History

የጄኔራል አማን አንዶም ግድያ በገዳዩ አንደበት

ሌተናል ኮሎኔል ዳንኤል አስፋውይባላል፡፡ የደርግ ዘመቻና ጥበቃ ሃላፊ ነው፡፡ “ጨካኝ፤ ምህረት የለሽ ፤ነፍሰ በላ” እንደነበር በርካቶች ይናገሩለታል፡፡ 
በንጉሰ ነገስቱም ሆነ ደርግ ተቀዳሚ ሊቀመንበር በነበሩት  ሌተናል ጄኔራል አማነ ሙካኤል አንዶም ግድያ በቀጥታ ተሳታፊም ነበር፡፡ ኮሎኔሉ ጄኔራል አማን በተገደሉ  ሁለተኛ ቀን ህዳር 16 ቀን 1976 ዓ.ም ለግዜያዊ  ወታደራዊ ደርግ 1ኛ ምክትል ሊቀመንበር ለሆኑት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም የግድያውን ዝርዝር አተገባበር ውጤት ፊልም በሚመስል መልኩ “ ሌ/ጄ አማን ሚካኤል አንዶምን  ለመያዝ የተደረገ የውግያ ዘመቻ ሪፖርት” በሚል ርዕስ በእንዲህ ያለ መልክ በፅሁፍ ሪፖርት አደረገ፡፡

ቅድመ ታሪክ

ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምና  ሶስተኛ ክፍለ ጦር ጓደኞቹ  ለወሳኞቹ ቀናት አድፍጠዋል፡፡ የደርጉ ሊቀመንበር ከደርጉ ውጭ ይመረጥ በማለት ሲያዘናጉ እና ግዜ ሲገዙ ቆይተዋል፡፡ የመጀመሪያው እጣም  ለሌተናል ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም ደረሰ፡፡ ሌተናል ጄኔራሉ ከሰራዊቱ አገልግሎት ርቀው ለ13 ዓመታት ያህል በሲቪል ስራ ከቆዩ በሁዋላ መጨረሻ ከነበሩበት ከህግ መወሰኛ ምክር ቤት በደርጉ ተመርጠው የቀድሞው ንጉስ ፊት ቀርበው ሌተናል ጄኔራል ተብለው የጦር ሃይሎች ተቅላይ ኤታማዦር ሹም ሆኑ፡፡ ወታደራዊ ደርግ ንጉሱን ከስልጣን አውርዶ ወታደራዊ መንግስት ባወጀበት  ዕለት መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም የደርጉ ዋና ሊቀመንበር ተብለው  በደርጉ ውሳኔ ተሸሙ፡፡

General Aman Andom

ይሁን እንጂ ከደርግ ሰዎች ጋር መግባባት ባለመቻላቸው ጄኔራሉ በዚህ ቦታ ከ2 ወር የዘለለ ቆይታ አላደረጉም፡፡ ከህዳር  17 ቀን976 ዓ.ም ጀምሮ ከልዩ ልዩ መንግስታዊ ስራዎች እና ተግባራት እራሳቸውን አገለሉ፡፡ ይህም ደርግ በእኔ ላይ እያሳደሙ ነው፤ መፈንቅለ መንሰግስት ሊያደርጉብኝ አስበዋል የሚል  አቋም እንዲይዝ አደረገው፡፡

ሌተናል ጄኔራል አማን  ከደርግ  በተለይም ከሌተናል ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ጋር ከፍተኛ አለመግባበት ውጥ ገቡ በተለይ በደርግ በኩል “የደርግ ሊቀመንበር ሳይሆን የክብር  ሊቀመንበር  መባል አለባቸው፡፡ ደርግን እንደሚመሩት ሆነው የሚናገሩትን ያቁሙ፤ የስልጣን ሽሚያ አድሮባቸዋል፤የደርጉ ሊቀመንበር ሆነው እንዲፈርሙ ተወስኗል ይህ ትክክል ባለመሆኑ የደርግና የሳቸው ስልጣን  ተልይቶ ለህዝብ ይገለፅ” ሲል በጄኔራሉ በኩል ደግሞ “ ደርጉ አምኖ ነው የመረጠኝ፡፡ ደርጉ ከተጠቀመብኝ በሁዋላ አሁን ለደርጉ ሊቀመንበር መሆኔ ቅሬታ ካሳደረ ስልጣኔን እለቃለሁ፡፡”  በማለት መልስ የሰጡ ሲሆን “ እኔ ሊቀመንበር ብሆን የሚኖረኝ አንድ ድምፅ ነው፡፡ የደርጉ አቋምና የእኔ ስልጣን መወሰን አለበት፡፡ የእኔን አመራር በግልፅ መወሰን አለባችሁ፡፡ በእኔላይ እምነት ከሌላችሁ እና ስራውን ሁሉ እንቆጣጠራለን ካለችሁ እኔ የፎቶ ግራፍ ጄኔራል መሆኔ ነው በዚህ አይነት አብረን መጓዝ አንችልም፡፡” በማለት አሻፈረኝ አሉ፡፡

በተለይ ኤርትራን በተመለከተ ጄኔራሉ ችግሩ በሰላም ይፈታ፤ የሰላሙ ጥረት ይቀጥል እስከዚያ ሰላም አስከባሪ ሀይል አንድ ብርጌድ ከ3ተኛ ክፍለ ጦርና  ከክብር ዘበኛ እንልካለን ብዬ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ፡፡ ወደ ጦርነት ከመሄዳችን በፊት በሰላም መሞከር ከፍተኛ ትዕግስት ቢጠይቅም ደጋግሞ መሞከ ይበጃል ደም ከፈሰሰ መቆሚያ አይኖረውም አሉ፡፡ ሌተና ኮሎኔል መንግስቱ  ከ3ተኛ ክፍለጦር ሰራዊት መላኩን ሲቃወም ከአጠቃላይ ሰራዊቱ ጦር  ወደ ኤርትራ መላኩን  ደገፈ፡፡ ይሄኔ ሌተናል ጄነራል አማን “ ደርጉ ሃሳቤን አልተቀበለም በእኔ ላይ እምነት የለውም” በማለት ራሳቸውን አራቁ፡፡

 ጄነራሉ ከህዳር 6 ቀን ጀምሮ ስራ ባለመግባት እቤታቸው ተቀምጠዋል፡፡ ተጠርተው ተባብረው ለመስራት ያላቸውን ፍቃደኝነት ወይም እንቢተኝነት ለመጠየቅ ሰው ቢላክ ፍቃደኛ አልሆኑም( መልዕክት አድራሹ ጄኔራል ግዛው በላይነህ ነበሩ) ያለው ደርግ ደርግ ንዑስ አባሎች ከያሉበት ከሰሜንና ከምስራቅ ጦር እንዲሁም ከፖሊስ(4ሰው) ጠራ፡፡ ሌ/ጄ አማን  ባሉበት ቦታ ይጠበቁ ሲልም ለሌተናል ኮሎኔል ዳንኤል፤ በጦር  ሃይሎች ውስጥ የማዘዝ ስልጣን እንዳይኖራቸው ደግሞ በጎን ለጄኔራል ግዛው ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

የፖሊስ፤የሰሜንና የምስራቅ ንዑስ አባላት ጄኔራሉን ማነጋገር አለብን ብለው ደጋግመው ቢጠይቁም  የጄኔራል አማን ጉዳይ ተወስኖ ያለቀለት በመሆኑ ማነጋገር እንደማይችሉ ተገለፀላቸው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የሌተናል ጄኔራል አማን ስልክ በደህንነት ባለሙያዎች ሲተለፍ ቆይቷል፡፡ እሳቸውም መጠለፉን እያወቁ ህዳር 13 ቀን ሱዳን ወታደራዊ አታሼ  ፀሃፊ ከሆኑት ከወ/ሮ የወርቅ ውሃ ጋር ውይይት አደረጉ ይሄም ተጠልፎ እነ መንግስቱ ጆሮ ደረሰ በንግግራቸውም ላይ፡-

“ ስልኬ ተጠልፏል የሆኖ ሆኖ እኔ አልፈራም፡፡ ሰው ሁሉ ትንሽ ጠብቅ ነው የሚለኝ፡፡  ዛሬየቁርጥ ቀን ነው፡፡ ነገ ከእናንተ ጋር ነኝ ወይም አይደለሁም እና ማንንም አልፈራም…….፡፡ መጀመሪያ ነገር ሻለቃ መንግስቱ  መቀጣት አለበት፡፡ መውረድ አለበት፡፡ ምክንያቱም ከስልጣኑ በላይ ይጠቀማል፡፡”

ይህ አባባላቸው በመንጌ ዘንድ ጥርስ አስነከሰባቸው፡፡

ጄኔራሉ የመረጠኝ  ጦሩ ስለሆነ ለጦሩ አሳወቄ መነሳት አለብኝ የሚል አቋም ነበራቸው፡፡ ይሁን እንጂ ተቀድመዋል ስልክ መስመራቸው ተጠልፎ እንኳን የሚናገሩት የሚተነፍሱት ሁሉ ይደመጣል፡፡እሳቸው ባያወቁትም የተማመኑበት ጦርም  በእሳቸው እንዳይታዘዝ ታግዷል፡፡ አሁን ጄኔራሉ ብቻቸውን ናቸው፡፡

ከመሞታቸው አንድ ቀን ቀደም  በፊት ያወሩት ነው ተብሎ ከጄኔራል ግዛው በላይነህ ጋር የተነጋገሩት የተጠለፈ የስልክ ንግግርም ደርጉ ዘንድ ደረሰ ፡፡ ምልልሱ ጄኔራል አማን ጦር እንዲንቀሳቀስ ያዘዙበት ሁኔታ እንዳለ ሚያሳይ ነበር (የመጀመሪያው የጄኔራልግዛው ቀጣዩ ደግሞ የጄኔራል አማን ምልልስ ነው)

General Aman Andom Visiting Eritrea

ጌታዬ እኔ ትዕዛዝ  ደርሶኛል፡፡ ይሄ ነገር እኮ አስቸገረኝ ጌታዬ

ምንድነው ያስቸገረህ ንገረኝ እንጂ ምን ይላል?

ለኔ የደረሰኝ መቼም ትዕዛዝ ነው ፡፡ማንኛውም የጦር ንቅናቄ እንዳይታዘዝ ነው የሚሉኝ፡፡ ጌታዬ ምነው ያነጋገርኩዎት ነገር ሁሉ…… እኔ እኮ በጣም ተቸገርኩኝ፡፡

ምነድነው የነገርከኝ?

አይ እንዲየው ሄደው ብትነጋገሩ?

ከእነሱ ጋር?

አዎን፡፡

እንዴት አድርጌ ነው የምነጋገረው? ግዛው  ምነው አንተ ደህና ሰው አልነበርክም እንዴ?

 ጌታዬ እኔስ  ደህና ሰው ነኝ…..

 በእነዚህ መቀመጫቸውን ባልጠረጉ ልጆች ነው  እኔ የምዋረደው?

መግባባት ላይ ትደርሳላችሁ ለማለት ነው፡፡

 ከማን ከሻለቆች ጋር?

ጌታ እንደው ይሄ እንቅስቃሴ በእርስዎ በኩል ባይመጣ ነው የምለው… ምናለ ሁሉንስ ቢንቁት… ያው መንግስቱ አብረን እዚህ ድረስ እንደደረስን አብረን ወደፊት አብረን እንቀጥል በላቸው ያለኝን መልዕክት ነግሬዎታለሁ ጌታዬ፡፡

እኔ ቦታ መልቀቄን ጦሩ ማወቅ የለበትም ለምንድነው ዝም የምለው እንደራስህ አመዛዝነው እንጂ ክቡራን ጓደኞቼ ለራሴ ብቻ አይደለም ይህን የማደርገው፡፡ በጦሩ ውስጥ ላሉ ከፍተኛ መኮንኖች ጭምር ነው፡፡ ካልተጠነቀቅክ ወደፊት ምን እንደሚያደርጉ ታያለህ::

                     (ጥብቅ ሚስጥር 333 ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም  ከ ጄኔራል ግዛው በላይነህ  ጋር ህዳር 1967)

 ይህንግግር በደርጉ ከተደመጠ በሁዋላ ጀነራሉ እንዲገሉ በ93 የደርግ አባላት ድምፅ ተወስኗል ተብሎ ተመሳሳይ ውሳኔ ከተላለፈባቸው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሚኒስትሮች እና ጄኔራሎች ስም ዝርዝር ውስጥ  በ58ተኛ ረድፍ ላይ ስማቸው ሰፈረ፡፡ ትዕዛዙን እንዲያስፈፅም ሌ/ኮ ዳንኤል አስፋው ከፈጥኖ ደራሽ ፖሊስና ከደርጉ የተውጣጣ አንድ ጓድ ወደ መኖሪያቸው አመራ፡፡

ድህረ ታሪክ

እነሆ የገዳይ ቡድኑ አዛዥ የሌተናል ኮሎኔል ዳንኤል አስፋው ሪፖርት በራሱ አንደበት፡-

ጄኔራሉ ተይዘው መጥተው እንዲታሰሩ ፤ አልያዝም ካሉ እንዲገደሉ ደርጉ አዘዘኝ፡፡ እኔም መድፈኛውን አዛዥ ሻለቃ ኃይሉ ፋንታዬን፤የወታደር ፖሊስ አዛዥ ሻምበል ስሜን  እና አጅቦ የሚያመጣ ቃኝ ጦር ይዤ ወደ ጄኔራሉ ቤት ሄድኩ……. በግምት በ1950ሰዓት( ወታደራዊ አቆጣጠር) ጄኔራሉ በደርግ መፈለጋቸውን በልዩ ልዩ ምነገዶች ማስረዳት ጀመርኩ፡፡ በመጀመሪያ የቤቱን  ደውል ደወልኩ እና ከቦታው ዞር አልኩ፡፡ ምንም መልስ ስለጠፋ በከፍተኛ ድምፅ ጄነራል አማን ደርጉ ዘንድ ይፈለጋሉ አልኩ፡፡ ምንም መልስ ስለሌለ ይህንኑ ሶስት ግዜ ደጋገምኩ፡፡ ሰውየው መልስ ስለከለከሉ ጄነራል አማን እጅዎን ይስጡ ባይሰጡ ይገደላሉ! ብዬ ተናገርኩ፡፡ አሁንም መልስ በመጥፋቱ ክቡር ጄነራል አምስት ደቂቃ አለዎት፤ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ባይወጡ ይተኮስብዎታል አልኩ፡፡

 ከዚያም አራት ደቂቃ ብዬ ሶስት ደቂቃ ስል ወደ ሳሎን መጡና ማነው የፈለገኝ አሉ፡፡ እኔም መልሼ ደርጉ አልኳቸው ለምን አሉ፡፡ ለስራ ነው ስላቸው አንድ በግልፅ ያልሰማሁትን ነገር ተናገሩ፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ምንም ድምፅ ስላላሰሙ እንደገና ሶስት ደቂቃ አለዎት አልኩና ወታች እቆጠርኩ 10 ሴኮንድ  ከዚያም ዜሮ ሆነ ተኩስ ብዬ የፓንሀርድ ሞርታር በሩን እንዲሠበር አዘዝኩ፡፡ ሞርታሩ ተሰናከለና ለሁለት ደቂቃ ያህል ዘግይቶ መብራት ወደ በሩ እያበራ ሲተኩስ ዋናው በር ተሰብሮ ወለል ብሎ ተከፈተ፡፡ አሁንም እጅዎን ይስጡ ብል ዝም ስላሉ የፓንሀርድ መትረየስና ኮርታር ተኩስ ቀጠለና መስኮቶች ደ ምዕራብ ያሉት ሙሉ በሙሉ ተመቱ፡፡ ቀጥሎ 5ቱን የፈጥኖ ደራሽ  ወታደሮች ይዤ ወደ በሩ ተጠጋሁና ጨበጣ ግቡ ስላቸው ከውጭ ብቻ እየተኮሱ ሳለ ሰውየው ከወደ መኝታ ቤት አከባቢ በኮሪደሩ ውስጥ እያሳለፉ አውቶማቲክ ተኩስ ተኮሱብን፡፡ ወታደሮቹ በተኩሱ ውስጥ ለመዝለቅ ስላልሞከሩ ጄኔራሉ እየተኮሱ መሳደብና መፎከር ጀመሩ “ እኔ አማን ነኝ ፣አንበሳው አማን ነኝ አታውቀኝም” እያሉ ማስፈራራት ቀጠሉ፡፡ 

 ….. መትረየስ እንዲመጣ አዘዝኩና ከጂፕ ላይ ኤ.4 ተፈትቶ መጣ፡፡ ያመጣውን ወታደር እንዲተኩስ ባዘው  መትረይስ ተኩሼ አላውቅም አለኝ፡፡ ተቀበልኩና እንዴት እንደሚተኮስ አሳይቼ ስሰጠው ተቀብሎ ምላጩን ሲጨረግድ አፈሙዙ ወደኔ ዞረ ለማምለጥ ስሞክር ከአፈሙዙ በወጣው ጥይት የቀኝ እጄን ትንሽዋ ጣት በጣም ትንሽ በሆነ ጨረፍታ ተጫረች፡፡ ወታደሩ መትሬሱንትቶ ከኪሱ ባንዴጅ አውጥቶ አሰረልኝ፡፡ እኔም መትረየሱን ተቀበልኩና በበሩና በመስኮቱ እየዞርኩ ተኩስ ብዙ ቆይቼ በመሃሉ ሻምበል ስሜ መጥቶ  ወደጎፋ ሰፈር ተኩስ ይተኮሳል በጣም ከፍተኛ ተኩስ  ነው አለኝ፡፡

እኔም ተኩሱን አዳምጨ ጦሩን ጎበዝ ተኩስ የሚተኮሰው ለሚገደሉት እስረኞች/ ለ59ሚኒስትሮችና ጄኔራሎች/ ስለሆነ ምንም አትደናገሩ፡፡ ግዳጃችሁን ቀጥሉ አልኩና እኔምወደ ቤቱ ተመለስኩ  ከዚያም ጎበዝ ወደ ውስጥ እንግባ አልኩና መትረየሱን እየተኮስኩ ወደ ሳሎን ገባሁ፡፡ የሳሎን መብራት የሚበራ ሲሆን ሰውው ያሉበት ክፍልናኮሪደር ጨለማ ስለሆነ ት እናዳሉ አይታወቅም መብራቱን እንዳላጠፋው የባሰ ችግር ይፈጠራል፡፡ አስር አለቃ አየለ ሃብተማሪያም የመትረየሱን ጥይት ይዞልኝ አብሮኝ ገባ፡፡ ቀጥሎም አስር አለቃ አየለ ከገበታ ቤትና ሳሎን መሃል ሆነን ስንተኩስ ተራ ወታደር በቀለ በጥይት ተመታ፡፡ ጄኔራሉ እያከታተሉ አውቶማቲክ ይተኩሱ ስለነበር ወታደር ጉዲሳ ገመዳ ወደ ቤቱ ውስጥ ገብቶ እንደገና ሊወጣ ሲሞክር በጥይት ተመታ፡፡ ሰውየው በተኩስ መልስ ወደሚሰጥበት ክፍል መትረየሱን ስተኩስ ተሰናከለ፡፡ ያንን መትረየስ ትቼ ዑዚ ስተኩስ አስር አለቃ አየለ መትረየሱን አስተካክሎ መተኮስ ጀመረና ድጋሚ ተሰናከለበት፡፡ እኔም ተቀብዬ ተኩስ መተኮሱን ስላቆመ ትቼለት እሱ ሲቀበለኝ በጥይት ተመታ፡፡ በዚህ መሃል ታንክ መጥቷልና አብረህ እንዳትመታ ውጣ የሚል ጩኸት  ከውጭ ስላስተጋባ በገበታ ቤቱ መስኮት ከፍቼ ዘለልኩና ወጣሁ፡፡……. ታንክ ወደቤቱ ተጠግቶ እየገፋ እንዲያፈርሰው ተደረገ……. ሰውየው በጀርባቸው ወድቀዋል፡፡……. ሌሎች ገብተው ሬሳቸውን እንዲያወጡ ጠራሁ፡፡

……ጄነራሉ ሞተው ሲገኙ አጠገባቸው አንድ ዑዚ ድግን መትረየስና አንድ ኮልት.38 ተገኘ…፡፡

 ( ህዳር 16 /1967  ከኮሎኔል ዳንኤል አስፋው  ከቀረበ ሪፖርት)

 እኚያ በዱር በገደሉ ለሀገራቸው ዳር ድንበር ደማቸውን ያፈሰሱ ፤ በሰራዊቱ ውስጥ  በጀግንነት የሚወደሱት ትልቅ ፍቅር እና ክብር  የነበራቸው በዚህም በ ጦሩ  “ኮዳ ትራሱ”  እየተባሉ የሚጠሩት ሌተናል ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም የህይወት ፍፃሜም በእንዲህ አይነት መንገድ ሊቋጭ በቃ፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s