Culture & Lifestyle

​ፓስተሮቹ ምን እየሰሩ ነው?

በአብይ ሰለሞን

መንደርደርያ

ኢትዮጵያ በአለም ከምትታወቅባቸው ዋነኛው የጥንታዊ ስልጣኔና የራሷ የሆነ ልዩ ሀይማኖታዊ ማንነቷና ባህሏ ነው። በኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶና እስልምና ረዥም ታሪክ ያላቸው ሃይማኖቶች  ሲሆኑ ተመሳሳይ የኦርቶዶክስም ሆነ የእስልምና ሃይማኖቶች በሌላው አለም ካላቸው ስርዓትና ምዕመኖች ራሱን የቻለ እጅግ ልዩ የእምነት፣ የመቻቻል፣ ልዩ ስርዓትና ቅርሶች ባለቤት ናቸው። ብዙ ታዛቢዎች፣ ተጓዦችና የታሪክ ፀሃፊዎች በተደጋጋሚ ስለሃገሪቱ ልዩ ሃይማኖታዊ ባህል የተናገሩትን ስንመለከት ህዝቡና ሀገሩ ለእምነቱ ያለውን ፅኑ መሰጠት፣ ቅን ልቦናና ቅንአት እንረዳለን። ታላቁ አሜሪካዊ የነፃነት ታጋይ ማርከስ ጋርቬይ ሲናገር፣ “አዲስ ኢትዮጵያን እናያለን፣ አዲስ አፍሪካ፣ በመልካም ተፅዕኖዋ አለምን ስታዳርስ። ለሰውልጅ የህይወትን መንገድ እያስተማረችች፤ ለሰው ልጅ የእግዚአብሄርን መንገድ እያመላከተች።” ይለናል።

በሃገሪቱ ታሪክ በአብዛኛው የኦርቶዶክስ ክርስትና እና እስልምና ጉልህ ሃይማኖቶች ሆነው ቢዘልቁም በተለያዩ የታሪክ ሁነቶች የተለያዩ  ሀይማኖቶች ወደ ሃገሪቱ ገብተው ቤተ-አምልኮ በመመስረት የራሳቸውን ተከታይ ምዕመናን ማፍራት ችለዋል። ሆኖም የደርግ መንግስት ሀይማኖት ላይ በነበረው ተቃውሞ ምክንያት እምነታቸውን በነፃነት ሊያስፋፉና ተጠቃሽ በሆነ መልኩ ተከታይም ሊያፈሩ አልቻሉም። ከነዚህ ሃይማኖቶች አንደኛውና ዋነኛው የፕሮቴስታንት እምነት ነው።

በ 1983 ዓ.ም የደርግ መንግስት መውደቅን ተከትሎ መንግስት በሰጠው የሃይማኖት ነፃነት የፕሮቴስታንት እምነት ከሌሎቹ ሃይማኖቶች ቤተ-አምልኮዎችን በመመስረትና ሃይማኖታዊ አስተምህሮቱን በማዳረስ እጅግ በፍጥነት መስፋፋትና በአጭር ጊዜ ውስጥም ሰፊ ተከታይ ምእመናንን ማፍራት ችሏል። የፕሮቴስታንት ሃይማኖት በሃገሪቱ ከነበሩ ቀደምት ሃይማኖቶች አንፃር ካለው የአምልኮና የመፅሃፍ-ቅዱሳዊ ኃሳብ ነፃነት፣ ዘመናዊና አለማዊ ስርአቶችን በቀላሉ ከመንፈሳዊው ጋር ማዋሀዱ እንዲሁም ቀድሞ ከሚታወቁ የክርስትና አስተምህሮቶች በተወሰነ መልኩ የተለየ ዶክትሪን ይዞ መቅረቡ በተለይ በ 1980ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት ላይ የተወሰነ ተቃውሞና እንዲገጥመውና በጥርጣሬ እንዲታይም ሊያደርገው ችሏል። በ SOAS ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ለንደን ተመራማሪ የሆነው ጆርግ ሁስተን “የፔንቴኮስታሊስም አጭር ታሪክ በኢትዮጵያ” በሚለው ፅሁፉ፣ “በጅምር ወንጌልን የማስፋፋት እንቅስቃሴያቸው ፔንቴኮስታላዊ ቤተክርስትያኖች ሰፊ የሆነ ሃይማኖታዊ ተቃውሞ ኢላማ ነበሩ። እናም በዚህን ጊዜ ስራቸውን በአብዛኛው በትንንሽ መጠለያዎች ውስጥ ገድበው ለመቆየት ተገደው ነበር። ይህ ተፅዕኖ ፔንቴኮስታል አስተምህሮ ውጪ ከሆኑ ሌሎች የክርስትናና የሚሽን ሃይማኖቶች ጭምር የሚመጣ ነበር። የዚህ ተፅዕኖ አንዱ የአደባባይ መገለጫ ማንኛውም ወደ ፔንቴኮስታላዊ ኃይማኖቱን የቀየረን ሰው የማናናቅ አንደምታ ያለው “ጴንጤ” የሚል ስያሜ የመስጠት ል

ሃይማኖቱ በነዚህ ተፅዕኖና ተግዳሮቶች አልፎ ዛሬ በኢትዮጵያ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች የጠቅላላ ህዝብ ብዛቱን ወደ 20% በመሸፈን ወደ 17 ሚሊየን እንደሚጠጋ ይታመናል። እንደ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ህብረት መረጃ መሰረት በህብረቱ ውስጥ 56 እና 100 ተባባሪ ቤተ-እምነቶች ሲኖሩ ይህም ከአጠቃላይ የወንጌል አማኞች 97 በመቶውን ይወክላል። የህብረቱ ድረ-ገፅ እንደሚጠቁመውም ወደ 29,805 አብያተ-ክርስትያናት በነዚህ ቤተ-እምነቶች ስር ይተዳደራሉ። የፕሮቴስታንት እምነት ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ በደረሰበት ሰዓት ከተለያዩ አለም አቀፍ የእምነቱ ተፅዕኖዎችና የእድገት ሂደቱ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው የአመለካከት አቅጣጫዎች ልዩነት መብዛት ነፀብራቅ ሊሆን በሚችል መልኩ አያሌ ህብረተሰባዊም ሆነ ሀገራዊ ጉዳዮችን የሚነኩ የሞራልና የመንፈሳዊነት ጥያቄ የሚያስነሱ ክስተቶች የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስትያኖች ውስጥ እየታዩ ነው።&nb

ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ከወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ዶክትሪን እንዲሁም መንፈሳዊ ብለን ከተቀበልናቸው ልምምዶችና ተግባራት ፍፁም በተለየ መልኩ የተለያየ አመለካከትና አቋም የሚያራምዱ አብያተ ክርስትያናትና ፓስተሮች እየታዩ ነው። ይህን ፅሁፍ በሚቀጥለው እትማችን እንደምናወጣ በቀዳሚው እትማችን ስንገልፅ ሰዎችን ለአስተያየት ጋብዘን ነበር። መፅሄቱ ከወጣ በማግስቱ ጀምሮ ባነሳነው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተበዳይ ነን የሚሉ የተለያዩ የስልክ ጥሪዎች አስተናግደናል። ከነዚህም ውስጥ ውጭ ሰርታ ያጠራቀመችውን ገንዘብ ይባረክልሻል፣ ይበዛልሻል በማለት የተወሰደባት፣ ከእኔ ጋር እንድታድሪ አምላክ አዟል በማለት ባሏ የእኔ ነው ብሎ እያሳደገው ያለ ልጅ በመውለድ ለህሊና እስራት የተዳረገች፣ ነብይ በተባሉ አገልጋዮች ከትዳራቸው እንዲፋቱ የታዘዙ ወንዶችና ሴቶች…ወዘተ።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ ብቻ የተፈጠረ ሳይሆን በተለያዩ የአፍሪካና ሌሎችየ 3ኛው አለም ሀገራት ውስጥ የተፈጠረ ሁነትም ነው። Christianity Today የተባለው ሃይማኖታዊ የሚድያ ድረ-ገፅ በቅርቡ እንዳስነበበው ጎረቤታችን ኬንያ በአቃቤ ህጓ አማካኝነት ሀሰተኛ አብያተ ክርስትያናትን ከማገዷ በተጨማሪም አንድ ቤተ ክርስትያን እውቅና ስታገኝ እንደ የፓስተሮቿ የስነ-መለኮታዊ ትምህርት ደረጃ፣ አመታዊ የአባልነት ክፍያ ኮታ እና የአብያተክርስትያናት ህብረትን መቀላቀል ያሉ ሟሟላት ስላለባት ቅድመ ሁኔታዎች የሚደነግግ አዋጅ አውጥታለች። የኬንያ የኮሚንኬሽን ሚንስትር በበኩሉም በስርጭታቸው ምዕመናንን የገንዘብ ስጦታ እንዲያበረክቱ የሚጠይቁ ኃይማኖታዊ ሬድዮና ቴሌቭዥኖችን የሚያግድ አዲስ ፖሊሲ እስከማውጣት ደርሷል። ይህን እርምጃ አስመልክቶ ቄስ ቤኔ ሳላህ የተባሉ የአንድ የኬንያ ወንጌላዊ ቤተክርስትያን አገልጋይ ሲናገሩ፣ “አስከፊ ነገሮች በቤተክርስትያን ውስጥ እየተከናወኑ ያለበት ጊዜ ላይ ነው የምንገኘው። ወንጌል እጅግ በተራቀቀ ሁኔታ ለንግድ ቀርቧል።” ይላሉ።

ይህ ጉዳይ በሀገራችን ያለውን ገፅታ፣ ተፅዕኖ እና የአካሄድ አቅጣጫ አንድ ራሱን የቻለ ማህበራዊ ቀውስ ወደመሆን ደረጃ የደረሰውን ይህን ጉዳይ በአጭሩ ለመዳሰስ ሞክሯል።

መንፈሳዊ አገልግሎትን በገንዘብ (Simony) እና የብልፅግና ወንጌል

በአንድ በኢንተርኔትና በስማርት ስልኮች በሰፊው በተሰራጨ ቪድዮ ላይ ፓስተር ዳዊት ሞላልኝ ከአንድ ፓስተር በተለምዶ በማንጠብቀውና አዝናኝ በሆነ መልኩ የሚናገረውን ኃሳብ በሰውነቱም ጭምር እየገለፀ ይታያል። “ሩኒን በቅርብ ጊዜ ሲያስፈርሙት በሳምንት 300,000 ፓውንድ ነው ደሞዙ። ይህን ስንቀይረው የወር ደሞዙ ወደ 40,000,800 ብር አካባቢ ይመጣል። አስቡት ወይኔ…ወይኔ ከተሰበረ እኮ ኳስ አይጫወትም ለወር፤ ሳይጫወትም 40 ሚሊየን ይከፈለዋል።ስማ! እሱኮ ኳስ እያባረረ ነው፤ እኔ አጋንንትህን እያባረርኩልህ…” በማለት ፓስተር ይቀጥላል።

ይህ ንግግር በኢትዮጵያዊ ክርስቲያናዊ ባህል ውስጥ ላደገ (ኦርቶዶክሳዊም ሆነ ፕሮቴስታንታዊ) በመጀመሪያ እይታው የፓስተር ዳዊት ንግግርና ዲስኩር ፍፁም እንግዳ እንደሚሆንበት እርግጥ ነው። በኢትዮጵያዊ ክርስቲያናዊ ባህልና ስርዓት ውስጥ ለቆየ ከመንፈሳዊነት፣ በተለይ ደግሞ ከመንፈሳዊ አገልጋይነት የተዋረደ መንፈስ፣ ልባዊ ትህትና፣ ከትዕቢትና ከትምክህት የራቀ ንግግር እንዲሁም ምንም አይነት የአፀፋ ምላሽ የማይጠብቅ ለማገልገል የተሰጠ ስነ ምግባር ይጠብቃል። ከዚህ አንፃር ይህ የፓስተር ዳዊት ንግግር ቢያስገርምምና ጥያቄ ቢያስነሳም፣ አሁን በተለይ በተለያዩ አብያተ ክርስትያናት የሚታየውና የሚሰማው ከዚህ የላቀና የረቀቀ እጅን በአፍ የሚያስጭን እየሆነ ነው። ለምዕመናን የተባረከ ነው በማለት ራሳቸው ያመጡትን ዘይት፣ ጨውና ካናቴራ መሸጥ፣ የመንፈሳዊ አገልግሎት ስም በሚሰጧቸው ስብሰባዎችና ጉባኤዎች ታዳሚ ምዕመናን ላይ የመዋጮ ኮታ ጥሎ መንፈሳዊ ቴሌቶን ማድረግ፣ “ነቢይ” ተብሎ የተሾመው ሰው ለአንድ ግለሰብ በሚናገረው የትንቢት ቃል ሞቅ ያለ ክፍያ መጠየቅና መጠየቅና መጠበቅ. . .ዝርዝሩ ብዙ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉና በክርስትና ሃይማኖት ውስጥ ባለ በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ ለሚሰጥ ማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት በአደባባይ አፍ አውጥቶ የአገልግሎት ገንዘብ መጠየቅ ለምዕመኑም ሆነ ለሃይማኖት አባቶች እንግዳ ጉዳይ እየሆነ ነው። በመፅሐፍ ቅዱስም ሆነ በወንጌላውያን ቤተክርስትያናቱ ዶክትሪን መሰረት ቤተ ክርስትያን ለአገልግሎቷ ገቢ እንድታገኝባቸው ከተፈቀዱት ከ “መባ”፣ “አስራት” እና በበጎ ፍቃደኛ ምዕመኖች በራስ ተነሳሽነት ከሚሰጡ ስጦታዎች ውጭ መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ለንግድ ማቅረብ መሰረታዊ ጥያቄ የሚያስነሳ አነጋጋሪ አጀንዳ ሆኖ እናገኘዋለን። የኢትዮጵያ አብያተ ክርስትያናት ህብረት ፕሬዝዳንት የሆኑት ፓስተር ፃዲቁ አብዶ እንደሚሉት፣ “ቁሳቁስን በመሸጥ መንፈሳዊ በረከት ታገኛላችሁ የሚለው ቀልድ ነው። በመፅሐፍ ቅዱስ ትርጉምም “ሲሞኒ” ይባላል። እጄን የምጭንባቸው ሰዎች መንፈስ ቅዱስ እንዲቀበሉ ላድርግ፤ ለዚህ ደግሞ ገንዘብ ውሰድ ያለው ሰውዬኮ አላማው ቢሽነስ በማሰብ ሊቸረችር ፈልጎ ነው። (የሐዋ ስራ ምዕራፍ 18) ልብህ በእግዚአብሄር ፊት የቀና አይደለምና ብሩ ከአንተ ጋር ይጥፋ ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ የእርግማን ቃል አውጥቶበታል። መንፈሳዊ በረከት ለማግኘት ገንዘብ መስጠት ወይም ገንዘብ ተቀብሎ መንፈሳዊ አገልግሎት እሰጠለሁ ማለት ሲሞኒነት ነው። ቁሳቁስ መሸጥና ያልተፈቀደ ንግድ መነገድ በቤተክርስትያን ያልነበረ ልምምድ ነው። የመጣውም ከምዕራብ አፍሪካና ከሰሜን አሜሪካ ሰባኪዎች በመቅዳት ነው። በነፃ ተቀብላችኋል፣ በነፃ ስጡ ነው የሚለው፤ ይህ የግድ መከበር አለበት። ተባርከው ለቤተክርስትያን መስጠት ይቻላል፣ ለሌላ አላማ ግን መንፈሳዊ በረከትን መጠየቅ አይቻልም።”

እንደ ፓስተር ፃዲቁ ገለፃ አብያተ ክርስትያናት ፕሮጀክት ነድፈው ከመባና አስራት ውጪ ሌላ ገቢ ማሰባሰቢያ መጠየቅ ይችላሉ፤ ነገር ግን መንፈሳዊ ቋንቋ መጨመር የለበትም። የገንዘብ ፍቅርና ከፍተኛ የሞራል ችግር ካለባቸው የሃሰት አስተማሪ መሆናቸው ግልፅ ነው። የተቀባ የእግዚአብሔር ቃል አገልግሎት ቤ/ክ መጋቢ የሆነው ፓስተር ሚካኤል ወንድሙም በዚህ ኃሳብ ይስማማል፣ “በነፃ የተሰጠ የፀሃ ስጦታ ለአገልጋዮች ጥቅም መዋል ሲጀምር ስህተቱ ያኔ ይጀምራል። በነፃ የተቀበልነውን በነፃ መስጠት የግድ ነው። የፀጋ ስጦታ የሚሸጥ አይደለም። እግዚአብሔር በኔ ፈውስ ክብሩን መውሰድ ሲኖርበት እኔ የጥቅም ማሳደጃ ካደረግኩት ስህተት ይሆናል። ሌላው በዘይት፣ በጨው፣ በመሃረብ ደጋግሞ ፈውስ አለው ብሎ ማገልገል ሰዎች እምነታቸውን ከኢየሱስ ላይ አንስተው ቁሱ ላይ እንዲያሳርፉ ያስገድዳል። ይህም ተቀባይነት ያለው አይደለም።”

በሌላ መልኩ አገልጋዮች ግላዊ ስኬታቸውን በቤተክርስትያን መድረክ ደጋግመው በማሳየትና በመናገር ብልፅግናን ከመንፈሳዊ ብቃት ጋር የማገናኘት አስተምህሮ ሌላኛው እንግዳ ሁነት ነው። ይህ ክስተት በራሱ የመጣ ሳይሆን አለም ላይ በፕሮቴስታንት እምነት አስተሳሰቦች ዙሪያ በየጊዜው ከሚፈልቁ እንቅስቃሴዎች አካል እንደሆነ የሚጠቁሙን ምልክቶች አያሌ ናቸው። ይህ ስኬትና ብልፅግናን ከመንፈሳዊ እድገት ውጤት ጋር አገናኝቶ የማቀንቀን እንቅስቃሴ “የብልፅግና ወንጌል” (Prosperity Gospel) ሲባል በዚህ የቲዮሎጂ አስተሳሰብ የፋይናንስ በረከት እና ጤና ለእነሱ የተዘጋጁ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆኑና እምነት፣ መልካም አንደበትና መስጠት (Donation) የአንድን አማኝ ቁሳዊ በረከት ሊጨምሩ የሚችሉ ሃይማኖታዊ መንገዶች ናቸው ተብሎ ይታመናል። ( Prosperity theology (sometimes referred to as the prosperity gospel, the health and wealth gospel, or the gospel of success) [A] is a religious belief among some Christians, who hold that financial blessing and physical well-being are always the will of God for them, and that faith, positive speech, and donations to religious causes will increase one’s material wealth.)

ፓስተር ዳዊት በጠቀስነው ቪድዮ ውስጥ ንግግሩን ሲቀጥል፣ “ ‘ፓስተር ዳዊት በአካውንቱ 80 ሚሊዮን ተገኝቶ መንግስት አስሮታል’” ይላል በማሽሟጠጥ ለዛ…ምዕመናን ይስቃሉ…ፓስተር ይቀጥላል፣ “እኔ የሚያሳዝነኝ ጴንጤው ራሱ መንግስታችንን አላወቀውም። 80 ሚሊዮን አለው ብሎ እኔን ለምን ያስረኛል። ልማታዊ ባለሃብት ብሎ ይሸልመኛል እንጂ!” . . .ምዕመናን በሆታ ይስቃሉ።

ይህ የብልፅግና ወንጌል አስተምህሮት የንዋይ ፍቅርና አምልኮ የኃጢአት ምንጭ ነው ብሎ ለሚያምነው ለመሰረታዊው የክርስትና አመለካከት ፍፁም ባይተዋር የሆነ አቅጣጫ ይሆናል። ፓስተር ፃዲቁ በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ፍፁም ተቃውሞ ሲገልፁ፣ “የብልፅግና ወንጌል ቢሉትም። እኔ ደግሞ የስግብግብነት ስራ እለዋለው። በአለም ላይ ራሱን የቻለ አስተምህሮ ነው። አገልጋዮቹ ይበለፅጋሉ። ለኔ ስጠኝ አንተ ትበለፅጋለህ ይላሉ። መፅሐፍ ቅዱስ ግን ‘ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው’ ይላል። እነርሱ ሲያገኙ ህዝቡ ይደኸያል። ይህ የስህተት አቅጣጫ ነው። እግዚአብሔር ይባርካል፣ ያበለፅጋል የሚለው ጥያቄ አይደለም። የመንፈሳዊ አገልግሎት መለኪያው የሃብት ክምችት አይደለም። ክርስቶስ ራሱ ሲገልፅ “ከፍሬያቸው ታውቋችኋላችሁ” ብሏል። መለኪያው የኪስ ማበጥ ሳይሆን ክርስትያናዊ ባህሪ መያዝ ይመስለኛል። ከዚህ ደሃ ህዝብ እየዘረፉ ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ በመፅሐፍ ቅዱስ ተቀባይነት የለውም። እውነተኛ አገልጋይ ነፍሱን ለሰው የሚሰጥ እንጂ ከሰው የሚዘርፍ አይደለም። . . . ቁሳቁስ መሸጥ፣ ገንዘብ ለኔ ስጡኝና ትበለፅጋላችሁ ማለት፣ ፖዘቲቭ ኮንፌሽን. . . ወዘተ የአንድ አስተሳሰብ የተለያዩ አቅጣጫዎች ናቸው። ይህ የብልፅግና ወንጌል የተለያየ ቅርፅ አለው እንጂ ግማሽ ወንጌል ነው። ወይም ግማሽ እውነት ነው። ግማሽ እውነት ደግሞ ሀሰት ነው። ይህ ራሱን የቻለ የተለየ ወንጌል ነው። የተሟላውንና ክርስቶስና ሐዋርያት ያስተማሩትን የአዲስ ኪዳን አስተምህሮ የማይወክል ነው።”

የምዕመናን ድርሻ ምንድን ነው? 

አንጋፋው የፕሮቴስታንት እምነት ዘማሪ ዶ/ር ደረጀ ከበደ ቀደምትና ፈር ቀዳጅ ከሚባሉት የእምነቱ ዘማርያን አንዱ ሲሆን በተለያዩ  ጊዜና ዘመን ባወጣቸው ዝምሬዎቹ ቤተክርስትያን ውስጥ በሚታዩ የሞራልም ሆነ የአስተምህሮት ህፀፆችን በመተቸትና መንፈሳዊ ተግሳፅ በማስተላለፍ ይታወቃል። በአንድ ታዋቂ ዝማሬው እንዲህ ይላል:-
”በቤተ መቅደስ ውስጥ ሶስት አይነቶች አሉ፣

የእግዚአብሄርን መንጋ የሚያመሳቅሉ፣

ኤልሻዳይ ደጃፉን ከነሱ እስኪያጠራ፣

የጨነቀው ሁሉ አዳኙን ሳያቋርጥ እንዲጣራ፣

አደራ።“
ይህን ትክክለኛ ወንጌልና አስተምህሮዎችን ተገን አድርጎ በመእመናን እና በመንፈሳዊ ህይወትና አገልግሎት ንፅህና ላይ አደጋ እየሆነ ያለውን ሁኔታ ምዕመናን እንዴት መቀበል፣ መለየት እና መልስ መስጠት አለባቸው የሚለው ወደ መፍትሄ አቅጣጫዎች ለማምራት አይነተኛ ነጥብ ነው። መንፈሳዊ ህይወትን ከንግድና ብልፅግና ጋር በስህተት በማዛመድ ላይ የተመሰረቱት እነዚህ አስተምህሮቶችና ተግባራት ስር የሰደደ የድህነትና የመንፈሳዊ ጥያቄዎች ችግር ባሉባቸው የአፍሪካና የኤዥያ ሃገራት መስፋፋት የቻሉበት ዋነኛው ምክንያት ለፋይናንስ እንዲሁም የመንፈሳዊ ጥያቄዎች የበረታ ጉጉት ላለው የድሃ ሀገራት ህዝብ እነዚህ መንፈሳዊ ልምምዶች ፈጣን መልስ የሚሰጡ የአምላክ በረከቶች አድርጎ የመውሰድ ዝንባሌውን ስለሚጨምሩት ነው።

ፓስተር ሚካኤል ይህንን ነጥብ ሲያስረዳ፣ “ምዕመናን ሀሰተኛውን አገልግሎትና አገልጋይ መቃወም አለባቸው። ተቃውሞ ስንል ማንኛውም አገልግሎት መሰረቱ የእዚአብሔር ቃል እንደሆነ ማረጋገጥ አለባቸው።  እኔ መሰረታዊ ችግር የሚመስለኝ  ምዕመኑ በሚገባ ቃለ-እግዚአብሔርን ሳያውቅ ለችግሩ መፍትሄ ፍለጋ ወደ አምልኮ ቦታዎች ይሄዳል። መሄዱ ባይከፋም አገልግሎቱን የሚመዝንበት ዕውቀት ስለሌለው ለስህተት ተላልፎ ለመሰጠት ዝግጁ ነው ማለት ነው። ከዚህ አንፃር ሁሉም ሰው መጠንቀቅ አለበት። ችግርህን ለማስወገድ ሌላ ችግር ማምጣት ተገቢ አይደለም። እግዚአብሔርን ሳምን ችግሬን እሱ ያውቃልና ለችግሬ ብዙ መንከራተት፣ ብዙ ገንዘብ ማውጣት አለብኝ ብዬ አላምንም። ያውም እግዚአብሔር ቤት መጥቼ ለችግሬ ስል ጥሪቴን መጨረስ አለብኝ ብዬ አላስብም። ሀኪም ቤት ሄጄ ቢሆን ስመረመር፣ ስታከም ገንዘብ ላወጣ እችላለሁ። በእግዚአብሔር ቤት ግን ይህ ተገቢ አይደለም። እናም ሰዉ እምነቱን በእግዚአብሔር ላይ ቢጥልና ቢረጋጋ መልካም ነው። አገልግሎት የሚያገለግሉ ሰዎች ገንዘብ ባናበዛባቸውና እንዲስቱ ባናደርግ የተሻለ ይመስለኛል” በማለት ይናገራል።

ፓስተር ፃዲቁ በበኩሉ የወንጌላውያን አማኞች መሰረታዊ እምነት በክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ በሚለው ላይ የተመሰረተ ነው። “ነቢይ ይሁን ፓስተር፣ ሃዋርያ ይሁን የትኛውም ስም ይኑረው ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ልዩ ፈቃድ (Access) የለውም። በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ያለው ክርስቶስ እንጂ ሌላ መሃል ሰፋሪ ሊኖር አይችልም፣ የለምም። ስለዚህ ምንም አይነት መሰላል መንጠላል የለብንም። እውነተኛ ክርስቲያን ራሱ ፀልዮ ከእግዚአብሔር የሚፈልገውን ማግኘት ይችላል። ሁሉም አማኞች ይህ እውነት ሊገባቸው ይገባል።”

የሁኔታው የጉዞ አቅጣጫ

በወንጌላውያን ቤተክርስትያኖች ውስጥ ይህ ግራ የሚያጋባ አዲስ ባህል የተለያዩ  መገለጫዎች ቢኖሩትም የአንዳንድ ፓስተሮችና የሃይማኖት ተቋማቸው ድርጊት ሁኔታው አድጎ አድጎ የት እንደደረሰና ወዴትም እንደሚሄድ ሁነኛ ጥቆማ ይሰጠናል። ከነዚህ ውስጥ የአንድ ፓስተርን እንቅስቃሴ እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። ይህ ፓስተር ከሚመራው መከከለኛ የኑሮ ደረጃ ድንገት ተመንጥቆ፣ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም ገንብቶና፣ የነቢይነት ፀጋ ተላብሶ ብቅ ያለ ነው። ይህ ፓስተር አብረውት በቤተክርስትያን መድረክ ጭምር የሚቆሙ የራሱን ወደ 10 የሚሆኑ ቦዲጋርዶች ያደራጀ፣ አዲስ ቤተክርስትያን መመስረት ሳያስፈልገው አንዲት ደካማ አቅም ያላትን ቤተክርስትያን ከነምዕመኗ መግዛት የቻለ፣ ለትልልቅ ብሄራዊ የልማት ድርጅቶች የሚያቅተውን አንድ ሆቴል ውስጥ በዛጋጀው ገቢ ማሰባሰቢያ እስከ 80 ሚሊየን ብር መሰብሰብ የቻለ እንዲሁም የሚነሳበትን ወይም ሊነሳበት የሚችልን ማንኛውም ተቃውሞ በቀላሉ አፍ የሚያስይዝ ፈርጣማ ፓስተር ነው።

ይህን እንደ ምሳሌ አነሳነው እንጂ በየቦታው የዚህ ፓስተር ታናሾች የማጭበርበርበርና የሃሰት አስተምህሯቸውን በማከናወን የፋይናንስ አቅማቸውን በመገንባት ለኃያልነት ሲፍጨረጨሩ እናገኛቸዋለን። በተለይ የጊዜው አይነተኛ መገለጫ ሆኖ የምንመለከተው ከሌላው ዘመን በተለየ መልኩ የ “ነቢያት” መብዛት ነው። በወንጌላውያን ቤተክርስትያናት ዶክትሪን (በኤፌሶን 4:11 እንደተገለፀው) አንድ ቤተ ክርስትያን ከ 5 መንፈሳዊ አካላት፤ ማለትም የሐዋርያት፣ የነቢያት፣ የወንጌላውያን፣ የፓስተሮች (ወይም “እረኞች)፣ እና መምህራን የተዋቀረ ሲሆን በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ውስጥ ከሌሎቹ አካላት ነቢያት እጅግ በቁጥር በዝተው እናገኛቸዋለን። ከምዕመናን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ስንቃኘው ደግሞ የምናየው ደግሞ በአብዛኛው አገልግሎታቸው ከጥቅም ከሃብትና ከብልፅግና ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ለመረዳት ከባድ አይሆንም።

“የነቢይነት አገልግሎት ቅዱሳንን ለማገልገልና ፍፁማን ለማድረግ፣ ክርስትያኖችን ለእግዚአብሔር አላማ ማብቃት እንዲችል የተሰጠ አገልግሎት ነው።  ክርስቲያኑን ወደ ክርስቶስ ሙላት የማድረስ አላማን የያዘም ነው። የትኛውም የነቢይነት አገልግሎትም ለዚህ አላማ ብቻ የሚውል ብቻ ነው። በነቢይነት አገልግሎት  ምዕመኑ ከራሱ ጋር ያልተገናኘ ነገር ካልተነገረው ገንዘብ አይሰጥም በማለት ስህተት ሲፈጠር እናያለን ይህም ተገቢ ያልሆነ ተግባር እንደሆነ እናገራለሁ። የነቢይነት አገልግሎት ብዙዎችን ነፃ የሚያወጣ አገልግሎት ቢሆንም እንዲህ ከጥቅሙ ጉዳቱ እየበለጠ ከመጣ ግን የከፋ ነገር መከሰቱ አይቀርም ባይ ነኝ። በጥቂቶች የተነሳ የእግዚአብሄር ስም ሊሰደብ፣ ትክክለኛው ነገርም ሊወገዝ ይችላል። በነቢይነት አገልግሎት ውስጥ ሙስና ገባኮ! ብዙ ሰው ወደ ፓስተርነትና ወንጌላዊነት አገልግሎት መምጣት አቁሟል አቁሟል። ብዙዎች ወደ ነቢይነት እየተሳቡ መጡና አገልግሎቱ እያበላሸው ሄደ።” በማለት እንደ ቤተክርስትያን አገልጋይ ሁኔታው ያለውን አሳሳቢነት ኃላፊነት በተሞላው ስሜት ያስረዳል።

ይህ መንገዱን የሳተ የአንዳንድ ቤተክርስትያኖችና አገልጋዮቻቸው ተግባራት በአብያተ ክርስትያኖቻቸው የተገደበ ብቻ አይደለም። ይልቁንም ሰፊ ምህዳር ይዞ በኢንተርኔትና በሳተላይት ቴሌቪዝን ፕሮግራሞች ጭምር ተደራሽ ምዕመኖቻቸውን በአስተምህሮታቸው ያጠምቃሉ።
“ከህዝቡ በሚዘርፉትና በሰበሰቡት ገንዘብ በከፈቱት ቻናል ማስታወቂያ  ማሰራታቸው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ መደረጉ አይቀርም ፈፅሞም የተከለከለ ነው። በሃገሪቱ ደግሞ ያሱን የቻለ የብሮድካስት ህግ አለ። ከየትኛውም ሀገር ይተላለፍ የሃገሪቱን ህግ ማክበር አለበት። እዚህ ቢሮና አድራሻ ስላላቸው ቀጥጥር መካሄድ ይኖርበታል። እነርሱ የሚዘርፉት አንሶ ቢጤዎቻቸውን ከውጭ እየጠሩ እንደመልዓክ በባንዲራ አጅበው እየተቀበሉ፣ ነገም እንዲህ አድርጋችሁ እንኤን ተቀበሉኝ ቅስቀሳ ማድረግ ማቆም አለባቸው። ” በማለት ቅሬታቸውን ፓስተር ፃዲቁ ይገልፃሉ።

እንደ አብያተ ክርስትያናት ህብረት ፕሬዝዳንቱ እምነት በአለም ላይ አይ. ኤስ. አይ. ኤስ፣ ቦኮሃራም፣ አል ሸባብና አልቃይዳ አይነቶቹ የእስልምናን ተፅታ እንዲጠፋ እንዳደረጉት ሁሉ እንዲህ አይነቶቹ ድርጊቶች የፕሮቴስታንት (በተለምዶ ጴንጤ) የሚባለውን እምነትና ምዕመን ትክክለኛና መልካም ገፅታ ያጠፋል። በዚህም መሰረት የአብያተ ክርስትያናት ህብረቱ በዚህ በኩል እኛ ማን ነን? ማንን ነው የምናቃናው? ተግባራችን ምን ይሆናል የሚለውን በመወሰን ገልፆ ከዚህ ውጪ ያለው ግን እኛን አይመለከትም ብሎ የማሳወቅ አቋም ላይ መድረስ ይኖርበታል።

ሁኔታው በደምሳሳው ከላይ የጠቀስነውን ሲመስል በአንዳንድ አብያተ ክርስትያናትና በተወሰኑ ፓስተሮች እኩይ ተግባር ሰፊው የወንጌላውያን ቤተ-እምነቶችና አማኞቻቸው ለትዝብት መዳረጋቸውና መጠቋቆሚያ ለመሆን ተዳርገዋል። ይህ ሁኔታ በጊዜ ልጓም  ካልተበጀለት ወዴት ሊያድግ እንደሚችልም በቀላሉ ለመገመት አያዳግትም። ፓስተር ፃዲቁ ይህን በተመለከተ የወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ህብረቱ ባለፈው አመት ጠቅላላ ጉባኤው በህይወታቸው፣ በአስተምህሮአቸውና በአካሄዳቸው ጥያቄ የተፈጠረባቸው ህብረተሰቡን አግባብ ባልሆነ ሁኔታ የሚበዘብዙ አገልጋዮች የህብረቱን መድረኮች እንዳይጠቀሙ እንደወሰነ ገልፀዋል።

(በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ አስተያየት ያላቸውን፣ ‘ይመለከተናል’ የሚሉ ማንኛውንም አስተያየት ለማስተናገድ በራችን ክፍት መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን)

Leave a comment