋሪ” ተብሎ ይጻፍ ጀመር። እኛ ባዳ የሆንነው ሰዎች እነዚህ ስሞች በሕይወት ያሉ ግለሰቦችን የሚወክሉ ይመስሉን ነበር። ተስፋዬ ገብረአብ “የጋዜጠኛው ማስታወሻ”ን በጻፈ ማግስት ግን ከውስጠ አዋቂዎች አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ በፈቃዱ ሞረዳ “የብዕር ስሞች ናቸው” በማለት ሚስጢሩን አፈነዳው። ተስፋዬን ስንጠይቀው ደግሞ እውነት መሆኑን አረጋገጠልን።

በዚህም መሠረት “ዋለልኝ ብርሃነ” የተስፋዬ ገብረአብ የብዕር ስም ነው። “ሱልጣን አባዋሪ” የተባለው ደግሞ መኩሪያ መካሻ ነው።

ከላይ እንደገለጽኩት “እፎይታ” መጽሔት በጀመረበት ማራኪ አቀራረብ መቀጠል አልቻለም። በጊዜ ሂደት አቀራረቡም ሆነ ይዘቱ ተቀይሮ አሰልቺ የፕሮፓጋንዳ ድርሳን ሆኗል። ለውድቀቱ መንስኤ የሆኑት የኢህአዴግ የፕሮፓጋንዳ ሙጋሎች በዝግጅቱ ሂደት ጣልቃ እየገቡ በመጽሄቱ ላይ በሚወጡት ጽሑፎች ይዘትና ጭብጥ ላይ ውሳኔ መስጠት መጀመራቸው ነው።

ተስፋዬ ገብረአብ በኢህአዴግ አውራዎች ጣልቃ ገብነት ቢከፋም ከእነርሱ ለመሽሽ አልሞከረም። ከዚያ ይልቅ ከእነርሱ ጋር ሆኖ ከውስጥ የሚንተከተከውን የጥበብ ጥሪ የሚያሟላበትን ሌላ መንገድ መሻትን ነው የመረጠው። በዚህም መሠረት “ፋና ዴሞክራሲ አሳታሚ” የተባለ ድርጅት አቋቁሞ ወደ ትክክለኛው የጽሑፍ መድረክ ገባ። “እፎይታ አሳታሚ” የተሰኘው ድርጅት እንዲዘጋ ተወስኖ የ“እፎይታ” መጽሔት ህትመት በዚህኛው ድርጅት ባለቤትነት እንዲከናወን ተደረገ። በዚህም ድርጅት አማካኝነት “ተስፋዬ ገብረአብ” የተሰኘ ስም በመጻሕፍት ሽፋን እና በመጻሕፍት የውስጥ ገጾች ላይ መታየት ጀመረ። በዚህም መንገድ አንዳንዶች “አወዛጋቢ” የሚሉትና ሌሎች “ተደናቁው” እያሉ የሚያወድሱት ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ወደ ታሪክ መድረክ ብቅ አለ።

ይቀጥላል

የዚህን ፅሁፍ ተከታታይ ክፍሎች በሚከተሉት ሊንኮች ያግኙ

የአድአው ጥቁር አፈር (ዝክረ ተስፋዬ ገብረአብ) ክፍል ፩  https://bit.ly/3qUYHVI

የአድአው ጥቁር አፈር (ዝክረ ተስፋዬ ገብረአብ) ክፍል ፪  https://bit.ly/3t6G6IY

የአድአው ጥቁር አፈር (ዝክረ ተስፋዬ ገብረአብ) ክፍል ፫  https://bit.ly/3f1MDMQ

One thought on “የአድአው ጥቁር አፈር (ዝክረ ተስፋዬ ገብረአብ) ክፍል ፫

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s